1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ልውጥ የኮሮና ተዋህሲያንና ባህርያቸው

ሐሙስ፣ መጋቢት 30 2013

የኮሮና ተዋህሲ ራሱን እየቀየረ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት በቻይና ከተገኘው ከመጀመሪያው ተዋህሲ ጋር ተመሳሳይ አይደለም።ለዘርፉ ሊቃውንት የኮሮና ተዋህሲ ራሱን መለወጡ የሚጠበቅ ነው።ነገር ግን የተዋህሲያኑ የመተላለፍ ፍጥነት ከፈተኛ መሆኑና በክትባቶች ውጤታማነት ላይ ሊያሳድሩ የሚችሉት ተጽእኖ አሳሳቢ ነው።

https://p.dw.com/p/3rh5C
Illustration eine Coronavirus-Mutation
ምስል DesignIt/Zoonar/picture alliance

ልወጥ የኮሮና ተዋሲያንና ባሀሪያቸው

የኮሮና ተዋህሲ ከዓመት ከመንፈቅ በፊት በቻይና ውሃን ከተማ ሲገኝ ከነበረው ባህሪ በእጅጉ እየተለወጠ መምጣቱን ተመራማሪዎች በመግለፅ ላይ ናቸው።የዘርፉ ሊቃውንት እንደሚሉት የኮሮና ተዋህሲ እንደሌሎቹ ተዋህሲያን ራሱን መለወጡ  የሚጠበቅ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ተዋህሲያን ለምን  ራሳቸውን ይለወጣሉ?የተለወጠው ተዋህሲስ የበለጠ አደገኛ ነውን?የመሰራጨት ፍጥነቱስ?ይህ እየተለወጠ የመጣ ተዋህሲ በክትባቶች ውጤታማነት ላይ ተፅዕኖ ይኖረው ይሆን? የሚሉት ጥያቄዎች ተደጋግመው ይነሳሉ።የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅትም በነዚሁ ጥያቄዎች ላይ ያተኩራል። 
የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ዋና ሳይኒቲስት ዶክተር ሶማያ ስዋሚናታን እንደሚሉት ሁሉም ተዋህሲያን ራሳቸውን ይለወጣሉ።ልክ እንደሌሎቹ ተዋህሲያን የኮሮና ተዋህሲም ራሱን በመለወጥ ላይ ይገኛል።በዚህ የተነሳ የኮሮና ተዋህሲ በአሁኑ ወቅት በቻይና ከተገኘው የመጀመሪያው ተዋህሲ ጋር በአብዛኛው ተመሳሳይ አይደለም።ይህንን ተከትሎ  የሳይንስ ሊቃውንት  የኮሮና ተዋህሲን የለውጥ ጉዞ በዓለም ዙሪያ በመከታተል ላይ ናቸው።ከኦስትሪያ የሳይንስ አካዳሚ ሞለኪውላዊ ሕክምና ምርምር ማዕከል ዶክተር አንድሪያስ ቤክ ታይለር  የተለያዩ የተዋህሲያን ለውጦች መኖራቸውን ያስረዳሉ።
 «በመቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የተዋህሲያን ለውጦች አሉ።ይህ ደግሞ ሙሉ በሙሉ  ሙሉ ተፈጥሯዊና የተለመደ  ሂደት ነው። ምክንያቱም  በራሳቸው ዘረ-መል ውስጥ ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ የተባዙ ተዋህሲያን አሉ።ስለዚህ  የተለወጠ ተዋህሲ ተገኜ ማለት መጥፎ  ወይም ጥሩ ነው ማለት ሳይሆን ፤ ተፈጥሯዊ አሰራር ነው።»
ተመራማሪዎች እንደሚሉት የኮሮና ተዋህሲ በየጊዜው ራሱን እየለወጠ የመጣው በሰዎች ሰውነት ውስጥ በመባዛት  ሲሆን፤ሂደቱም  ተዋህሲው የራሱን የዘረ-መል  መረጃ ወደ  ሰዎች ህዋሳት በማሰራጨት ራሱን ለማባዛት ይጠቀምበታል። ከዚያም የሰውነት ህዋሳት ለተዋህሲው መዳበር የሚረዱ  የዘረ-መል  ቁሳቁሶችን በጅምላ የሚያመርቱ  የፋብሪካዎች ይሆናሉ ማለት ነው።
ይህ ማለት የዘረ-መል ለውጥ ተዋህሲው ራሱን እንዲለውጥ ያደርጉታል  ማለት ነው ።ይህ ለውጥ ከመነሻው ከነበረው ተዋህሲ የበለጠ አደገኛና ተላላፊ ሊሆን ይችላልን? የተዋህሲያን ተመራማሪዋ ሜላኒ ቢሪንክማን ለዚህ መሰሉ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ጠለቅ ያለ ጥናት ያስፈልጋል ባይ ናቸው።
«ያ በቤተ ሙከራ ውስጥ በጣም የተወሳሰበ ሙከራን ይጠይቃል።ማለትም የበለጠ ለተላላፊ ነው? የበሽታ መከላከል ስርዓትስ በተሻለ ሁኔታ ሊቋቋመው ይችላል? ለሚሉት ለጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሙከራው በትክክል መከናወን አለበት።እንደዚህ ያሉ ጥናቶች ደግሞ ብዙ ጊዜ ይወስዳሉ።» 
የመጀመሪያው የተለወጠው የኮሮና ተዋህሲ በብሪታንያ የተገኘውና B.1.1.7 በመባል የሚጠራው ዝርያ ሲሆን፣ቆይቶም በደቡብ አፍሪቃ B.1.351 የተባለ ሌላ ዝርያ ተገኝቷል።
በቤልጅየም የሊጅ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ባለፈው ሳምንት  B.1.214.2 የተባለ አዲስ የኮሮና ተዋህሲ ዝርያ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።ይህ ዝርያ በፈረንሳይ ፣ በእንግሊዝ ፣ በጀርመን ፣ በአየርላንድ ፣ በፖርቹጋል ፣ በአሜሪካ ፣ በሴኔጋል ፣ በኔዘርላንድስ እና በቡልጋሪያ ተለይቷል። በዚህ ሳምንትም በብራዚል ከደቡብ አፍሪካው ዝርያ  ጋር የሚመሳሰል አዲስ የኮሮና ተዋህሲ መገኘቱን የሀገሪቱ የጤና ባለስልጣናት እየገለፁ ነው።ባለሙያዎች እንደሚሉት በእነዚህ ዝርያዎች የተያዙ ህሙማን በሰውነታቸው ውስጥ የተዋህሲ ቁጥር በርከት ያለ ነው። 
« እንደማስበው በዚህ ወቅት የመተላለፍ ሂደቱ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በጣም ጥቂት ማስረጃዎች አሉ። ልገምተው የምችለው ብቸኛው ነገር ፤በተለወጠው ተዋህሲ የተያዙ ህሙማን ከፍ ያለ የተዋህሲ ቁጥር በሰውነታቸው ይኖራል።ይህም ለከፍተኛ የመተላለፍ አደጋ ሊዳርግ እንደሚችል ይብዛም ይነስም ማስረጃዎች ያሉ ይመስለኛል። ነገር ግን ለዚህ ትክክለኛ ማረጋገጫ አሁንም ቢሆን አልተገኜም።» 
በቤተ-ሙከራ ደረጃ የተደረጉ ምርምሮች እንደሚያሳዩት  በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለወጠው የኮሮና ተዋህሲ ስሪት ከመጀመሪያው ይልቅ  ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ዕድሉ ከፍተኛ ነው።ያ ማለት ግን የተለወጠው  የኮሮና ተዋህሲ የበለጠ አደገኛ ነው ማለት እንዳልሆነ ተመራማሪው  ይገልፃሉ።
« የበለጠ አደገኛ ነው ማለት አይደለም።በእርግጥ ከወራት በፊት ተመራማሪዎች የለዩት «ዲ 614» የተባለው የዘረ-መል ለውጥ በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ በየትኛውም ቦታ ይገኛል። በተጨማሪም ወደ ከፍተኛ ስርጭት ሊያመራ እንደሚችልም  ተመራማሪዎች በቤተ-ሙከራ ማስረጃ አግኝተዋል።ይህ ተዋህሲ  ከሰው ወደ ሰው የመተላለፉ ሁኔታ ላይ ግን  ተመራማሪዎች ሊሰሩበት የሚገባ ነገር ነው ፡፡» 
እንደ ዶክተር አንድሪያስ ቤክ ታይለር  በአሁኑ ወቅት ራሱን በመለወጥ ላይ ያለው የኮሮና ተዋህሲ በክትባት ማበልፀግ ሂደትና በክትባቱ ውጤታማነት ላይ በመጠኑም ቢሆን ተፅዕኖ ሊያሳድር  ይችላል።
«በእርግጥ ክትባቱ ብዙውን ጊዜ የሚሰራው በፀረ-በሽታ አካላት ወይም «ቲ ሴል» በተባለ  ሌላ የበሽታ ተከላካይ ሕዋስ  አማካኝነት መሆኑን ግልፅ ማድረግ ያስፈልጋል።እናም እነዚህ የበሽታ ተከላካይ ህዋሳት በተዋህሲው ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ የፕሮቲን ክፍሎችን ለይተው ያውቃሉ።እነዚህ ፕሮቲኖች ከተወገዱ ግን ዓላማው ግቡን አይመታም።ክትባቱም ሊሰራ አይችልም። ሆኖም ግን የክትባቱ ዒላማ  አንድ ብቻ አይደለም።ከዚህ አኳያ በአስር ወይም በመቶዎች የሚቆጠሩ ብዙ ዒላማዎች ሊኖሩት ይችላሉ።ነገር ግን ጥቂት የተለውጡ ተዋህሲያን የክትባቱን ውጤታማነት ሊፈታተኑ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ።»
በሌላ በኩል በህንድ ሁለት ጊዜ የተቀየረ በእንግሊዥኛው አጠራር/Double mutation/ የተባለ ሌላ የኮሮና ተዋህሲ ዝርያ መታየቱን የሀገሪቱ  ብሔራዊ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል በቅርቡ አስታውቋል። 
ይህ ዝርያ ሁለት የተለወጡ የኮሮና ተዋህሲ ዝርያዎች በአንድ ላይ በመሆን ሶስተኛ አይነት የኮሮና ተዋህሲ ዝርያ ሲፈጥሩ የሚከሰት ሲሆን፤የህንድ የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት በቅርቡ በሀገሪቱ  የተለያዩ ግዛቶች ከ700 በላይ ሰዎች በዚሁ ተዋህሲ ተይዘዋል።ይህም ከመጀመሪያው የበለጠ አደገኛ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ አሳድሯል።
ሻሂድ ጀማል የተባሉ የህክምና ባለሙያ በበኩላቸው ምንም እንኳ ተጨማሪ  ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ለሚታየው የኮቪድ-19 ህሙማን መጨመር ይህ ዝርያ  ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል።
 በአጠቃላይ የተለወጡ የኮሮና ተዋህሲዎች  ለሰው ልጆች  የበለጠ አደገኛና ተላላፊ መሆኑናቸው ወይም ለክትባቶች ያላቸው ምላሽ በጥናት ተረጋገጠም አልተረጋገጠ፤ ከምንም በላይ የጥንቃቄ መርሆዎችን በመከተል ከተዋህሲው ራስን መጠበቅ ጥናት የማያሻው መፍትሄ ነው።

UK Corona-Pandemie London
ምስል Dinendra Haria/ZUMAPRESS/picture alliance
Shimbun Cover Parodie Olympisches Logo von Tokio kombiniert mit Merkmalen des Sars-CoV-2-Virus
ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Hoshiko
Deutschland Stuttgart | Coronavirus | Moderna Impfstoff
ምስል Markus Mainka/dpa/picture-alliance

ፀሐይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ