1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማጎ ስድስት ዝሆኖች ከገደሉ መካከል አንዱ የቀድሞ ባለሥልጣን ናቸው- የፓርኩ ኃላፊ

ረቡዕ፣ ግንቦት 26 2012

ባለፈው ሳምንት በማጎ ብሔራዊ ፓርክ ስድስት ዝሆኖችን በመግደል ከተጠረጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል የቀድሞ የወረዳ ባለሥልጣን እንደሚገኙበት የፓርኩ ኃላፊ ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። ስድስቱ ዝሆኖች ውኃ ለመጠጣት በፓርኩ ውስጥ ወደ ሚገኘው የማጎ ወንዝ ባቀኑበት በአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት መገደላቸውን የፓርኩ ኃላፊ አቶ ጋናቡል ቡልሚ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/3dCwc
Südafrika Elefantendung für Gin
ምስል picture-alliance/AP Photo/D. Farrell

«በዝሆኖቹ ግድያ የቀድሞ የወረዳ ባለስልጣናት ጭምር ተሳታፊዎች ሆነዋል»

ባለፈው ሳምንት በማጎ ብሔራዊ ፓርክ ስድስት ዝሆኖች መገደላቸውን የፓርኩ ኃላፊ አቶ ጋናቡል ቡልሚ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። «በማጎ ብሔራዊ ፓርክ ባለፈው ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ ዝሆኖቹ ውኃ ለመጠጣት ከፓርኮ ወደ ኦሞ ወንዝ ድንበር ላይ ሲወርዱ ከማኅበረሰቡ ሕገ ወጦቹ ከበው ተኩስ ከፈቱባቸው» ያሉት አቶ ጋናቡል ስድስቱ ተገድለዋል ብለዋል። አዳኞቹ የስድስቱን ዝሆኖች ጥርስ ነቅለው ወስደዋል። ሌሎች ከጥቃቱ የተረፉ ሌሎች ሁለት ዝሆኖች ወደ ደን ቢሸሹም ስድስት አዳኞች ተከትለዋቸዋል። የቀሪዎቹ ሁለት ዝሆኖች እጣ ፈንታም አልታወቀም።

አቶ ጋናቡል እንዳሉት ከሕገ ወጥ አዳኞቹ መካከል ሁለቱ በዝሆኖቹ ጉዳት ደርሶባቸዋል። እንደ አቶ ጋናቡል ማብራሪያ አዳኞቹ ከካሮ እና ከሐመር ብሔረሰቦች አባላት ሲሆኑ አንዱ ደግሞ የቀድሞ የወረዳ ባለሥልጣን የነበሩ እና በአሁኑ ወቅት በትምህርት ላይ የሚገኙ ግለሰብ ናቸው።

ዝሆኖቹን የገደሉ አዳኞች እስካሁን ለሕግ አልቀረቡም። «የጸጥታ አስከባሪ አልገባም። በወረዳ አመራር እና በሽማግሌዎች በውይይት ይፈታል ተብሎ ቀጠሮ ተይዞ ነው ያለው» ሲሉ አቶ ጋናቡል ተናግረዋል።

ሕገ ወጥ አደን በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል የሚሉት አቶ ጋናቡል «በዱር እንስሳቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በብሔራዊ ፓርኩ ሰራተኛ ላይም ጉዳት እየደረሰ ነው። አቻምናም አንድ የፓርክ ሰራተኛ ተገድሎ እስካሁን ለሕግ የቀረበ ሰው የለም» ብለዋል።

ከአምስት አመታት በፊት በተደረገ ቆጠራ በማጎ ብሔራዊ ፓርክ ወደ 175 ዝሆኖች መኖራቸው ተረጋግጧል። በኢትዮጵያ ዝሆኖች ከሚገኙባቸው በጣት የሚቆጠሩ ብሔራዊ ፓርኮች አንዱ ነው። ይሁንና በአካባቢው ያለው የሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር አቶ ጋናቡል ለሚመሩት ብሔራዊ ፓርክ ሥጋት ሆኗል።

«የጦር መሳሪያ ንግድ እና ልውውጡ አልቆመም» የሚሉት አቶ ጋናቡል «ሰው ሊያስተምር የሚችል እርምጃ መወሰድ አለበት። በኛ አቅም ብቻ የሚፈታ አይደለም። አጎራባች የሆኑ ማኅበረሰቦች ሙሉ በሙሉ የታጠቁ ስለሆኑ ኋላ ቀር የጥበቃ መሳሪያ ይዞ ጥበቃ ላይ ያለ ሰው የሚጋፈጠው አይደለም» ብለዋል።

ማጎ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ክልል የሚገኝ ሲሆን የተቋቋመው በ1971 ዓ.ም. ነበር።  በፓርኩ አካባቢ የሚኖረው ማኅበረሰብ ወደ ውስጥ በመግባቱ እንዲሁም ሕገ ወጥ አደን በመስፋፋቱ ኅልውናው አደጋ ላይ ወድቋል።

 

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ