1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መንግሥትና ሕወሓት፤ ኢሰመኮ ስለአባገዳዎች ግድያ

ዓርብ፣ ጥር 27 2014

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሓት እየተደራደሩ ነው ስለመባሉ በእየ ፊናቸው መልስ ሰጥተዋል። ስለ ከረዩ አባገዳዎች ግድያ ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። አዲስ አበባ ለአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ ዝግጅት ሽር ጉድ እያለች ነው። የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት በእነዚህ ሦስት ጉዳዮች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል።  

https://p.dw.com/p/46UKs
Preparation of Addis Abeba for the AU Summit
ምስል Seyoum Getu/DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅንት አስተያየት

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በሕወሓት መካከል ድርድር እየተደረገ መሆኑን ሕወሓት ሲገልጥ፤ የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ ከሕወሓት ጋር ንግግር አለመኖሩን በቃል አቀባዩ በኩል ዐስታውቋል። በኦሮሚያ ክልል በከረዩ አባገዳዎች ላይ ግድያ የፈጸሙና ያስፈጸሙ የፀጥታና የአስተዳደር አባላት ላይ ተገቢው የወንጀል ምርመራ ተደርጎ ለፍትሕ እንዲቀርቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በዚሁ ሳምንት ባወጣው በመግለጫው ዐሳውቋል። አዲስ አበባ የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ 35ኛ የመሪዎች ጉባኤን ለማስተናገድ ሽር ጉድ ጀምራለች። የአፍሪቃ ኅብረት አባል ሀገራት ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት 40ኛው የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጉባኤ ረቡዕ ዕለት ሲጀምርም ከተማዪቱ ላይ ጠንከር ያለ ጥበቃ ተስተውሏል። በሦስቱ ጉዳዮች ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል። 

Äthiopien | Dr. Legesse Tulu - Kommunikationsminister
ምስል Seyoum Getu/DW

ስለ ድርድር
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)ይፋዊ ባልሆነ መልኩ እየተደራደሩ ነው የሚሉ ዘገባዎች እየተደመጡ ነው። በዚህ የድርድር ጉዳይ ላይ የፌዴራል መንግሥትም ሕወሓትም በእየ በኩላቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚንስትር ለገሰ ቱሉ መንግስታቸዉ ሰላምን ለሚያመጣ ለየትኛዉም አማራጭ በሩ ክፍት እንደሆነ በተለይ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። እስካሁን ድረስ ግን ከሕወሓት ጋር የተደረገ ንግግር አለመኖሩን አክለው ገልጠዋል። 
የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው ባለፈዉ ሳምንት መገባደጃ ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ሕወሓት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተዘዋዋሪ እየተደራደረ መሆኑን ዐስታዉቀዉ ነበር። ዶክተር ደብረ ፅዮን ተዘዋዋሪ ያሉት ድርድር «ዕመርታ እያሳየ» መሆኑንም ገልጠዋል። እየተደራደርን ነው እየተደራደርን አይደለም ለሚሉት የየቅል መግለጫዎች በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። 

«አቦ ተደራድረው ይገላገሉን፤ ሰላም ነው የምንፈልገው» ሲሉ አስተያየት የሰጡት ትእግስት ዓለሙ ናቸው በፌስቡክ አስተያየታቸው። መንግሥት ከሕወሓት ጋር የተደረገ ንግግር የለም ማለቱን በተመለከተ ደግሞ ብሩክ ዘርፌ፦ «አንች ታመጭው፤ አንች ታሮጭው አሉ» ሲሉ አስተያየት ሰንዝረዋል። «ተደራደርክ አልተደራደርክ እውነቱ ይወጣል» አስተያየቱ የሚካኤል መኮንን ነው። ሰዒድ ዳውድ፦ «ወቸው ጉድ» ሲሉ ይጀምራሉ አስተያየታቸውን። «በቃል ሳይገኙ ሁለዜ ሁለዜ ማስተባበል?» ይጠይቃሉ። «በዚህ የከፍታ ዘመን (የብልጽግና መፈክር፣ ያውም የሚያሳርር፣) አለማፈር?» ይቀጥላሉ በአስተያየታቸው። «ሰውን አመሳስሎ ተመሳስሎ ማለፍ ይቻል ይሆናል፣ ግን ህሊናን እንዴት? ነው የለም ? ለሁሉም አላህ ያውቅልናል» ሲሉም ያጠቃልላሉ። እየተደራደርን ነው፤ የለም ንግግር የሚባል የለም ለሚሉ የሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የተጣረሱ መግለጫዎችን አስመልክተው ሀበን ጋልአቡአ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ይጠይቃሉ። «የናይጄሪያው መሪ -ኦባሳንጆ መቋለ የሚመላለሰው ለሽርሽር ነው ማለት ነው?» ዳውድ ላቭ የተባሉ የፌስቡክ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ቀጣዩን ብለዋል። «የመግለጫዉ አንደምታ ሲያዩት ድርድር እንደማይቀር ነዉ። ለምሳሌ 'ሰላምን ለሚያመጣ ለየትኛዉም አማራጭ በሩ ክፍት ነዉ' እምትለዉ ዓረፍተ ነገር ታመላክታለች አለቀ» ሲሉም አስተያየታቸውን አጠቃለዋል።  

Äthiopien Konflikt in Tigray | Debretsion Gebremichael
ምስል Tiksa Negeri/REUTERS

«ብልፅግና ከሕወሓት ጋር ከመደራደሩ በፊት ከአፋርና ከአማራ ክልል ሕዝብ ጋር በጉዳዮ ላይ ቢመካከር አይሻልም የይስሙላ ድርድር ለቀጣዮ መፍትሄ የለውም።» አስተያየቱ የበሱፈቃድ ዘምና ሙሉ ነው። ቃፋን ሙሳ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ በበኩላቸው፦ «አፋር በጦርነት እየታመሰ የሚደረግ ድርድር ዜሮ ዜሮ ዜሮ መቻቻል ይሆናል» ብለዋል። 

Äthiopien l Geflüchtete Menschen in Afar Iwa
ምስል Seyoum Getu/DW

ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ ሕወሓት አፋር ክልል ውስጥ ጥቃት ሰንዝሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን መጉዳቱን ነዋሪዎች፣ የመብት ተሟጋቾች እና ፖለቲከኞች ገልጠዋል። ከሰሞኑም ብራስልስ ከተማ ውስጥ የአፋር ዲያስፖራ ማኅበረሰብ የተቃውሞ ሰልፍ አሰምተዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ችላ ያለው የአፋር ሕዝብን ያስተውል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል። «ምን የአለም ማኅበረሰብ ብቻ መንግስታችንስ?» ጥያቄው የሰንቲ ሙሉ ነው። ሰልፈኞቹ የፌዴራል መንግሥት አፋርን ችላ ብሏል ሲሉ ቅሬታ አሰምተዋል። «በአፋር ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ እና እልቂት ለምን መታፈን አለበት» ሲሉ በጥያቄ የሚንደረደሩት ቃፋርባጣ ሞውዳ የተባሉ የፌስቡክ አስተያየት ሰጪ ናቸው። «በሰሜን አፋር ክልል 250,000 ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለምንድነው የሴቶች እና የህጻናት ግድያ እየተፈጸመ አይደለም ብሎ መናገር ለምን አስፈለገ?» ይጠይቃሉ ቃፋርባጣ። «በዚህ ላይ ግልጽ ብርሃን እንፈልጋለን። ለኢትዮጵያ ሲሉ ራሳቸውን መስዋዕት በሆኑ ሰዎች ላይ እንጨት መጨመር በጣም ያማል» ሲሉ አስተያየታቸውን ቋጭተዋል። አስተያየቱ ለዶክተር ለገሰ ቱሉ ነው። አፋር ክልል ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ነዋሪ በጦርነቱ ከአካባቢው መፈናቀሉን ዶይቸ ቬለ ከሰሞኑ ዘግቧል።

በኦሮሚያ ክልል በከረዩ አባገዳዎች ላይ ግድያ የፈጸሙና ያስፈጸሙ ያላቸው የፀጥታና የአስተዳደር አባላት ላይ ተገቢው የወንጀል ምርመራ ተደርጎ ለፍትሕ እንዲቀርቡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)ጠይቋል። ኮሚሽኑ ለሟቾች ቤተሰቦች እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎችም ተገቢው ካሳ እንዲሰጥ ሲል አሳስቧል። «ኦ ዛሬ ተቋሙ በጣም ጠከር ያለና ጥንካሬውን በርታ የሚያስብል መረጃ ሪፓርት ሰጥቷል።» የተፈሪ ኃይሉ የፌስቡክ አስተያየት ነው። ወንድወሰን ዘውዱ በበኩላቸው፦ «እኛማ ሸኔ ገደላቸው ብሎ መንግስት ቅጥፈቱን ሲግተን አምነነው ነበር» ሲሉ ጽፈዋል።  ማንኛውንም አይነት ግድያም ተቃውመዋል። «በወለጋ በየቀኑ የሚጨፈጨፈው አማራስ?» ጥያቄው የዘውዴ ሙሴ ነው። «ልብ ይሰብራል። ኢትዮጵያ ውስጥ ለንጹሃን ዜጎች ፍትሕ እንጠይቃለን» ከራውዳ ሞሐመድ አስተያየት የተወሰደ ነው። 

Symbolfoto Justitia
ምስል picture alliance

ከዚህ ቀደም የመንግሥት መገናኛ አውታሮች የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትን በመጥቀስ ግድያውን የፈጸሙት የኦነግ/ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው በማለት ዘግበው ነበር። ይህንኑ በተመለከተ ቂልጡ ዳጋጋ በትዊተር ጽሑፋቸው፤ «የመንግሥት መገናኛ አውታሮች ግድያውን የፈጸመው ኦነግ ሸኔ ነው ብለው ነበር» ብለዋል።  «ማንም ከሕግ በላይ አይደለም! የንጹሀንን ሕይወት የቀጠፉ እና በዚህ እኩይ ተግባር የተሳተፉ በሙሉ ፍትህ ፊት መቅረብ አለባቸው።» አስተያየቱ የመሳይነህ እሸቱ ነው። ወደ ቀጣዩ ርእስ ጉዳይ እንሸጋገር። ለአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ አዲስ አበባ የምታደርገውን ዝግጅት ይመለከታል። አጠር ያለ ዳሰሳ አድርገናል።  

የአፍሪቃ ኅብረት ስብሰባ ዝግጅት በአዲስ አበባ
የአፍሪቃ ኅብረት መቀመጫ የኾነችው አዲስ አበባ ከተማ 40ኛውን የኅብረቱ የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጉባኤ ረቡዕ እና ሐሙስ አስተናግዳለች። የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ ደግሞ 35ኛውን የመሪዎች ጉባኤን ለማስተናገድ እየተሰናዳች ነው። ከተማዪቱ ዋና ዋና ጎዳናዎቿን በአባል አገራቱ ሰንደቅዓlማ ከማስጌጧ ባሻገር የፀጥታ ኃይላት ጠንካራ ጥበቃ እያደረጉ መኾናቸውም ተገልጧል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ስብሰባው «በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ የግብረ-ኃይል» ያለውን ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን ይፋ አድርጓል። «በርቱልን» የዮሴፍ ጌታመሳይ አጭር የትዊተር መልእክት ነው። «ለአፍሪቃ ምን ይጠቅማታል? ምንስ ጠቀመ?» ሲሉ በፌስቡክ የጠየቁት ደግሞ ሰለሞን መኮንን ናቸው። 

Preparation of Addis Abeba for the AU Summit
ምስል Seyoum Getu/DW

«ደሞ ልታጉላሉን ነው። መተው ለሚያንቀላፋት ነገር» ይላሉ አሚ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጽሑፍ ላይ በሰጡት ምላሽ። ደሞዝ ወርቅነህ በትዊተር ጽሑፋቸው፦ «ያለአግባብ ህዝባችንን አታንገላቱት» ብለዋል። «ጸጥታ እያስከበራችሁ ለሕዝባችን፣ ፍቅር፣ ፈገግታና ትህትና ዐሳዩ፣ ምክንያቱም ህዝባችን ደሞዝ የሚክፍላችሁ፣ የሥራ እድል የፈጠረላችሁ ስለሆነ» የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። «ባይጀመርስ ምን ያረግልናል ደግሞ ለአምባገነኖች ሆዳሞች» ያሉት ደግሞ ኤደን ብዙ ናቸው በፌስቡክ ጽሑፋቸው። ኤፍሬም ካሣ ስብሰባው አዲስ አበባ ውስጥ ስለመደረጉ ባቀረቡት አጭር ጽሑፋቸው፦ «ሀገሬ ኢትዮጵያ ሰላምሽ ይብዛ» ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።  እኛም በዚህ የዛሬውን የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ቅኝት መሰናዶዋችን እናጠናቅቃለን።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ