1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማነጋገሩ የቀጠለው የረቂቅ ኤክሳይዝ ታክስ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 15 2012

በኢትዮጵያ በሥራ ላይ ያለው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 307/2002 ዓ.ም ሕጉ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር እና ከሌሎች አገሮች ልምድ አንጻር መሻሻል ስለሚገባው ወደ 19 በሚደርሱ የተለያዩ ምርቶች ላይ የኤክሳይዝ ታክስ ለመጣል በገንዘብ ሚኒስቴር ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ታኅሣሥ 7 ቀን 2012 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።

https://p.dw.com/p/3VK8x
Geldscheine
ምስል DW/E. Bekele Tekle

ከኤኮኖሚው ዓለም

በዚህ መሠረት ተጨማሪ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣልባቸው የተዘረዘሩት ማነጋገር ቀጥለዋል። የምጣኔ ኃብት ምሁራን በተለይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን የተመለከተውን በአዎንታዊነት፤ በዚህ ዘርፍ ንግድ የተሰማሩ ወገኖች ደግሞ ትችት እያቀረቡ ነው። 

የገቢዎች ሚኒስቴር እንደሚያብራራው ኤክሳይዝ ታክስ የቅንጦት ዕቃዎች ሆነው ዋጋቸው ጨመረም አልጨመረም መሠረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ተፈላጊነታቸው በማይቀንስ እቃዎች ላይ እንዲሁም የኅብረተሰቡን ጤና የሚጎዳ እና ማኅበራዊ ችግሮችን የሚያስከትሉ ዕቃዎችን አጠቃቀም ለመቀነስ ሲባል የሚጣል የታክስ አይነት ነው። በኢትዮጵያ በሥራ ላይ ያለው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 307/2002 ዓ.ም ሕጉ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር እና ከሌሎች አገሮች ልምድ አንጻር መሻሻል ስለሚገባው ወደ 19 በሚደርሱ የተለያዩ ምርቶች ላይ የኤክሳይዝ ታክስ ለመጣል በገንዘብ ሚኒስቴር ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ታኅሣሥ 7 ቀን 2012 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።
በረቂቅ አዋጁ ከተካተቱ የታክስ ምጣኔዎች ከፍተኛ ቀረጥ እንዲጣልባቸው የቀረበው የተሽከርካሪ ምርቶች ላይ ነው። ድንጋጌው ለግብርና ዘርፍ ግልጋሎት የሚሰጡ ትራክተሮች ላይ እስክ 400 በመቶ ፣ ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ደግሞ እንደ የጉልበት መጠናቸው እስከ 500 በመቶ ቀረጥ ለመጣል ታስቧል። የምጣኔ ሃብት ተንታኙ አቶ ሽዋፈራሁ ሽታሁን በሲጋራ፣ ቢራ እና ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ሊጣል የታሰበው ታክስ ተገቢም ወቅታዊም ነው ብለው ያምናሉ። ሲጋራ ከማጨስ የሚገኝ ማኅበራዊ እርካታ የለምም ብለዋል።
በተሽከርካሪ ረገድም የአሮጌ ተሽከርካሪዎች ማራገፊያ ሆነን መቀጠል የለብንም ። መንግሥትም ለነዳጅ ማስመጫ የሚያውለውን ድጎማ ትምህርት ቤት እና ጤና ጣቢያ ለመገንባት ነው ሊያውለው የሚገባድ ይላሉ። በአዲስ አበባ ዩኑቨርሲቲ አካውንቲንግ እና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል የፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሰዋለ አባተ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ሊጣል የታሰበውን ታክስ በአወንታ ይመለከቱታል። ለሃገር ውስጥ የተሽከርካሪ አምራቾች ትልቅ የፖሊሲ ማሻሻያ መሆኑን በማመልከት የሥራ እድል እንዲፈጠር ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠርች፣ የውጭ ምንዛሪ ወጪያችን እንዲቀንስም ይረዳል ይላሉ።
ይህ ሲደረግ ግን በተለይ ለሀገር ውስጥ የተሽከርካሪ አምራቾች መንግሥት አስቻይ ሁኔታዎችን ማለትም የቴክኒክ ፣ የፋይናንስና ፣ የመሬት አቅርቦቶችን ማቅረብ እንዳለበት ፤ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ደግሞ በፍራንቻይዚንግና በጆይንትቬንቸር ከውጭ ባለሃብቶች ጋር ሃብታቸውን እያጣመሩ እንዲሰሩ ሊያግዝ እንደሚገባ አቶ ሽዋፈራሁ ሽታሁን ጠይቀዋል። በሌላ በኩል መሠረታዊ ምርቶች ላይ ሊጣም የታሰበው የኤክሳይዝ ታክስ ተቀባይነት የሌለውና የሀገሪቷን የኑሮ ሁኔታ ያላገናዘበ እንደሆነ ነው ባለሙያዎቹ የሚከራከሩት። የምጣኔ ሃብት አዋቂዎች የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ብለው ከሚገልጿቸው ጉዳዮች አንዱ መገለጫ የበጀት ጉድለት ነው። የኢትዮጵያ የበጀት ግኝት ታሪክ በአብዛኛው ብድር እና እርዳታ በመሆኑ ይህንን ልምድ ለመቀየርና የራስን በጀት በራስ ለመሸፈንም የኤክሳይዝ ታክሱ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ፍንደሆነ ታምኖበታል። የረቂቅ ህጉ መውጣት በጎ እርምጃ ቢሆንም የሃገሪቷ ህግን ተፈጻሚ የማድረግ ልምድ በዚህ ረቅቅ ላይም መሰል ችግር ፍንዳያስከትልም ባለሚያዎቿ ጠይቀዋል።

Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ