1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መንግሥት በሃገሪቱ ያለዉን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያስቆም ተጠየቀ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 24 2010

የኢትዮጵያ መንግሥት በሶማሌ እና በኦሮሚያ መስተዳድሮች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚካሔደዉን ግጭት እና የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲያስቆም የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ዛሬ ይፋ ባደረገዉ መግለጫ አሳሰበ።

https://p.dw.com/p/32P6g
Äthiopien Flüchtlinge vor ethnischer Gewalt
ምስል DW/J. Jeffrey

በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች

ጉባኤዉ እንዳስታወቀዉ በሁለቱ ድንበር በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።  ከብሔር-ተኮር ግጭቶችና ጥቃቶች መካከል በአማራና በኦሮሞ፣ በኦሮሞና በሶማሌ፣ በኦሮሞና በጌዴኦ፣ በወላይታና በጋሞ፣ በወላይታና በሲዳማ፣ በአኙዋክና በኑዌር፣ በሱርማና በዲዚ ተወላጆች መካከል የተከሰቱት ግጭቶች ለአብነት የሚጠቀሱ መሆናቸዉን ጉባዔዉ አስታዉቋል። ዛሬ « ሰመጉ » ይፋ ያደረገዉ መግለጫ የሚያሳየዉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከጥር 2009 እስከ ጥር 2010 ዓ,ም ድረስ በኦሮምያና በኢትዮ ሶማሌ አጎራባች ላይ በተከሰቱ ግጭቶች የደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መሆንም ገልፆአል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የሰመጉ»  ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም አባተ፤ የተፈፀሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለማጣራት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን መረጃ ጠይቀን የኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መረጃን ሊሰጠን አልቻለም ሲሉ ተናግረዋል። አቶ ቢኒያም አባተ መግለጫዉ በብዙ መቶዎች መገደላቸዉን ፤ የሰዉነት ጉዳት፤ አካል መጉደል፤ እንዲሁም ከአካባቢያቸዉ የተፈናቀሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚዘረዝር መሆኑን በመጥቀስ በቀጣይ መረጃዉን ለመንግሥት ማሳወቅ ነዉ ስራችን ሲሉ ተናግረዋል። ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በመባል ይታወቅ የነበረዉና በአሁኑ ወቅት የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) የሚል መጠርያን የያዘዉ ተቋም መስከረም ወር 1984 ዓ.ም የተቋቋመ የመጀመሪያው መንግሥታዊ ያልሆነ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም መሆኑ ይታወቃል።

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ