1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መፍትሄ ያላገኘው የአማራው መፈናቀል

ረቡዕ፣ ግንቦት 29 2010

ከቤንሻንጉል እና ከኦሮሚያ ክልሎች የተፈናቀሉ ጥቂት የማይባሉ የአማራ ተወላጆች ዛሬም በተለያዩ መጠለያ ስፍራዎች እንደሚገኙ አመለከቱ። ተፈናቃዮቹን ወደ ነበሩበት አካባቢ ለመመለስ የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ ከኅብረተሰቡ የተውጣጣ አንድ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ከቤንሻንጉል ከተፈናቀሉት 50 ገደማውን ወደቦታቸው መመለስ ማስቻሉን ገልጿል።

https://p.dw.com/p/2z3Fy
Äthiopien Ausnahmezustand
ምስል James Jeffrey

የተወሰኑት ወደቤንሻንጉል ቢመለሱም አብዛኞቹ ስጋት አላቸው

ዛሬም ከቤንሻንጉል ክልል የተፈናቀሉ ከአንድ መቶ የሚበልጡ ወገኖች ባህር ዳር ከተማ ከሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እንደተጠለሉ ነው። ከኦሮሚያ ክልል ከቡኖ በደሌ ዞን ዴዴሳ ወረዳም በየካቲት ወር መጀመሪያ ቀናት የተፈናቀሉት ከ400 የሚበልጡ የአማራ ተወላጆች በክልሉ ርዕሰ መዲና ባህር ዳር በመጠለያ ስፍራ ተጠግተው እንደሚገኙ ይናገራሉ። 

«ከወራዳው 400 ነው የተፈናቀልነው፤ ያው ከ1999 ጀምሮ የእምነት ብጥብጥ አለ። በዚያን ሰዓት ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠል፤ ሰዎችም ሲታረዱ ነበረ። መንግሥት ማረጋጋት አድርገናል፤ በቦታችሁ ተመለሱ ተብለን ተመልሰን እየሰራን ቆየን። የካቲት ሰባት ሙሉ ለሙሉ ንብረታችን አወደሙ፤ የሞቱም ሞቱ።»

ቤት ንብረታችን ተቃጥሏል የሚሉት እነኚሁ ተፈናቃይ ዜጎች ከድንኳን መጠለያ እና ከዕለት ቀለብ የዘለለ ድጋፍ እስካሁን እንዳላገኙም ያስረዳሉ። ከኦሮሚያ የተፈናቀሉት ቀሪዎቹ የክልሉ መንግሥትን አንዳች መፍትሄ ይሰጠናል በሚል እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል።  ለተፈናቀሉት ወገኖች መፍትሄ የሚያፈላልግ  ከሃይማኖት አባቶች ሦስት ፤ ከምሁራን ወኪሎች ሁለት እንዲሁም የክልሉን መንግስት በመወከል የርዕሰ መስተዳድሩ አማካሪ የሚገኙበት ኮሚቴ ወደ ቤንሻንጉል ተጉዞ ነበር። እነዚህ ከተለያየ የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ወገኖችም ከተፈናቃዮቹ በቃል የሰሙትን በስፍራው ተገኝተው ለማጣራት ችለዋል ይላሉ ከኮሚቴው አባላት አንዱ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ እና ኤኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን እና የማኔጅመን ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ጌትነት አንስማው።

«በጆሯችን የሰማነውን በዓይናችን አይተን ለማረጋገጥ በቦታው ሄድን። የደረሰውን ጉዳት አይተናል፤ የተቃጠሉ ቤቶችን አይተናል። በወቅቱ የነበረው መረጃ 13 ሰዎች እንደተገደሉ ነበር። በነበረው ውይይት ዘጠኝ ከአማራው፤ አንድ ከጉምዝ ተወላጅ ባጠቃላይ የአስር ሰዎች ሕይወት ማለፉን የሃይማኖት አባቶችም በቦታው ላይ ተገኝተው ጸሎት አድርገን፤ የወረዳው አስተዳዳሪ ተወካይ ፤ የዞኑ አስተዳዳሪ ባሉበት ከማኅበረሰቡ ጋር ውይይት አድርገናል።»

Äthiopien Ausnahmezustand
ምስል James Jeffrey

በዚሁ መሠረትም ከቤንሻንጉል ከተፈናቀሉት ሃምሳ አንድ የሚሆኑት ወደዚያው ለመመለስ መቻላቸውን ያስረዳሉ። ቤት ለፈረሰባቸው ሰላሳ ሰላሳ ቆርቆሮ እና ምስማር ፤ ሲሚንቶ እንደተሰጠ እንዲሁም ምግብም እንደተጫነም ይዘረዝራሉ። አሁን ባህር ዳር ላይ የቀሩት ደግሞ ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ የመፈናቀል ሁኔታ እንደነበር በመጥቀስ በመፍትሄ መፈለጉ ሂደት የተሰጠው ዋስትና በቂ አይደለም የሚሉ መሆናቸውንም አስረድተዋል። ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደመጡበት ስፍራ እንዲመለሱ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ በቤተ ክርስቲያን ተጠልለው መቀመጠን ለምን እንደፈለጉ የጠየኳቸው ከተፈናቃዮቹ አንዱ፤ ራሳቸውም ተፈናቃዮችን ወክለው ከሄዱት አንዱ መሆናቸውን በመጠቆም እንዲህ ይላሉ።

«እዛ ቦታ ስንሄድ የመግባባት ሁኔታ አልተፈጠረም። እርግጥ እንደኮሚቴ ከመቶ ስልሳ ሕዝብ በቤተ ክርስቲያን ተጠልለን ከቆየነው 24 ሰዎች ወደ ቦታው ገብተዋል። እነዛም የተለያዩ ባለሃብቶች፤ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ያላቸው ናቸው ወደዚያ እንዲገቡ የተደረገ እንጂ ከዚያ ከ159 ቤቱ ከወደመ ከአራት ሰዎች ውጭ የተመለሰ የለም።»

ከአንድ መቶ የሚበልጡ ተፈናቃዮች የተጠጉበት የባህር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ገብረ ጻዲቅ ታረቀኝ የመፍትሄ አፈላላጊው ኮሚቴ አባል ናቸው። እስካሁን ሕዝቡ እየረዳቸው መሆኑን በማመልከት የተገኘውን መፍትሄ አልተቀበሉንም ነው የሚሉት።

ላለመመለስ ያስወሰናቸው ለደህንነታቸው የገባቸው ስጋት መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተዋል። በተለይም ጉዳዩን ወደመገናኛ ብዙሃን አድርሰዋል የተባሉ ወገኖች ማስፈራሪያ እንዳጋጠማቸውም አንስተዋል። ከቤንሻንጉል በመጀመሪያ የተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች 527 እንደነበሩ የገለጹት እኝሁ ግለሰብ ከምግብ ዋስትና የሚመገቡት እየተሰጣቸው ቆይተው ከ300 የሚበልጡት እርሻ ሜካናይዝድ በሚባለው ስፍራ መጠለያ ውስጥ ገሚሱ እንዳሉም ዘርዝረዋል። አሳሳቢዉ ግን አሁንም መፈናቀል መቀጠሉ መሆኑንም ተናግረዋል። ተወላጆቹ የተፈናቀሉበትን የአማራ ክልልን የሚመለከታቸው ኃላፊዎችን አስተያየት ለማግኘት ብንሞክርም አልተሳካም።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ