1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምግቤን ከጓሮዬ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 19 2014

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሞከረ የሚገኘው የከተማ ግብርና በምግብ ምርት ዋጋ መናር ለሚሰቃየው ከተሜ አማራጭ መፍትሄን ይዞለት የመጣ ይመስላል። በመኖሪያ እና በመንግሥታዊ ተቋማት ቅጥር ግቢዎች የጓሮ አትክልቶች ልማት ከሚስተዋልባቸው ከተሞች መካከል ሀዋሳ አንዷ ናት።

https://p.dw.com/p/4EgGw
Äthiopien Gemüse aus dem Hinterhof
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ጤና እና አካባቢ

 

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ትንሣኤ ጨነው በኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት ውስጥ በአነስተኛ ደመወዝ ተቀጥረው ኑሯቸውን ከሚገፉት ሠራተኞች መካከል አንዷ ናት፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚታየው የምግብ ዋጋ መናር ትንሣኤና ባልደረቦቿን አንድ ነገር እንዲያማትሩ አስገደዳቸው፡፡ በመሥሪያ ቤታቸው በሚገኝ ትርፍ ቦታ ላይ የተለያዩ ለምግብ የሚሆኑ አትክልቶችን ለማልማት ተስማሙ፡፡ ከመደበኛ ሥራቸው ጎን ለጎን እንደ ጥቅል ጎመን ፣ ቆስጣና ሰላጣ የመሳሰሉ አትክልቶችን ማልማት የጀመሩበት ሥራቸው አሁን ውጤት እያስገኘላቸው ነው። «እያንዳንዱ ችግር የየራሱን መፍትሄ ይዞ ይመጣ»ል የምትለው ትንሣኤ ‹‹ የአትክልት ልማቱ የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ እያገዘን ይገኛል ፡፡

Äthiopien Gemüse aus dem Hinterhof
የራስን አትክልት በቀላሉ ማብቀልምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

መጀመሪያ ገንዘብ በማዋጣት በአነስተኛ ደረጃ ነበር የሞከርነው ፡፡ ነገር ግን ጥቅሙን በማየት በሁለተኛው ዙር በስፋት በመሥራት የተሻለ ምርት አግኘተናል፡፡ ይህም ምርቱን ወደ ቤቱ ይዞን በመሄድ ቢያንስ በሳምንት ሁለት ግዜ አትክልት እንድንመገብ አስችሎናል ›› ትላለች። አቶ ዘመን ለገሠ በኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት የሀዋሳ ቅንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ናቸው ፡፡ አቶ ዘመን በሠራተኞቹ ተነሳሽነት በግቢው የተጀመረው የአትክልት ልማት «ጥቅሙ የቤተሰብ የምግብ ፍላጎትን በማርካት ብቻ የተገደበ አይደለም» ይላሉ፡፡ እያንዳንዱ ተቋምና ቤተሰብ በዚህ መልኩ ከሠራ የአትክልት ገበያ ዋጋን የማረጋጋት አስተዋጽኦም እንዳለው ይናገራሉ፡፡ በሀዋሳ ከተማ የሚታየው የአትክልት ልማት ሥራ በመሥሪያ ቤቶችና ተቋማት ቅጥር ግቢ ውስጥ ብቻ የተወሰነ አየደለም፡፡ በከተማው ‹‹ ምግቤን ከጓሮዬ ›› በሚል የተጀመረው የከተማ ግብርና እንቅስቃሴ በግለሰብ መኖሪያ ግቢዎችም እየተተገበረ ይገኛል፡፡ በከተማው በሐይቅ ዳር ክፍል ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ጽዮን አለማየሁ በግቢያቸው የአትክልት ልማት የጀመሩት በአዲስ አበባ እና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የአትክልት ሥራዎችን በቴሌቪዝን ካዩ በኋላ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

Äthiopien Gemüse aus dem Hinterhof
ከጓሮ የተገኘው ቆስጣምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

‹‹ እኔስ ከምቀመጥ ለምን አልሠራም ›› በሚል የጀመሩት የጓሮ አትክልት ሥራ አሁን ለምግብ ፍጆታ ወደ ገበያ ከመሄድ እንዳዳናቸው ነው ወ/ሮ ጽዮን የገለጹት፡፡ በእርግጥ አብዛኛው ከተሜ ስለአትክልት ልማት በቂ የሆነ ግንዛቤ ላይኖረው ይችላል፡፡ ይህን ክፍተት ለመሙላት እነትዕግሥት በቃሉን የመሳሰሉ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የግብርና መምሪያ ባለሙያዎች ለነዋሪው ነጻ የድጋፍና የምክር አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው። በወ/ሮ ጽዮን አለማየሁ ግቢ ውስጥ የድጋፍ አገልግሎት በመስጠት ላይ እያለች ያገኘኋት ትዕግሥት አትክልትን በራስ ጓሮ ማምረት ከጤና አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ትላለች፡፡ የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት የሀዋሣ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘመን ለገሠ ከግብርና ባለሙያዋ ትዕግሥት ጋር አስተያየታቸው ይመሳሰላል፡፡ አቶ ዘመን በራስ ጓሮ መምረት ከማሳ እስከ ገበታ ያለውን የምግብ ሰንሰለት አጭርና ጤናማ እንዲሆን ያደርገዋል ይላሉ፡፡ በተለይ በእኛ አገር ሁኔታ የአትክልት ምርቶች ከማሳ ወደ ገበያ ሲጓጓዙና በመሸጫ ሥፈራዎች አካባቢ ከንጽህናና አጠባበቅ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመከላከል እንደሚረዳ ነው አቶ ዘመን የተናገሩት።

Äthiopien Gemüse aus dem Hinterhof
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የአትክልት ልማት ባዶ መሬት መኖር የለበትም በሚል በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የከተማ ግበርና ንቅናቄ አካል መሆኑን የአስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታውቋል። የከተማ ግብርናው ወደ ጎን እና ወደ ላይ በሚሠሩ ሁለት አይነት የማምረቻ ቦታ አዘገጃጀት ዘዴዎች እየተሠራ እንደሚገኝ በመምሪያ የእርሻ ልማት ዘርፉ ዳይሬክተር አቶ ዘርይሁን ሳርሚሶ ይናገራሉ፡፡ መምሪያው የከተማ ግብርናን ለማስፋፋት በአማካኝ ሥፍራዎች ላይ ለእርሻ ተስማሚ የሆነ አፈር በተሸከርካሪ በማራገፍ ነዋሪዎች ወደ የቤታችው አስገብተው እንዲጠቀሙበት መደረጉን የጠቀሱት አቶ ዘርይሁን የአትክልት ዘርም በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረብን እንገኛለን ብለዋል። በሀዋሳ ከተማ በግለሰብ መኖሪያ ቤቶችና በተቋማት ግቢ ውስጥ የተጀመረው የከተማ ግብርና እንቅስቃሴ ከምግብ ፍጆታና ከገበያ ማረጋገት ባለፈ ትልቅ መነሳሳትን እየፈጠረ ይገኛል። «እኛ ከዚህ በላይ ለመሄድ አቅደን እየሠራን እንገኛለን» የሚሉት የኢትዮጵያ የመድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት የሀዋሳ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘመን ‹‹ የጀመርነውን የከተማ ግብርና ለማስፋፋት ግብ አስቀምጠን እየሠራን እንገኛለን ፡፡ በቀጣይ አሁን ካሉት የአትክልት አይነቶች በተጨማሪ እንጉዳይ ለማምረት ሠራተኞቻችን በግብርና መምሪያ እና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ሥልጠና በመውሰድ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ በከተማ ማር ማምረት እንደሚቻል ማሳየት እንፈልጋልን ፡፡ በአጠቃላይ በ2015 ማለትም በሚቀጥለው ዓመት ከአፍሪካ ምርጥ የከተማ ግብርና ለመሆን ራዕይ አስቀምጠን እየሠራን እንገኛለን ›› ብለዋል።

Äthiopien Gemüse aus dem Hinterhof
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ