1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሞ ኢብራሒም ስለአፍሪቃ መልካም አስተዳደር

ቅዳሜ፣ ግንቦት 12 2015

በአፍሪቃ ሃገራት እንደሚታዩት በርካታ ግጭቶች ሱዳን ውስጥ ከወር በላይ የዘለቀው የእርስ በእርስ ውጊያ ከባድ ጉዳት እያደረሰ ነው። የተመድ ትናንት ባወጣው መረጃ እስካሁን ጦርነቱ ከአንድ ሚሊየን በላይ ሕዝብ ለስደት ዳርጓል። የአፍሪቃ ሃገራት የጠብመንጃን ላንቃ እንዘጋለን ቢሉም ያሉት ግን ገና ተግባራዊ አልሆነም።

https://p.dw.com/p/4RazF
Mo Ibrahim | britisch-sudanesischer Mobilfunkunternehmer
ምስል Hollie Adams/AFP/Getty Images

«የሱዳን ተፋላሚ ጀነራሎች ለህዝቡ ደንታ የላቸውም»

በአፍሪቃ ሃገራት እንደሚታዩት በርካታ ግጭቶች ሱዳን ውስጥ ከወር በላይ የዘለቀው የእርስ በእርስ ውጊያ ከባድ ጉዳት እያደረሰ ነው። የተመድ ትናንት ባወጣው መረጃ እስካሁን ጦርነቱ ከአንድ ሚሊየን በላይ ሕዝብ ለስደት ዳርጓል። ምንም እንኳን ከተፈናቃዮቹ አብዛኞቹ በሀገር ውስጥ ከቀያቸው ቢሰደዱም በሺህዎች የሚገመቱት ወደ ጎረቤት ሃገራት ለመሸሽ ተገደዋል። ሱዳን ውስጥ የህዝብ መፈናቀል ያስከተለው ያልበረደ ግጭት የመንግሥታቱ ድርጅትን ሳይቀር እንዳሳሰበው እየተነገረ ነው። የአፍሪቃ ሃገራት የጠብመንጃን ላንቃ እንዘጋለን ቢሉም ያሉት ግን ገና ተግባራዊ አልሆነም። ከዶቼ ቬለ ቴሌቪዝን ጋር በጉዳዩ ላይ ቃለመልልስ ያካሄዱት ትውልደ ሱዳናዊው ቢሊየነር ሞ ኢብራሒም የአፍሪቃ መሪዎች ቃል አሁንም ተከብሮ ለማየት እንደሚጠብቁና ተስፋ እንዳልቆረጡ ይናገራሉ።  

ሞ ኢብራሒም ለበርካታ ዓመታት በአፍሪቃ መልካም አስተዳደር ይሰፍን ዘንድ የአስተዳደር ሥልጣን የሚይዙ መሪዎችን ለማበረታታት ጥረት በማደርግ ላይ ናቸው። ምንም እንኳን አንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች ለህዝባቸው የተሻለ በመሥራት ስኬት ቢያስመዘግቡም፤ ውጊያ እና ግጭት ከክፍለ ዓለም አፍሪቃ ባንድም በሌላ መንገድ የሚርቅ አይመስልም። በአሁኑ ጊዜ የትውልድ ሀገራቸው ሱዳን የውጊያ አውድማ ሆናለች። ሞ ኢብራሒም ይኽ ጉዳይ በግል ስሜታቸውን እንደነካው አልሸሸጉም።

«በግል የሚነካኝ እና በጣም አስከፊ ነው፤ ህዝባችን ከዚህ የተሻለ ነገር ሊያገኝ ይገባል። የምናየው ግን እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ሁለት ቡድኖች በዋና ከተማችን ውስጥ ውጊያ ላይ ናቸው። ሁለቱም ሥልጣን ነው የሚፈልጉት። ከሥልጣን ጋር ነው የፋይናንስ ምንጭ የሚገኘው፤ አስከፊ ታሪክ ነው። ታሪኩ ደግሞ የወታደሮች እና የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ታሪክ ነው። ምዕተ ዓመት ያስቆጠረ የቆየ ታሪክ ነው። ለእነዚህ ሰዎች እንግዲህ በቃ ማለት በቃ ነው ማለት ይኖርብናል።»

Sudan Bürgerkrieg | beschädigtes Ost-Nil-Krankenhaus in Khartum
በጦርነት የምትወድመው የሱዳን ዋና ከተማ ኻርቱምምስል via REUTERS

የሱዳን ተፋላሚ ጀነራሎች በተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ስለማድረግ ቢናገሩም ተግባራዊ ሲሆን አልታየም። የሰብአዊ መርሆዎችን ቃል እየገቡ ባለማክበራቸውም ሲቪሉ ኅብረተሰብ ላይ የሚደርሰው ጉዳት ተባብሷል። ሞ ኢብራሒም ተፋላሚዎቹ ጀነራሎች የኅብረተሰቡ ጉዳት አይገዳቸውም ነው የሚሉት።

«ይገዳቸዋል ብዬ አላስብም። የሚያሸንፍ ባይኖርም፤፤ እያንዳንዳቸው የሚያስቡት በሆነ መንገድ ማሸነፍ ነው። በዚህ የሚከስር እንጂ አሸናፊ ሊኖር አይችልም። ሁሉም ወገን እየከሰረ ነው፤ የሱዳን ህዝብም ተጎጂ ነው። ያለችን ጥቂት መሠረተ ልማት እየፈራረሰ ነው፤ ሀገሪቱም ውጥንቅጥ ውስጥ ገብታለች። ከወታደሮች ይልቅ የሚሞቱት በርካታ ሲቪሎች ናቸው። በጣም ያሳዝናል።»

ሞ ኢብራሒም አፍሪቃ ውስጥ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የመንግሥት ሥልጣን የሚይዙ ፖለቲከኞችን ለማበረታታት የሚሞክሩበትን መርሃግብር እየመሩ ነው። በራሳቸው የትውልድ ሀገር ጭምር የሚታየውን የማያባራ ግጭትና የእርስ በእርስ ጦርነት፤ ያስከተለውንም ውድመት እና የሲቪሉ ኅብረተሰብ ስደት መፈናቀል ሲመለከቱ የተሻለች እንድትሆን በሚመኙላት አፍሪቃ ተስፋ ቆርጠው ይሆን?

«በፍጹም፤ ከ54 ሃገራት በአንድ ሀገር የሚታይ ነው። በእኛ መዘርዝር መሠረት፣ ማለቴ ላለፉት አስርት ዓመታት የአፍሪቃን መልካም አስተዳደር የለካንበት መዘርዝር አዘጋጅተናል። አብዛኞቹ፤ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት አፍሪቃውያን ከ10 ዓመታት በፊት ከነበረው የተሻለ አስተዳደር ባለባቸው ሃገራት ነው የሚኖሩት። እናም ወደፊት እየሄዱ ነው። እርግጥነው በአንዳንድ ሃገራት ውስጥ ውድቀቶች አሉ። እንዳለመታደል ሆኖ ከእነሱ አንዷ የእኔ ሀገር ናት። ሆኖም ግን ወደፊት የምንጓዝበትን መንገድ እንፈልጋለን።»

Sudan Khartum Kämpfe Bürgerkrieg
የጦርነቱ ውድመት ገጽታ በሱዳንምስል Mohamed Nureldin/REUTERS

አፍሪቃ ውስጥ የመንግሥት ግልበጣ እንዲቆም ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም ልማዱ ግን ዳግም እንደ አዲስ እያገረሸ ነው። በቅርቡ ሱዳን ውስጥ በመደጋገሙም ሀገሪቱን ወዳልተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ከቷታል። ለወትሮው በፖለቲካ ውስጥ የወታደሩን ተሳትፎ አጥብቀው ይቃወሙ የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሁን አሁን የመንግሥትን ሥልጣን የጨበጡ ፖለቲከኞች በአስተዳደር በሚፈጽሙት ነውር ምክንያት የጦር ኃይሉን ጣልቃ ገብነት ወደመቀበሉ ሲያዘነብሉ እየታየ ነው። ሞ ኢብራሒም ግን ይኽ ለዴሞክራሲ ጠንቅ መሆኑን ያስገነዝባሉ።

«በጣም አደገኛ ነው። ችግሩ፤ ለምሳሌ ጊኒን እንመልከት፤ አልፋ ኮንዴ በሥልጣን ሲባልጉ እና በሕገመንግሥቱ ለመጫወት ሲሞክሩ፤ ተቃማዊውን ወገን በኢፍትሀዊነት ጨቆኑ። ቀድሞ ዴሞክራሲያዊ የነበረው ሰው ሥልጣን ሲይዝ፣ ሥልጣኑ እራሱ ላይ ወጣ እና አምባገነን ሆነ። እንዲህ ባለው ሰው ላይ መፈንቅለ መንግሥት ሲደረግ ህዝቡ «ግሩም ነው አስወግድልን» የሚልበት ምክንያት ይገባሀል። መፈንቅለ መንግሥቱን ደግፈውት ነው ማለት አይደለም፤ ሕገ መንግሥቱን የሚጥስና ሥልጣኑን ያላግባብ የሚጠቀም ሙሰኛ ሲቪል ባለሥልጣንን በማስወገዳቸው ነው የሚደሰቱት። »

Elfenbeinküste 2019 Ibrahim Governance Weekend in Abidjan
ሞ ኢብራሒም ምስል DW/F. Quenum

ስለመልካም አስተዳደር ሲታሰብ የሰብአዊ መብት ይዞታ፤ የህዝብ ተሳትፎ፤ ፍትሀዊነትን የተከተለው የሀብት ክፍፍል እና የኤኮኖሚ ጉዳይ አብሮ እንደሚታሰብ ያመለከቱት ሞ ኢብራሒም፤ ምንም እንኳን  አፍሪቃ ውስጥ ይዞታው ድብልቅ ቢሆንም ባለፉት አስር ዓመታ በመሠረተ ልማት እና በሰብአዊ ልማት፤ የተሻለ ትምህርትና የጤና አገልግሎትን በተመለከተ አፍሪቃ መሻሻል እንዳሳየች ነው ያመለከቱት። የጸጥታ ይዞታው እና የሕግ የበላይነትን በተመለከተ ግን እንደውም በተቃራኒው እያቆለቆለ ሄዷል ባይ ናቸው።  የአፍሪቃ መሪዎች በጎርጎሪዮሳዊው 2020 የጠብመንጃን ላንቃ እንዘጋለን ቢሉም ከተጠቀሰው ዓመት ወዲህ እንደውም ግጭት ጦርነቱ ባልተጠበቁ ሃገራት ሳይቀር የከፋ ጉዳት አስከትሏል። ይኽ ሁሉ ግጭት ጦርነት እየተካሄደ የአፍሪቃ ኅብረት ቃሉን ማክበር ስላለመቻሉ የተጠየቁት ሞ ኢብራሒም፤ «የፀጥታው ምክር ቤትስ የት አለ?የአፍሪቃ ኅብረት ይቅር  የጸጥታው ምክር ቤት ገባ? የት ነው ያለው? » በማለት ነው መልሰው የጠየቁት። እሳቸው እንደሚሉትም በመላው ዓለም ያሉ ተቋማት ችግር ውስጥ በመግባታቸው ምንም መሥራት አልቻሉም። የአፍሪቃ ኅብረት ያሰበውን ለማሳካት አቅሙ እንደሌለው በማመልከትም እንደውም ከሞራል አኳያ ከጸጥታው ምክር ቤት በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።  በጎርጎሪዮሳዊው 2006 ዓም በስማቸው ያቋቋሙት ተቋም አፍሪቃ ውስጥ መልካም አስተዳደር እና ልዩ የአመራር ችሎታችን ለመደገፍ ይሠራል። ተቋማቸው  በታወቁ በርካታ ተቋማት በነጻ የሚማሩ መሪ ለመሆን የሚያልሙ አፍሪቃውያንን ይደግፋል።

ሸዋዬ ለገሠ