1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕገ-መንግሥቱ ያለ ተሟጋች ይተረጎማል?

ሰኞ፣ ግንቦት 3 2012

በጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ዕድሜ ላይ ለመወሰን ሶስት የሕገ-መንግሥቱ አንቀፆች የመተርጎም ኃላፊነት የተጣለበት የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ባለሙያዎች አስተያየት እንዲሰጡ በመጋበዝ ሥራ ጀምሯል። ጉባኤው ያለ ተሟጋች ሕገ-መንግሥት ተርጉሞ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት "ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሐሳብ" ማቅረብ ይችላል?

https://p.dw.com/p/3c2tq
Meaza Ashenafi
ምስል picture-alliance/Geisler-Fotopress/C. Niehaus

የኢትዮጵያ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ቅርቃር

የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሶስት የሕገ-መንግሥቱ አንቀፆች እንዲተረጎሙ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበ ጥያቄ መሠረት "ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሐሳብ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ" ባለሙያዎች አስተያየት እንዲሰጡ ጋብዟል። በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷ መዓዛ አሸናፊ የሚመራው አጣሪ ጉባኤ የሚያስተላልፈው ውሳኔ በጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና መንግሥታቸው የወደፊት የሥልጣን ጊዜ ላይ ኹነኛ ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው።  በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒም የሚመሩት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። ምክር ቤቱ ባለፈው ሳምንት ሶስት አንቀፆች እንዲተረጎሙ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላለፈውን ውሳኔ መቼ ወደ ሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ እንደመራ የታወቀ ነገር የለም።

የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ "ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሐሳብ" ላይ ተመርኩዞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚያሳልፈው ውሳኔ ሁሉንም የፖለቲካ ልሒቃን የማስማማቱ ጉዳይ አጠራጣሪ ይመስላል። በኖርዌይ በርገን ዩኒቨርሲቲ በሕግ የፒኤች ዲ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት ሙሉ በየነ «የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ- መንግሥቱ ተርጓሚ ሆኖ መቅረቡ በብዙ ጸሀፊያን፤ በብዙ ተንታኞች ተቃውሞ ሲቀርብበት ነበረ። ይኸም አባላቱ የሚመረጡበትን መንገድ ታሳቢ ያደረገ ነው። በተለይ ደግሞ ከ1997 ዓ.ም. በኋላ የክልል ፕሬዝዳንቶች በዋንኛነት በቢሯቸው፤ የክልል ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤዎች አባላት ናቸው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የሚባሉት በየክልሉ ተመርጠው የሚመጡ ፖለቲከኞች ናቸው። እንደዚህ አይነት ተቋም የሚሰጠው ውሳኔ በብዙ ሰው ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል ተብሎ አይገመትም" ሲሉ ይናገራሉ።

አቶ ሙሉ "ሕገ-መንግሥቱን መተርጎም አንችልም ሌላ የፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲሰጠው የሚል ውሳኔ ቢሰጥ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ከህወሓት ስለሆኑ ነው ሊባል ይችላል» ሲሉ የምክር ቤቱ ውሳኔ ሊገጥመው የሚችለውን ጣጣ ይገልፃሉ። ሶስቱን አንቀፆች ተርጉሞ የብልፅግና ፓርቲ በሥልጣን ላይ እንዲቆይ የሚፈቅድ ውሳኔ ቢያስተላልፍ በአንፃሩ አቶ ሙሉ እንደሚሉት ከምክር ቤቱ አባላት አብዛኞቹ የገዢው ፓርቲ አባል በመሆናቸው ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅ ድምዳሜ ላይ ደረሱ የሚል ሌላ ወቀሳ ይሰነዘርባቸዋል።  

የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ለወቅታዊው ቅርቃር ካቀረባቸው አራት አማራጮች መካከል ሕገ-መንግሥቱ እንዲተረጎም የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በ25 ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ጸድቆ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲላክ የተወሰነው ባለፈው ማክሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ነበር። ንትርክ እና መወራረፍ በበረታበት የማክሰኞው የምክር ቤት ውሎ የህወሐት ሥራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አዲስዓለም ባሌማ «ሕገ-መንግሥቱ ላይ፤ እዚህም የውሳኔ ሐሳቡ ላይ የተቀመጡት አንቀፆች ምንም አይነት የትርጉም ክፍተት የለባቸውም» ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

Logos TOLF  EPRDF
ኢሕአዴግ ፈርሶ ብልጽግና ሲመሰረት ያልተዋሐደው ህወሓት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ውሳኔ በብርቱ ተቃውሟል

ላለፉት 29 አመታት ገደማ ሥልጣን ላይ ቆይቶ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ምርጫ ማካሔድ ባለመቻሉ ቅርቃር ውስጥ የገባው መንግሥት ባቀረባቸው አራት አማራጮች ተቃውሞ የቀረበበት ግን ከህወሓት አባላት ብቻ አይደለም። ባለፉት ሁለት አመታት በአንፃራዊነት መጠናከር የታየበት እና ከውጪ አገራት ተመልሶ በኢትዮጵያ የከተመው የተቃውሞ ጎራ ብርቱ ትችት አቅርቧል። የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ትችት እና መፍትሔ ብለው የሚያቀርቧቸው አማራጮች ግን የዛኑ ያክል አከራካሪ እና አወዛጋቢ ሆነው ይታያሉ።

ትርጉም የተጠየቀባቸው አንቀፆች የትኞቹ ናቸው?

የሕግ፣ ፍትኅ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለትርጓሜ ከመረጣቸው የመጀመሪያው አንቀጽ 54 ንዑስ አንቀፅ አንድ ነው። ይኸው የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ «የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ ሁሉ አቀፍ፣ ነጻ ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምጽ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ» ሲል ይደነግጋል።

ሊተረጎሙ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተላኩ መካከል «የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፤ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል» የሚለው አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀፅ ሶስት ይገኝበታል።

ሶስተኛው እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚመለከተው አንቀፅ 93 በውስጡ ስድስት ንዑስ አንቀፆች ይዟል። ይኸኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለምን፣ እንዴት እና መቼ የሚሉ ጉዳዮችን በዝርዝር ይደነግጋል።

ማን ይተረጉማል?

በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው 153 አባላት ያሉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። በቪየና ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ ትምህርታቸውን በመከታተል የሚገኙት የቀድሞው የሕግ ባለሙያ እና መምህር ሞገስ ዘውዱ እነዚህን ሶስት አንቀፆች በመተርጎም ረገድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባኤ የቤት ሥራ እንደሚሰጥ ያስረዳሉ።

አቶ ሞገስ «ባለሙያዎች የሚበዙበት አጣሪ ጉባኤ ከሕግ አንፃር አይቶ ይኸ ለትርጉም የተጋለጠ ነው ወይስ አይደለም? የሚል ውሳኔ ወስኖ አስተያየቱን አክሎበት ፖለቲካዊ ለሆነው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስተላልፋል። አሁን ችግር የሚሆነው የሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባኤው ትርጉም አያስፈልገውም ቢል ምን ይሆናል? የሚለው ነው» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አስራ አንድ አባላት አሉት። በተቋሙ ድረ-ገፅ የአጣሪ ጉባኤው ዘጠኝ አባላት ስም እና ፎቶግራፍ ይገኛል። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ሲይዙ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት መዓዛ አሸናፊ በሰብሳቢነት ይመሩታል።

የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሰለሞን አረዳ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር መለስ ዜናዊ ልዩ አማካሪ የነበሩት ፋሲል ናሆም (ዶ/ር) እና የቀድሞው ፍትኅ ሚኒስቴር ምኒስትር ብርሀን ኃይሉ የአጣሪ ጉባኤው አባላት ናቸው። ሚሊዮን አሰፋ፣ ክፍለ ጺዮን ማሞ፣ ቀንዓ ያደታ (ዶ/ር)፣ መለስ ዓለሙ፣ ወይዘሮ ደስታ ገብሩ የአጣሪ ጉባኤው አባላት እንደሆኑ ይኸው የተቋሙ ድረ-ገጽ ይጠቁማል።

Premierminister Dr. Abiy Ahmed
ምስል PM Abiy Ahmed Ali Office

የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ለትርጉም የተላኩ ሶስት አንቀፆችን ለመመርመር ሥራ ቢጀምርም አቶ ሙሉ በየነ እንደሚሉት ግን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ብቻውን ሶስቱ አንቀፆች እንዲተረጉሙ የሚያበቃ አይደለም።

«አዋጅ 798 አንቀፅ 3 ንዑስ ቁጥር አንድ እና ሁለት [እንደሚሉት] አከራካሪ ለመሆን ውሳኔ መሆን አለበት። አሁን ግን የተወሰነ ውሳኔ የለም። ለምሳሌ መንግሥት ይቀጥላል የሚል ይፋ ውሳኔ የለም። እንደዚያ አይነት ውሳኔዎች ቢኖሩ ነው ይኸ ከሕገ-መንግሥቱ ይቃረናል ወይንስ አይቃረንም? የሚቃረን ከሆነ ምንድነው መሆን ያለበት የሚል ትንታኔ የሚሰጥበት። ራሱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የአሰራር መመሪያ አለው። ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚያመሩ አቤቱታዎች ማሟላት አለባቸው ከሚላቸው ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ ያለው ሕግ ወይም ውሳኔ ለምን ሕገ-መንግሥቱን እንደሚቃረን፤ የትኞቹን የሕገ-መንግሥት አንቀፆች እንደሚቃረን ማሳየት ማስቻል አለበት ነው የሚለው። እንጂ እንደዚህ አይነት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው እና ምን ይሁን የሚል አስተያየት እንዲሰጥ አይደለም የሕገ-መንግሥት ትርጓሜ ተብሎ የተቀመጠው» ሲሉ አቶ ሙሉ ይሞግታሉ።  

በዚህ ሐሳብ በርካታ የሕግ ባለሙያዎች ይስማማሉ። ከእነዚህ መካከል የሕገ-መንግሥታዊ ዴሞክራሲ እና የአስተዳደር ጉዳዮች አማካሪ እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አደም ካሴ (ዶ/ር) አንዱ ናቸው። አደም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሶስቱን አንቀፆች ለትርጓሜ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሚመራ ይልቅ መንግሥት የራሱን ውሳኔ አሳልፎ መገዳደር የሚሹ ለክርክር ባቀረቡት ነበር የሚል ዕምነት አላቸው።

አደም ካሴ «ጥያቄው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለበት ኹኔታ የፓርላማውን ዕድሜ፤ የመንግሥቱን ዕድሜ ማራዘም ይቻላል አይቻልም ነው። መንግሥት በራሱ ʽአዎ ይቻላልʼ ብሎ መወሰን ይችል ነበር። ʽአይ አይቻልምʼ የሚል ሰው ደግሞ ሕገ መንግሥቱን ተከትሎ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ወይም ደግሞ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ኮሚቴ መጠየቅ ይችል ነበር» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

Äthiopien EPRDF
ምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

የቀድሞው ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ በቆየባቸው ረዥም አመታት ምርጫዎች ቢካሔዱም «አንድ ፓርቲ ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ የያዘ፤ ጠቅልሎ መያዝ ብቻ ሳይሆን ፓርቲው ውስጥ በማዕከላዊነት መርኅ የሚመራ ውሳኔ የሚወሰንበት እና የሚቀበል ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ብትለውም፤ የሕገ-መንግሥት ተርጓሚ ብትለውም የፓርቲውን መስመር ተከትሎ የሚሔድ ነበረ። እነዚህ አካላት የራሳቸው ነፃ የሆነ አቅም፤ ነፃ የሆነ ልምድ የላቸውም» ይላሉ ዶክተር አደም።  ተንታኙ የኢትዮጵያ ተቋማት «ለዚህ ትርጓሜም አግባብ ያለው መልስ ላይሰጡ ይችላሉ፤ እንዲያውም በእኔ እምነት መንግሥት ወስኖ የማይፈልግ ሰው ʽአይሆንም፤ ይኸ ትክክል አይደለምʼ ቢል ይሻል ነበር። ቢያንስ መንግሥት ለውሳኔው ኃላፊነት ይወስድ ነበር። አሁን ግን እነዚህ አካላት መንግሥት የሚፈልገውን ውሳኔ ከሰጡት ኃላፊነት ሳይወስድ የሚፈልገውን ያገኛል» ብለዋል።   

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሚያዝያ 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ብልፅግና ፓርቲ «ሕጋዊ በሆነ አግባብ የኮቪድ19 ሥጋት እስኪወገድ እና ቀጣይ ምርጫ እስኪካሔድ ሀገር የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት ፓርቲ ነው» ሲሉ ተናግረዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አንዳች ውሳኔ ሳያሳልፍ ጠቅላይ ምኒስትሩ ይኸን ማለታቸው ለብርቱ ወቀሳ ዳርጓቸዋል።

ቪየና ዩኒቨርሲቲ የሚገኙት አቶ ሞገስ የሕገ-መንግሥቱ ሶስት አንቀፆች የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ከተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አኳያ ሊተረጎሙ ይችላሉ ሲሉ ይናገራሉ። አቶ ሞገስ እንደሚሉት «የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል የታወጀው አስቸኳይ አዋጅ በምክር ቤቱ የሥራ ዕድሜ ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል?» የሚለው ጉዳይ ብቻ ሊተኮርበት ይገባል።

«የኮሮና ወረርሽኝ የጋረጠው አደጋ በምክር ቤቱ ዕድሜ ላይ ምን ተፅዕኖ ይኖረዋል? ለምሳሌ አምስት አመት የተባለው በሰላም ጊዜ ነው። አደጋ ሲያጋጥምስ? እሱ ሕገ-መንግሥቱ ውስጥ አልተቀመጠም። ስለዚህ ይኸ ሊተረጎም ይችላል» ያሉት አቶ ሞገስ መንግሥት ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች መነጋገር እንደሚገባው በአፅንዖት ያሳስባሉ። በዚህም ውሳኔው የፖለቲካ ድጋፍ እና ቅቡልነት ያገኛል።

ከዚህ ቀደም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለያዛቸው የክርክር ጉዳዮች መፍትሔ ለማበጀት ረዘም ያለ ጊዜ ሲወስድበት ታይቷል። አንድ መቶ ሀምሳ ሶስት አባላት ያሉት ምክር ቤቱ የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ሥልጣን በአምስት ወራት ውስጥ ከማብቃቱ በፊት ለጉዳዩ ዕልባት የማበጀቱ ጉዳይ አጠራጣሪ እንደሚሆን አቶ ሙሉ ያጠይቃሉ።

«እንኳን እንዲህ ውስብስብ ያለ ጉዳይ ይቅርና በሁለት ሰዎች መካከል የመሬት አጠቃቀም ክርክር ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ሲደርስ አንድ አመት፤ ሁለት አመት ከዚያም በላይ ነው የሚፈጀው» የሚሉት አቶ ሙሉ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የሚያማክሩበት ዕድል ስለሚኖር ሒደቱ ሊራዘም እንደሚችል ተናግረዋል። «በአጭሩ ለመስከረም የሆነ ነገር እንዲባል ተብሎ ውሳኔ ቢሰጥ እንኳን ከሁኔታው ውስብስብነት የተነሳ ተዓማኒነቱ» ችግር ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።  

አቶ ሞገስ ግን በሕገ-መንግሥቱ አንቀፆች ትርጉም ተከራካሪ ወገኖች ባለመኖራቸው ሒደቱ ሊፋጠን ይችላል የሚል ዕምነት አላቸው። «አጨቃጫቂነቱ እንዳለ ሆኖ ሌላ ወገን ስለሌለ፤ አመልካች ብቻ ስለሆነ ያለው ፈጥኖ ውሳኔ መስጠት ይቀላል» የሚሉት አቶ ሞገስ ኢትዮጵያ በፈታኝ ወቅት የምትገኝ መሆኗ ለውሳኔው መፍጠን ተጨማሪ ገፊ ምክንያት እንደሚሆን ገልጸዋል። «መስከረም 30 ሁለቱም ምክር ቤቶች የሥራ ጊዜያቸው ስለሚያበቃ የፓርላማን ዕድሜ፤ በአጠቃላይ ደግሞ የምክር ቤቶቹን ዕድሜ ሲተረጉሙ የራሳቸውንም ጥቅም እያነበቡ ስለሆነ የሚተረጉሙት ከመስከረም 30 በፊት አስገዳጅ ውሳኔ» እንደሚሰጡ እምነታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሒቃን በየፊናቸው ይበጃሉ ያሏቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች ቢደረድሩም እስካሁን መስማማት ቀርቶ መቀራረብ አልታየባቸውም። «መነጋገር ያስፈልገናል። መቼ የሚለውን ሁሉም ተመካክረው መሠረታዊ የሚባሉ መርሆዎች ላይ መስማማት ይቻላል። ለምሳሌ መነጋገሪያ ነጥባችን እንዴት ነው የሚሆነው? ምን አይነት አካል አቋቁመን ነው መነጋገሪያዎችን የሚወስነው? ሕገ-መንግሥቱ መቀየር ካለበት በምን መልኩ ነው? ውሳኔዎች እንዴት ይወሰናሉ?» በሚሉ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ኃይሎች ተስማምተው ምርጫ ቢያካሒዱ የተሻለ እንደሚሆን ዶክተር አደም ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ