1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕወሓት፣ በትግራይ ክልል ምርጫ ሊያደርግ ወሰነ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 27 2012

ፓርቲው በትግራይ ክልላዊ ምርጫ እንዲካሄድና ለዚህም ዝግጅት እንዲጀመር መወሰኑን አስታውቋል። ህወሓት በመግለጫ እንዳስታወቀው ዘንድሮ ሊካሄድ ይገባው የነበረ ሀገራዊ ምርጫ በወቅቱ ካልተካሄደ የከፋ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ገልጿል

https://p.dw.com/p/3bogG
Äthiopien nach TPLF Meeting
ምስል DW/M. Haileselassie

ህወሓት በትግራይ ክልላዊ ምርጫ እንዲደረግ ውሳኔ አስተላለፈ።

ህወሓት በትግራይ ክልላዊ ምርጫ እንዲደረግ ውሳኔ አስተላለፈ።  «ሀገር ለመታደግ የሚያስችል መድረክ» እንዲመቻችም  ጠየቀ። የትግራይ ክልል ገዥ ፓርቲ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሚያዝያ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት አካሄድኩት ካለው ስብሰባ በኋላ ባወጣው መግለጫ እንደጠቆመው፣ ፓርቲው በትግራይ ክልላዊ ምርጫ እንዲካሄድና ለዚህም ዝግጅት እንዲጀመር መወሰኑን ይዘረዝራል። ህወሓት በመግለጫ እንዳስታወቀው ዘንድሮ ሊካሄድ ይገባው የነበረ ሀገራዊ ምርጫ በወቅቱ ካልተካሄደ የከፋ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል በመጥቀስ «ህወሓት እንዲህ ዓይነቱ ክስተት ሊፈጥረው የሚችለውን ትርምስ ለማስወገድ በሚደረጉ ሀገራዊ ጥረቶች ውስጥ ድርሻውን በቀናነት ለመጫወት ዝግጁ ቢሆንም የትግራይ ህዝብ በመስዋእትነቱ በተከለው ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የተረጋገጠለትን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንደዋዛ እንዲጣልበት አይፈቅድም፡፡ ለዚህም ሲባል ከትግራይ ህዝብና ለትግራይ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሙሉ እውቅና ከሚሰጡ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመሆን ክልላዊ ምርጫን ጨምሮ ይህንኑ የህዝባችንን መብት ከትርምስ ለመታደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን በክልል ደረጃ ለማድረግ ዝግጅት እንዲደረግ» መወሰኑ አስታውቋል፡፡ከዚህ ውጭ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አቋሙን የገለፀው ህወሓት፣ ሀገራዊው ምርጫ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው ማእቀፍ ውስጥ በመሆን ለመከወን በሚቻልበት መንገድ ላይ ሁሉም ፓርቲዎች የሚሳተፉበት መድረክ እንዲመቻች ጠይቋል፡፡የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት «በጠራራ ፀሐይ» እየተጣሰ ነው የሚለው ህወሓት የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮችና ፌደሬሽን ምክር ቤቶች ይኽ ተግባር እንዲቆም ጥረት እንዲያደርጉም ጠይቋል። 

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሰ