ወጣት መዓዛ ግደይ፤ ታዋቂዋ ተፅዕኖ ፈጣሪና የማኅበረሰብ አንቂ
ሐሙስ፣ ግንቦት 20 2018
መዓዛ ግደይ፤ ታዋቂዋ ተፅኖ ፈጣሪና የማኅበረሰብ አንቂ
ትዉልድዋ በትግራይ፤ እድገትዋ ደግሞ ትግራይን ጨምሮ አዲስ አበባ እና በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንደሆነ ትናገራለች። ኢትዮጵያን በዚህ አጋጣሚ በማወቅዋም በተለይ በሴቶች መብት ላይ እንዲሁ በተለያዩ አካቢዎች በመስራት ለሴቶች ግንዛቤ፤ ብሎም መብታቸዉን እንዲረጋገጥ ለዓመታት ሰርታለች። ትጋዋይት ነኝ ስትል የምትናገረዉ ወጣትዋ መዓዛ ግደይ የትግራይ ጦርነት ከመቀስቀሱ ጥቂት ቀደም ብሎ በዩናይትድ ስቴትስ የከፍተኛ ትምህርት እድልን አግኝታ በዝያዉ በአሜሪካ መኖር ከጀመረች፤ ዓመታት ተቆጥረዋል። የመጀመርያ ማስትሪት ዲግሪዋን በዓለም አቀፍ ግንኙነት፤ ከአንድ የአሜሪካ ዩንቨርስቲ ተቀብላለች፤ ባለፈዉ ሳምንት ደግሞ ከለንድን school of hygiene & tropical medicine ሁለተኛ ማስትሬት ዲግሪዋን ተቀብላለች።
በትግራይ ክልል ጦርነት የተቀሰቀሰዉ በዩናይትድ ስቴትስ ትምህርት ላይ ሳለች እንደነበር የምትናገረዉ ወጣት መዓዛ ግደይ፤ የሰዉ መብት እንደሚያስጨንቀዉ፤ ለዲሞክራሲ ትልቅ ክብር እንዳለዉ ሰዉ፤ ጊዜ እና እድሜዋን ተጠቅማ የህዝቧን ስቃይ ለመቀነስ ፤ መረጃዎችን በማሰባሰብ ትሰራ እንደነበር ተናግራለች።
ትግራይ ላይ ጦርነት ሲጀመር፤ ጦርነቱ ሰዎች ላይ ብቻ ያነጣጠረ አልነበረም፤ ጦርነቱ ሰዎች ብቻ የተገደሉበት አልነበረም፤ ስትል በቁጭት የምትናገረዉ ወጣት መዓዛ፤ የትግራይ ህዝብ ከሠላሳ ዓመት በላይ ጥሮ ግሮ ያፈራዉ ሐብትም ወድሞበታል ስትል ገልፃለች። በትግራይ በነበረዉ ጦርነቱ በተለይ የህክምና ተቋማት ወድመዋል። እናቶች በረሃ ላይ ነዉ የሚወልዱት፤ እናቶች አስፋልት ኮሪደር ላይ ነዉ የሚወልዱት፤ እናቶች በአሁኑ ወቅት ህይወት እየሰጡ፤ ህይወት እያጡ ነዉ። ምክንያቱም ሆስፒታሎች እንዳለ ወድመዋል። ስለዚህ ሌላ ነገር እንኳ ማድረግ ባልችል፤ በተቻለ እቅሜ እናቶች ኮሪደር ላይ እንዳይወልዱ፤ በጦርነቱ ወቅት የወደሙት የህክምና ተቋማት ተመልሰዉ እንዲያገግሙ፤ „Harambee Collective” የሚባል ድርጅት አቋቁማ እናቶች የተሟላ የጤና ተቋም እንዲኖራቸዉ እርዳታዋን እያደረገች እንደሆን ተናግራለች።
መዓዛ ግደይ በትግራይ ክልል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ለፍትህ በመጮዃ፤ በትግራይ ክልል ጦርነት እንዲቆም በመታገልዋ በተለይ በትግራይ ማኅበረሰብ ዘንድ ታዋቂ ናት። በትግራይ ክልል ጉዳይ ጠንካራ የሚባል የማኅበረሰብ አንቂ ፤ወይም አክቲቪስት መሆንዋን ብዙዎች ይናገራሉ። እንደዉ ያንን የጦርነት ወቅት እና ጦርነቱ እንዲቆም፤ ሴቶች እንዳይደፈሩ ንብረት እንዳይወድም ፤ ለፍትህ መታገልዋን ታስታዉሰዉ ይሆን?
«በደንብ አስታዉሰዋለሁ። ህይወቴን አስቤዉ በማላዉቀዉ መልኩ የቀየረዉ ጦርነት ስለነበር ከአዕምሮዬ አይጠፋም፤ በደንብ አስታዉሰዋለሁ። ከዝያ በተጨማሪ ያኔ የጀመርነዉን ሥራ ዛሬም በቀጣይነት እየሰራን በመሆኑ፤ ማንነታችን ቀጥሏል፤ በጣም የሚያሳዝን ነዉ፤ ስለዚህ በጣም ነዉ የማስታዉሰዉ።»
በዝያን ወቅት በትግራይ ክልል ጦርነት፤ የሴቶች መደፈር ብሎም በትግራይ ይታይ የነበረዉ ግፍ እንዲቆም ንቅናቂ ነበር ይመስለኛል፤ ምን አይነት ንቅናቄ ነበር አሁንስ የቀጠላችሁት ምንድን ነዉ?
«በመጀመርያ ትግራይ ላይ ጦርነቱ ሲታወጅ ፤ ሰላም የሚፈልግ ኃይል ወደ ድርድር ጠረቤዛ መጥቶ እንዲነጋገር፤ በማሰብ እና ጦርነቱ እንደጀመረ ሥራችን ጀመርን። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ ገብቶ የተቀሰቀሰዉ ጦርነት የባሰ ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ነበር ጥሪ ስናደርግ የነበረዉ። . . . »
በትግራይ ክልላዊ አስተዳደር እና በምርጫ ቦርድ እዉቅናዉን ባጣዉ በህወሓት መካከል ከፍተኛ አለመግባባቶች እንዳሉ፤ ከባለፉት ጥቂት ሳምንታት እና ወራቶች ጀምሮ በይፋ እየተሰማ ነዉ። በዚህ ጉዳይ የምትይን ነገር ካለ?
«በትግራይ የሚታየዉ የፖለቲከኞች ግጭት የፕሪቶርያ ስምምነት ባለመፈፀሙ የመጣ ነዉ። በሁሉም ወገን ያሉ ፖለቲከኞች ለስልጣናቸዉ እንጂ ለትግራይ ህዝብ የሚያስቡ አይደሉም። ለዉዝግቡ ዋና ምክንያት ግን የፕሪቶርያ ስምምነት ተግባራዊ አለመደረጉ ነዉ። ተጠያቂዉ ደግሞ በመጀመርያ ደረጃ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ነዉ፤ በሁለተኛ ደረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት ነዉ።»
ከቀናቶች በኋላ በኢትዮጵያ ምርጫ ይካሄዳል፤ ምርጫ 2018። ይህ ምርጫ ግን የትግራይ ክልልን ያካተተ አይደለም፤ ይህ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ነዉ። እዚህ ላይ ምን ትያለሽ ለሚለዉ ጥያቄ ወጣት መዓዛ ፤
« ትግራይን ያላካተተዉ ምርጫ የመንግሥትን እድሜ ለማራዘም የሚካሄድ ነዉ። በትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን በአብዛኛዉ የአማራ እና ኦሮምያ ክልልሎች ምርጫ አይካሄድም። በሁለቱም ክልሎች በአብዛኛዉ ዛሬም ጦርነት አለ።» ስትል መዓዛ ግደይ ተናግራለች። በሌላ በኩል በቂ የዉጭ ሚዲያ የማይዘግበዉ ጠቅላላ ምርጫ፤ ምርጫ ብለን ልንጠራዉ አንችልም፤ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት የለም። የአዲስ ስታንዳርድ ታግዷል፤ የዶቼ ቬለ ሁለት ጋዜጠኞችም ፈቃድ ተነጥቋል ስትል አክላለች። በትግራይ የጦር መሳር አይጩህ እንጂ ዛሬም ህዝቡ ስልታዊ በሆነ ሁኔታ ጦርነት ዉስጥ ነዉ ። የነዳጅ የለም፤ ለሲቪክ ሰራተኛዉ ደሞዝ የለም ፤ የህክምና መድሐኒት የለም፤ ህዝቡ የሚመገበዉ በቂ ምግብ የለዉም ስትል ተናግራለች።»
ከማኅበረሰብ አንቂና ተጽኖ ፈጣሪዋ መዓዛ ግደይ ጋር ያደረግነዉን ሙሉ ቃለ ምልልስ የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።