1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምር 3 የእንስሳት ተዋህሲያንን ለይቷል

ረቡዕ፣ ሐምሌ 17 2011

በኢትዮጵያ ለእንስሳት ሀብት ምርታማነት ማነቆ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ የበሽታዎች መስፋፋት ነው። በዘርፉ የሚገኝውን ጥቅም ለማሳደግ በሽታዎችን በሳይንሳዊ አሊያም በባህላዊ መንገድ መከላከልና ማስወገድ የግድ ይላል። በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የተደረገ ምርመር በዓለም ላይ የተገኘ አዲስ የእንስሳት በሽታ አምጪ ተህዋሲ ዝርያ በኢትዮጵያ መኖሩንም አረጋግጧል።

https://p.dw.com/p/3Mg2D
Kenia Rinderhüter und Rinder in Kajiado
ምስል dapd

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምር 3 የእንስሳት ተዋህሲያንን ለይቷል

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ብዛት ከአፍሪካ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ትመደባለች። ይሁን እንጂ የአረባብ ሂደቱ ለረጅም ዓመታት በሳይንሳዊ ምርምሮች ያልተደገፈ እና በተለምዶዊ መንገድ የሚከናወን መሆኑ አገሪቱ ከዘርፉ የታሰበውን ጥቅም እንዳታገኝ እያደረጋት ይገኛል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በእንስሳት እርባታ ዘርፍ ሳይንሳዊ የምርምር ድጋፎችን ማድረግ ጀምረዋል። በዚህ ረገድ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወተት ላሞችን የእርባታ ሂደት ለማስተጓጎል ምክንያት የሆኑ ሶስት የበሽታ አምጪ ተህዋሲ አይነቶችን በምርምር የለየበት ስራ በምሳሌነት ሊጠቀስ ይችላል።

በዩኒቨርሲቲው የእንስሣት ትምህርት ክፍል አስተባባሪ ፕሮፌሰር ካሳሁን አስማረ እንደሚሉት የበሽታ አምጪ ተህዋስያኑ የህይወት ዑደታቸውን የሚያካሂዱት በእንስሳቱ ውስጥ ብቻ አይደለም። ይልቁንም እንደውሻ ከመሳሰሉ ሌሎች የቤት እንስሳት ጋር ከፍተኛ ተዛምዶ እንዳላቸው በምርምር ስራው ለማረጋገጥ መቻሉን ጠቅሰዋል። ይህም የመተላለፊያ መንገዶቹን በማስፋት እና እንስሳቱን ለከፍተኛ ጉዳት በመዳረግ የምርት መጠኑ እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑን ፕሮፌሰር ካሳሁን ያብራራሉ። በምርምር ስራው የእንስሳቱ የመራባት ሂደት ለማጨናገፍ ምክንያት የሆኑ የበሽታ አምጪ ተህዋስያኑ ያላቸው ባህሪ ላይ ጥናት ተደርጓል። በተጨማሪም በዓለም ላይ የተገኘው አዲስ የተህዋሲ ዝርያ በኢትዮጵያ መኖሩን ለማረጋገጥ መቻሉን ፕሮፌሰሩ አስረድተዋል።  

Kuh Mikrochip Ohr
ምስል Getty Images

ተመራማሪውእንደሚሉት ኢትዮጵያ ሰፊ የእንስሣት ሀብት ቢኖራትም ከዘርፉ የሚገኘው የወተት እና የስጋ ምርቶች አቅርቦት ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለዚህ ደግሞ እነኝህ የበሽታ አምጪ ተህዋሲያን የእንስሳቱን የውልደት ሂደት በማስተጓጎል ለምርቱ አለማደግ ምክንያት መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። የበሽታ አምጪ ተህዋሲያኑ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት የየራሳቸውን ድርሻ መወጣት ይገባቸዋል የሚሉት ተመራማሪው በተለይም የእንስሳት አርቢው ሊያደርግ ይገባል የሚሉትን ምክረ ሀሳብም ጠቁመዋል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ተስፋለም ወልደየስ