ልጆቻቸው ትግራይ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ወላጆች ድምጽ
ዓርብ፣ ሐምሌ 16 2013ማስታወቂያ
ልጆቻቸው ትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ በርከት ያሉ ወላጆች እና ቤተሰቦች ዛሬ ጠዋት በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት ቢሮ በር ላይ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። ወላጆቹ «ልጆቻችን እስክሪብቶ እና ደብተር ብቻ ይዘው ለመማር ነው የሄዱት፣ አስመልሱልን» የሚሉ ጥያቄዎችን በለቅሶ እና እንባ በታጀበ ድምፅ አሰምተዋል። ጥያቄ አቅራቢዎቹ ትግራይ ውስጥ የሚገኙት ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቹን ለመመለስ የነዳጅ ፍጆታ እንደሌላቸው መናገራቸውን የተባበሩት መንግሥታት ተነግሮናል ብለዋል። ከዚህ መነሻ የነዳጅ ፍጆታውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለመሸፈን ተስማምቶ ሚኒስቴሩ በተባበሩት መንግሥታት በኩል ሁለት ቦቴ ነዳጅ ማቅረቡን እና 63 አውቶቡሶች ማዘጋጀቱን እንደገለፀላቸው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል። ሆኖም ከእሁድ እስከ ማክሰኞ ይመለሳሉ የተባሉት ተማሪዎች መውጣት ስላልቻሉ ለጥያቄ ዛሬ መውጣታቸውንም ወላጆች ተናግረዋል። በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው ሁሉ መረጃ ለማግኘት ያደረግኩት ተደጋጋሚ ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ