1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“መጪው ምርጫ ሁከትን ሊያቀጣጥል ይችላል” -ክራይስስ ግሩፕ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 6 2012

ኢትዮጵያ ዉስጥ ዘንድሮ ይደረጋል የተባለዉ ምርጫ በሀገሪቱ ውስጥ የሚታየውን ክፍፍል ሊያሰፋው እና ሁከትንም የበለጠ ሊያቀጣጥል እንደሚችል ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የተሰኘው ዓለም አቀፍ አጥኚ ተቋም አስጠነቀቀ። በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ ከተባባሰ የኢትዮጵያ መንግስት መጪውን ምርጫ የሚያካሄድበትን ጊዜ እንዲያዘገይ ተቋሙ መክሯል።

https://p.dw.com/p/3UreL
Logo der International Crisis Group
ምስል Gemeinfrei

“መጪው ምርጫ ሁከትን ሊያቀጣጥል ይችላል”-ክራይስስ ግሩፕ

ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ይህን ያለው የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በተመለከተ ዛሬ ሰኞ ታህሳስ 6 ባወጣው ዳሰሳ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ቀውስ አምጪ ሁነቶችን በመተንተን የሚታወቀው ይሄው ተቋም በኢትዮጵያ በመጪው ግንቦት ወር ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ምርጫ በሀገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የሚታዩትን ሁከቶች የበለጠ ሊያባብስ እንደሚችል ተንብዩዋል።

በኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ከፍተኛ ተንታኝ ዊሊያም ዳቪሰን ለዶይቼ ቬለ (DW) እንደተናገሩት በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ የታዩት የፖለቲካ እና የጸጥታ ቀዉሶች እየከፉ ከመጡ “ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ አይኖርም”። “የፖለቲካ ልዩነቶችን ለመፍታት ምርጫ ሁነኛ መፍትሔ የማይሆንበት ደረጃ ላይ ሊደረስ ይችላል” የሚሉት ተንታኙ  እንዲህ አይነቱ ሁኔታ “ክፍፍሉን ይበልጥ ሊያባብሰው ይችላል” ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ። 

“ጥቅል ስጋቱ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ልንደርስ እንችላለን የሚል ነው። ከዚህ በተጨማሪም ምርጫ ለሀገሪቱ ክፍፍል ፈውስ ከመሆን ይልቅ ይበልጥ የሚያባብስበት ደረጃ ላይ ልንደርስ እንችላለን” ሲሉ ዳቪሰን ተቋማቸው ከምርጫ ጋር ተያይዞ ይከሰታሉ ብሎ የሚያስባቸውን ችግሮች ጠቁመዋል። ምርጫው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ሊያደርጉ ይችላሉ ያሏቸውን ምክንያቶችም ጠቅሰዋል።  

ባለፈው ጥቅምት ወር በኦሮሚያ የተከሰቱ ሁከቶችን እና ባለፉት 18 ወራቶች በተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶችን በምሳሌነት ያነሱት ተንታኙ እንዲህ ዓይነት ብጥብጦች ከቀጠሉ ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ አዳጋች መሆኑን ያስረዳሉ። ከዚህ ቀደም የታየው አይነት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀያቸው የመፈናቀል አካሄድ በድጋሚ ከተከሰተ ምርጫው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ዳቪሰን ገልጸዋል። 

Will Davison - Äthiopien-Experte der International Crisis Group (ICG)
ምስል CRISISGROUP/Julie David de Lossy

በምርጫው ይሳተፋሉ ተብለው የሚጠበቁ ዋነኛ ኃይሎች “በሂደቱ ላይ አንሳተፈም” የሚል ስምምነት ላይ ከደረሱ ምርጫው ሊራዘም እንደሚችልም ተንታኙ አመልክተዋል።
“የተወሰኑ ተቃዋሚዎች በምርጫ ቦርድ እና በአዲሱ የምርጫ ህግ ደስተኛ እንዳልሆኑ አይተናል። ይህ ምርጫውን ለማዘግየት ያን ያህ ጉልህ ምክንያት አልሆነም። ነገር ግን የምርጫ እቅዱን፣ የምርጫ ቦርድን ወይም ሌሎች የምርጫ ሂደቶችን በጅምላ ውድቅ የማድረግ አካሄድ ካለ ምርጫውን ሁሉን ባካተተ ስምምነት ለማዘግየት እንደ አንድ ምክንያት ሊወሰድ ይችላል” ብለዋል ዳቪሰን ። 

ዛሬ ለንባብ የበቃው የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ዳሰሳ በኢትዮጵያ አደጋን ያዘሉ አራት አሳሳቢ የፖለቲካ ጉዳዮችን ዘርዝሯል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በተወከሉበት ኦሮሚያ ክልል ሊከሰት የሚችል የፖለቲካ ችግርን በቀዳሚነት አንስቷል። በኦሮሞ እና አማራ መሪዎች እንደዚሁም በአማራ እና ትግራይ ፖለቲከኞች መካከል ሊኖር የሚችለው ክፍፍል በተከታይነት ተቀምጧል። በትግራይ ክልል አመራሮች እና በፌደራል መንግስት ባለስልጣናት መካከል ሊከሰት የሚችለው አለመግባባት አደጋ የደቀኑ ጉዳዮችበሚለው ዝርዝር ውስጥ ተካትቷል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና አጋሮቻቸው በፖለቲካ አመራሮች መካከል የሚደረግን ውይይት ይበልጥ እንዲያበረታቱ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ በዛሬው መግለጫው አሳስቧል። ማሻሻያዎችንም በጥንቃቄ እንዲያካሄዱ ተቋሙ መክሯል። በኢትዮጵያ ለሚታዩ አሳሳቢ ሁኔታዎች ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ይበልጥ ትኩረት መስጠት አለበት ያለው ተቋሙ ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች ህዝብን ከሚያነሳሱ ንግግሮች እንዲታቀቡ ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ጥሪ ያቀርብ ዘንድም ጠይቋል።

ተስፋለም ወልደየስ 

ነጋሽ መሐመድ