1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሜድትራኒያን ባሕር የሰመጡት ስደተኞች ቁጥር 250 ይደርሳል ተባለ

ዓርብ፣ ሐምሌ 19 2011

ከሊቢያ የሜድትራኒያን ባሕር አቋርጠዉ ወደ አዉሮጳ ለመግባት ሲሞክሩ ትናንት ባሕር ዉስጥ የሰመጡት ስደተኞች ቁጥር 250 ሊደርስ እንደሚችል ተነገረ። የሰመጠዉ ሰዉ ቁጥር 150ም ሆነ 250 7 ኛ ወሩን ባገባደደዉ በጎርጎሪያኑ 2019 ፈለገ-ሞት በሚል ቅፅል በሚጠራዉ በሜድትራንያን ባሕር ላይ ባንድ ጊዜ በርካታ ስደተኛ ሲያልቅ ይህ የመጀመሪያዉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3Mnnl
Italien Küstenwache
ምስል Getty Images/AFP/M. Mirabelli

ከሊቢያ የሜድትራኒያን ባሕር አቋርጠዉ ወደ አዉሮጳ ለመግባት ሲሞክሩ ትናንት ባሕር ዉስጥ የሰመጡት ስደተኞች ቁጥር 250 ሊደርስ እንደሚችል አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት አስታወቀ። ድንበር የለሽ ሐኪሞች (MSF-በፈረንሳይኛ ምሕፃሩ) እንዳስታወቀዉ በሕይወት ከተረፉ ስደተኞች ባገኘዉ መረጃ መሠረት እስከ ዛሬ  ድረስ  ያልተገኙት ስደተኞች ቁጥር ከ250 አያንስም። የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ከፍተኛ ኮሚሽነር UNHCR እንደሚለዉ ግን ሰምጠዉ የቀሩት ስደተኞች ከ150 ብዙም አይበልጥም።የድርጅቱ ቃል አቀባይ ቻርሊ ያክሲሌይ እንዳሉት በሕይወት የተረፉት ሰዎችም ከ140 ይበልጣል።«300 ሰዎች ከሊቢያዋ አል-ኹምስ ወደብ በጀልባ መቅዘፍ ጀመሩ።ብዙም ሳይጓዙ መስመጥ ጀመሩ።መጀመሪያ በአካባቢዉ የነበሩ አሳ አጥማጆች፣ ከዚያ ደግሞ የሊቢያ የባሕር ጠረፍ ጦር ባደረጉት ጥረት 147 ሰዎች ማዳን ችለዋል።የዳኑት ሰዎች አሁን ሊቢያ ናቸዉ።እዚያ የሚገኙ ሰራተኞቻችን ርዳታ እየሰጧቸዉ ነዉ።ስደተኞቹ እንዳሉት ጀልባ ዉስጥ የነበሩ ሌሎች 150 ሰዎች ሰምጠዉ ሞተዋል።» የሰመጠዉ ሰዉ ቁጥር 150ም ሆነ 250 ሰባተኛ ወሩን ባገባደደዉ በጎርጎሪያኑ 2019 ፈለገ-ሞት በሚል ቅፅል በሚጠራዉ በሜድትራንያን ባሕር ላይ ባንድ ጊዜ በርካታ ስደተኛ ሲያልቅ የትናቱ የመጀመሪያዉ ነዉ።በትናንቱ አደጋ ከሞቱትም ከዳኑትም አብዛኞቹ የኤርትራ፣የኢትዮጵያና የሱዳን ዜጎች ናቸዉ። 
 

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ