1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምርጫ በክረምት፦ ክፋቱ እና ደግነቱ

ዓርብ፣ ጥር 8 2012

አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመስከረም ወር ሥራ እንዲጀምር ይጠበቅበታል። ነባሩ ምክር ቤት ደግሞ የራሱን ዕድሜ ማራዘም አይፈቀድለትም። እንዲያውም የኢትዮጵያ በጀት ዓመት መዝጊያ ሰኔ 30 በመሆኑ ከሐምሌ 1 በኋላ ፓርላማው ሕጋዊ አይደለም እያሉ ‘አሁንም ቢሆን ምርጫው ዘግይቷል’ የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ ሰዎች አሉ።

https://p.dw.com/p/3WLRe
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ በጊዜያዊነት ይፋ አድርጓል። አሁን ተራው በምርጫ ሰሌዳው ላይ መጨቃጨቅ ነው። ምንም እንኳን ቦርዱ ጠቃሚ ግብዓት ካገኘሁ የጊዜ ሰሌዳውን እቀይራለሁ ቢልም። ከወዲያ እና ከወዲህ በከልካይ ሁኔታዎች ተወጥሮ መያዙን የቦርድ ሰብሳቢዋ ንግግር ይገልጸዋል። ቀኑን ያስቀመጠነው "ምርጫችን ስለሆነ አይደለም" ብለዋል፤ ይልቁንም ሊሆን የሚችለው ቀን እሱ ብቻ ስለሆነ ነው ማለታቸው ነው።

 

እንደ ምርጫ ቦርድ ገለጻ በተለመደው የግንቦት ወር እንዳይካሔድ ምርጫ ቦርድ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ለማስፈፀም የሚያስችል አቅምም ዝግጅትም የለውም። የዛሬ ሁለት ዓመት የተጀመረው የተቋማት መልሶ ማቋቋም ጉዳይ እንዳዘገያቸው ተናግረዋል። የቦርድ ሰብሳቢዋ ብርቱካን ከተሾሙ አንድ ዓመት ከሁለት ወራቸው መሆኑን ልብ ይሏል። የምርጫ ቦርድ መልሶ ማቋቋሚያ አዋጅ የወጣው እርሳቸው ከተሾሙ ወዲህ ነው። የቦርድ አባላት የተሟሉት ደግሞ የዛሬ ሰባት ወር ገደማ መሆኑን ልብ ይሏል።

 

በሌላ በኩል በመጪው ዓመት እንዳይካሔድ ደግሞ "ሕጉ አይፈቅድም"። አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመስከረም ወር ሥራ እንዲጀምር ይጠበቅበታል። ነባሩ ምክር ቤት ደግሞ የራሱን ዕድሜ ማራዘም አይፈቀድለትም። እንዲያውም የኢትዮጵያ በጀት ዓመት መዝጊያ ሰኔ 30 በመሆኑ ከሐምሌ 1 በኋላ ፓርላማው ሕጋዊ አይደለም እያሉ ‘አሁንም ቢሆን ምርጫው ዘግይቷል’ የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ የሕወሓት ወኪል፣ ከዚህ በፊት አብዛኛዎቹ ምርጫዎች በግንቦት የተካሔዱት ለዚህ ነው ብለዋል፤ በክረምት መካሔዱ ምርጫውን የይስሙላ ያደርገዋል ብለዋል። በርግጥ ነሐሴ ላይ የተካሔደም የማሟያ ምርጫ ነበር።

 

የሆነ ሆኖ የጊዜ ሰሌዳው አሁን ይፋ ሆኗል። የድምፅ መስጫው የሚካሔደው በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት ነው። ምርጫው በክረምት መካሔዱ "ብዙ ጉዳት አለው" እየተባለ ነው። ጥቅምስ አለው ይሆን?

 

ጉዳቱ ምንድን ነው?

 

ምርጫ 2012 በክረምት መካሔዱ ብዙ ጉዳቶች አሉት። ዋነኛው በቅድመ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት፥ የፖለቲካ ድርጅቶች የአደባባይ ስብሰባዎችን ማድረግ ይቸግራቸዋል። ምክንያቱም በማንኛውም ሰዓት ሊዘንብና ደጋፊዎቻቸውን ሊበትንባቸው ይችላል። በጣም ርካሹ የቅስቀሳ ዘዴ ደግሞ የአደባባይ ስብሰባ ነው። ሌላው የተዳራሽነት ችግር ነው። አብዛኛዎቹ (ከ60 በመቶ በላይ) የኢትዮጵያ መንገዶች በክረምት ለመኪና ያስቸግራሉ። የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የምርጫ ታዛቢዎች፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች እና ሌሎችም እንቅስቃሴያቸው በጣም ፈተና የበዛበት ይሆናል። ይሔ ዞሮ ዞሮ የምርጫውን አሳታፊነት ሊጎዳው ይችላል። የመራጩም ቁጥር በዚህ ሳቢያ ሊያሽቆለቁል ይችላል። ይህ ምርጫ በጣም በጉጉት የሚጠበቅ ከመሆኑም ባሻገር፥ ድኅረ ምርጫ የፖለቲካ ሒደቱ በብዙ መሠረታዊ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ሊታጀብ ስለሚችል ብዙ መራጮች ቢሳተፉበት የበለጠ ተዓማኒ ይሆናል።

 

በክረምት መካሔዱ አርሶና አርብቶ አደሮችን ሥራ ያስፈታቸዋል የሚል ስጋት ያላቸውም አሉ። ይህ ግን ውኃ የሚያነሳ መከራከሪያ አይሆንም። ከተሜዎችም በየትኛውም ወቅት ምርጫው ቢካሔድ ሥራ ላይ ነው የሚሆኑት።

 

ጥቅምስ ይኖረው ይሆን?

 

ምርጫው በክረምት ይካሔዳል ሲባል በዝምታ ጮቤ የረገጡ ሰዎች አሉ። ገና ካሁኑ በግጭት እየታመሱ ያሉት ዩኒቨርስቲዎች ያኔ ይዘጋሉ። ትምህርት ቤቶችም እንደዚያው። ይህ ብቻ ብዙ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት የላኩ ቤተሰቦችን ቀልብ አረጋግቷል።

 

ክረምት መሆኑ ከላይ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅፋት ይሆናል ያልኩት የአደባባይ ስብሰባ በዝናብ ሊበተን ስለሚችል የማይሞከር መሆኑ የተፈራውን ግጭት ይቀንሰዋል የሚል ግምት ያሳደሩ ሰዎች አሉ። ምንም እንኳን የምርጫን አስፈላጊነት ቢረዱትም፥ በአሁኑ ሰዓት ከሰላም አይበልጥብንም የሚሉት በርካታ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ምርጫው እንደነገሩ ቢያልፍም ደንታ የላቸውም። ጉዳት የተባሉትን ጥቅም ከተባለው ስናወዳድረው ግን ጉዳቱ የሚያመዝን ይመስላል።

 

ፓርቲዎቹ ምን አሉ?

 

ብዙዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች የድምፅ መስጫ ቀኑ ቅር እንዳሰኛቸው ተናግረዋል። ከሕወሓት በስተቀር አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች ምርጫው እንዲራዘም ነው የሚፈልጉት። ነገር ግን ምክንያታቸው እንደሚሉት የአርብቶ እና አርሶ አደሩ መጉላላት ብቻ አይመስልም። ቀኑ ሲቆረጥ ብዙዎቹ ዝግጅታቸው እዚህ ግባ የሚባል እዳልሆነ ተረድተውታል። ብልፅግና ፓርቲ ቀድሞም ቢሆን ያለውን የመንግሥትነት መሰላል ተጠቅሞ በቅጡ የተዘጋጀው ብቸኛው አካል ሆኗል። የጊዜ ሰሌዳው በታወጀበት ዕለትም ያለማንገራገር የተስማማው ብልፅግና ፓርቲ ነው።

 

ሕወሓት ምርጫው እንደወትሮው ግንቦት ላይ አለመካሔዱ ያስቆጨው ይመስላል። የኢዴፓ አመራር ልደቱ አያሌው ደግሞ ምርጫው በዚህ ወቅት መካሔዱ ወደ ቅድመ 2010 ሕዝባዊ ቅሬታ ይመልሰናል ሲሉ ወቅሰዋል። እንደርሳቸው አባባል በሕግ ማክበር ሥም አለባብሶ ከማረስ መጀመሪያ ወደዚህ ቀውስ የመራንን ተቃርኖ ማስታረቅ ይቀድማል።

 

እነዚህን ሁኔታዎችን ደማምረን ስንመለከታቸው ምርጫ 2012 የተሰጋውን ያክል የግጭት መንስዔ ሳይሆን ሊያልፍ ይችላል የሚል ተስፋ ያሳድራል። በተቃራኒው ደግሞ የለውጥ ምዕራፍ ይሆናል የተባለለትን ያክል ገዢው ፓርቲ በሰላማዊ የምርጫ ሒደት ይሰናበት ይሆናል ተብሎ እንደተገመተው ታሪክ የሚሠራበት ላይሆን ይችላል። ግፋ ቢል በርካታ ተቃዋሚዎች ያሉበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊፈጠር ይችላል። ለምን ቢባል በገዢው ፓርቲ እና ተቃዋሚዎች መካከል የደጋፊዎች ተቀራራቢ ፉክክር ቢኖርም የኀይል እና የመዋቅር ግን ሰፊ ልዩነት አለ።

በፍቃዱ ኃይሉ

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ«DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።