1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕበራዊ የመገናኛ ዘሬዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሐምሌ 29 2014

የአውሮፓ ሕብረትና የአሜሪካ ልኡካን የትግራይ ጉብኝት፣ የደቡብ ክልል ወደ ሁለት ክልሎች ይከፈላል ስለመባሉና በተለይ በአዲስ አበባ ስለተስፋፋው ውንብድና በማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን ይዘን ቀርበናል።

https://p.dw.com/p/4FBGW
Symbolbild Facebook & Meta | Pfeil nach unten
ምስል Jakub Porzycki/NurPhoto/picture alliance

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የአውሮ ሕብረትና የአሜሪካ ልኡካን የትግራይ ጉብኝት፣ የደቡብ ክልል ወደ ሁለት ክልሎች ይከፈላል ስለመባሉና በተለይ በአዲስ አበባ ስለተስፋፋው ውንብድና በማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን  ይዘን ቀርበናል።

በአፍሪካ ቀንድ የአውሮፓ ሕብረት ልዩ መልእክተኛ አኔተ ቬበር እና የአሜሪካው ልዩ መልእክተኛ ማይክ ሀመር፣ባለፈው ሳምንትና በዚህ ሳምንት መጀመሪያ አዲስ አበባና መቀሌ ነበሩ። ሁለቱ መልዕክተኞች በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው የኢትዮጵያንና የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ባለስልጣናትን አነጋግረዋል።  በመቀሌው ጉብኝታቸው ላይም የተባበሩት መንግስት ድርጅት ተወካዮች እና ሌሎች መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ተገኝተዋል። የዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ልዑካን በዚህ ሳምንት ሰኞ በጋራ ባወጡት መግለጫ« በትግራይ ክልል የመብራት፣ የቴሌኮም አገልግሎት፣ የባንክ እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች በፍጥነት ወደነበረበት እንዲመለሱ  ጠይቀዋል።  በመግለጫው እንደተጠቀሰው ቬበርና ሀመር  ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት ድርድር እንዲጀመር ለማበረታታት ነው ተብሏል።  በሁለቱ ዲፕሎማቶች ጉብኝት ላይ በማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች የተለያዩ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። ከመካከላቸው ማሜ ሐበሻ የተባሉት የፌስቡክ ተጠቃሚ  «የሚሳካ አይመስለኝም ነጮችን አላምንም »ብለው ሐሳባቸውን በአጭሩ ሲቋጩ አበባየህ ደግሞ «በትክክል» የሚል አጭር አስተያየት አስቀምጣለች። ብሩክ ያሲኖ በፌስቡክ «ነገ ጠዋት ሁሉም አገልግሎቶች ቢጀምሩ ጎንበስ ብለው መሬት ከሚስሙ ሚሊዮኖች የአዲስ አበባ ነዋሪ ዜጎች አንዱ እኔ ነኝ። ከደስታዬ ብዛት በመንገድ የማገኘውን ሁሉ "እንኳን ደስ እያለን" እያልኩ የምስም ሁሉ ይመስለኛል። እንኳንስ የገዛ አጥንታችን ፍላጭ የስጋችን ቁራሽ ወገኖቻችን ይቅርና በየትኛውም የአለም ክፍል ያለ የሰው ልጅ ሁሉ የሰላም አየር እንዲተነፍስ፤ በብርሃን እንዲመላለስ ፀሎታችን አይደለምን?ሲሉ ምኞታቸውን ገልጸው«የሚመላለስብኝ ጥያቄ»ያሉትን አስቀምጠዋል።«የተጠቀሱት አገልግሎቶች ተጠግነው መቅረብ የሚችሉት እንዲሁም የሚተዳደሩት በፌዴራል መንግሥት መዋቅር በመሆኑ የፌዴራሉ የአስተዳደር መዋቅር ፈፅሞ በሌለበትና ክልሉ በታጠቁ አማፂያን እጅ ባለበት ሁኔታ ማቅረብ እንደምን ይቻላል ነው? ለምሳሌ አሜሪካ አፍጋኒስታንን ተቆጣጥራ ባስተዳደረችባቸው 20 አመታት በታሊባን ቁጥጥር ስር በነበሩ ግዛቶች መሰል አገልግሎቶች ይቀርቡ ነበር ወይ? ከሆነ እሰየው ተሞክሮውን መውሰድ ይቻላል። በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል።

Logos von Facebook und TikTok nebeninander
ምስል Jakub Porzycki/NurPhoto/picture alliance


በኢትዮጵያ ዋናዋና ከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ በጠራራ ጸሐይ ሰዎች ይገደላሉ መኪናን ጨምሮ ንብረት ይዘረፋል። በዚህም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተለይም የሜትር ታክሲ ባለቤቶችና ሹፌሮች ሰብሰብ ብለው ቁጣና ሐዘናቸውን የገለጹበት ዘገባ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን ትኩረት የሳበ ሌላኛው ርእስ ነበረ።  ሕዝቡ በጠራራ ጸሐይ የሚፈጸምን ውንብድና ሲያማርር የአዲስ አበባ የጸጥታ ሐላፊዎች «አንዴ ዝርፊያው ቢኖርም ወሬው መነገሩ ግን የአገሪቱን መልካም ገጽታ ለማጠልሸት ነው ሲሉ ሌላ ጊዜ ደግሞ በከባድ ውንብድና የተሰማሩ ሰዎችና በርካታ የጦር መሳሪያዎችንና መሰል ጥይቶች መያዛቸውን ይገልጻሉ። በዚህ ላይ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተሰነዘሩ አስተያየቶች በርካታዎቹ ስድብ የሚያመዝንባቸው በመሆኑ ከዚህ የጸዱትን በአጭር ባጭሩ እንመልከት።
ቀስቱ ደመቀ በፌስቡክ «ህዝባችን አስፈላጊውን ክትትል በማደረግ ለመንግስት ጥቆማ ያድርግ »ሲሉ የንፋስ ስልክ ልጆች በሚል በፌስቡክ የጻፉት « የቀድሞ የኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ ይሻሻል ! ህጉ ወንጀለኞችን አደብ ሊያሲዝ ይገባል።  አለበለዚያ ዜጎችን በጠራራ ፀሐይ የገደለ ወንጀለኛ በ10 እና 15 ዓመት ብቻ በሚቀጣበት የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ወንጀልን መከላከል ከባድ ነው።» ብሏል።
የዝራ ባቢ አስተያየት ደግሞ « ምን ዛሬ ሰርቆ ቢታሰር ነገ ትፈቱታላችሁ የሚል አጭር አስተያየት አስቀምጠዋል። ዳንኤል ዳንሳ ደግሞ በወንጀል ተግባር ላይ የሚደረግ ምርመራ መጠናከር አለበት የሚል ነው።
በደቡብ ክልል የሚገኙ 10 ዞኖችና 6 የልዩ ወረዳ መስተደድር ም/ቤቶች አሁን ያለውን የደቡብ ክልል በሁለት አስተዳደር ለማዋቀር የሚያስችለውን ውሳኔ ባሳለፍነው ቅዳሜና እሁድ ባካሄዷቸው ጉባኤዎች አጽድቀዋል፡፡ በም/ቤቶቹ ውሳኔ መሠረት የዎላይታ ፣ የኮንሶ ፣ የጋሞ ፣ የጎፋ ፣ የደቡብ ኦሞ ዞኖች ከአማሮ ፣ ከቡርጂ ፣ ከአሌ ፣ ከደራሼ እና ከባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ጋር በመሆን በአንድ ክልል የሚደራጁ ይሆናል፡፡ እንዲሁም የሃድያ ፣ የጉራጌ ፣ የስልጤ ፣ የሀላባ ፣ የከንባታ ጠንባሮ ዞኖችና የየም ልዩ ወረዳ ደግሞ ራሱን በቻለ ሌላኛው ክልላዊ መንግሥት ሥር እንዲሆኑ ያስችላል ነው የተባለው ፡፡
የነጻነትና እኩልነት ፖርቲ ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መኢአድ ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ኢዜማ እና ህብረ ኢትዮጵያ ፖርቲዎች ባወጡት የጋራ መግለጫ ከደቡብ ክልል የአደረጃጀት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የዳሰሳ ጥናት ማድረጋቸውን ጠቅሰው ይህ ከመተግበሩ በፊት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡ በዚህ ሐሳብ ዙሪያ በርካታ ሐሳቦች ተሰንዝሯል     
ኢማንዳ በፌስቡክ ከላኩት መልዕክት ውስጥ  «በክልል የመደራጀቱ ነገር ለጉራጌ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ተራ የፖለቲካ ጥያቄ ሳይሆን ህልውናውንና አንድነቱን የማስቀጠል ወይም አደጋ ላይ የመጣል የሞት ሽረት አጀንዳችን ነው። ማንም በመረጠውና በፈለገው መልኩ መደራጀት ይችላል ውሳኔውን እናከብራለን።»የሚለው አስተያየት ይገኝበታል። 
ኢሳያስ «ክልል ክልል የሚሉ ቢሰጣችው ምን ሊፈጥሩ ነው?  ዝም ብሎ ህዝብን የሚያውኩ ስግብግብ ፖሎቲካኞችና አክቲቪስት ባዮች ላይ መንግስት መታገስ አያስፈልግም።» በማለት ጠጠር ያለ አስተያየት አስፍረዋል።

Hass im Netz Symbolbild | Telegram
ምስል Stephan Schulz/dpa/picture alliance

እስራኤል መስፍን በበኩላቸው «የሚገርመው የወላይታን ህዝብ የማይመጥን አስተያየት ነው በየሚዲያው የምንሰማው። ህዝቡ ታታሪ እና እግዚአብሔር የሚፈራ ሀገሩን የሚወድ ህዝብ ነው። ታዲያ የጥቅመኞች አስተያየት ግን ሌላ ገጽታ ለመስጠት ያለመ መሆኑን ሁሉም መገንዘብ አለበት። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ።ብለዋል።
ዳንኤል የተባሉ የፌስቡክ ተሳታፊ«ሲጀመር እንዴት ይሆናል? ሲዳማ ማን ነው? ጌዴኦስ ምንድ ነው? ወላይታስ?  ሁሉም ደቡብ ነበሩ። ለሲዳማ ብቻውን ክልል ሰጡት። ለለሎች ሲሆን  በክላስተር ተደራጁ ለምን? ጌዴኦ ክልልን ቢሰጠው ምን ያንሰዋል? ወላይታስ ምን ይጎለዋም? »በማለት ይጠይቃሉ።መሐመድ በድሩ ይስሃቅ ያሰፈሩት ሐሳብ ደግሞ

ጉልበት ወይስ ሰላም? የጉራጌ ብሔረሰብ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር እና በክልል መዋቅር እንዲደራጅ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መብቱን መጠየቅ ከጀመረ ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ አስቆጥሯል። ዳሩ ግን ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ጥያቄውን «አሻጥርና ሴራ» ባሉት ጠቅለው እያንከባለሉት እስካሁን ፀጥ እንዳሉ አሉ። ከጉራጌ ህዝብ የመደራጀት ጥያቄ በኋላ የመጡ የመዋቅር ጥያቄዎች በፍጥነት ሲፈቱ በአይናችን ተመልክተን ታዝበናል።
የነዚህ ወንድሞች ጥያቄ መመለስ የሚያስደስት ቢሆንም ቅሉ ጥያቄያቸው በፍጥነት የመመለሱ ሚስጥር መብታቸውን የጠየቁት በሰላማዊ መንገድ ሳይሆን ጉልበት በቀላቀለ መንገድ መሆኑ ብቻና ብቻ እንደሆነ ፀሃይ የሞቀው  ነጭ ሃቅ ነው።
ሃገር ያለችበትን ውጥረት ተገንዝቦ፣ መንግስት ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት አስገብቶ፣ ጉልበት ሳይሆን ሰላማዊ ውይይት ለሃገራችን ጥያቄዎች አማራጭ የሌላቸው መፍትሄዎች ናቸው ብሎ የሚያምን ኩሩ እና ሆደ ሰፊ ማህበረሰብ ለምን ድምፁን ማፈን ተፈለገ?  የሰላምን መንገድ የመረጡት ለምን ተናቁ?ይህን ጥሬ እውነት ለመመስከር የግድ ጉራጌ መሆን አይጠበቅብህም። ለእውነት የምትኖርና ምክንያታዊ ሰው ከሆንክ ለሃገራችን ኢኮኖሚ ትልቅ  ሚና ያለውን ብሔር ክላስተር በሚባል የህግ መሰረት በሌለው ባእድ ቃል ማጨቅ ፍፁም ስሜት የማይሰጥና ኢ-ምክንያታዊ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ሕጋዊ መሠረት ያለውን ጥያቄ ፍፁም ሰላማዊና ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ እየጠየቅን ነውና በህጉ መሠረት አስተናግዱን። ለዛሬ ያልነውን በዚሁ እናጠቃልላለን።

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር 

ኂሩት መለሰ