1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሌዮፖልድ ሴዳር ሴንጎር

Robert Adé
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 8 2012

ሌዮፖልድ ሴዳር ሴንጎር የብዙ ተሰጥኦ ሰው፦ ገጣሚ፣ፖለቲከኛ እና የባህል አድናቂ ነበሩ። ይህ ብቻ አይደለም። ለጥቁር ኩራት እና ማንነት ከቆመው እና ኔግሪቲውድ ከሚባለው እንቅስቃሴ በስተጀርባ ያሉትም ሰው እሳቸው ነበሩ ። ከዚህ በተጨማሪም የሴኔጋል የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት ለመሆን በቅተዋል ፡፡

https://p.dw.com/p/3Zyox
Portrait Léopold Sédar Senghor

የሌዮፖልድ ሴዳር ሴንጎርን ህይወት በአጭሩ እንዴት መግለፅ ይቻላል?
ሴንጎር እጎአ ጥቅምት 9 ቀን 1906 ከሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር ደቡብ ምስራቅ ውስጥ በምትገኘው ጆዌል ፋዲዮስ ተወለዱ። ሴንጎር ኔግሪቲውድ በሚል መጠሪያው በ1930ዎቹ የተቋቋመው የፖለቲካ ንቅናቄ መስራች እና ዋና ተቆርቋሪም ነበሩ። በጋዜጠኝነት እና ሌሎች ሙያዎች ከተሳተፉ በኋላ እጎአ መስከረም 1960  የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ሆኑ። ሀገሪቷንም ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ በመሪነት አገልግለዋል። ሴንጎር እጎአ ታህሳስ 20 ቀን 2001 ዓም በ 95 ዓመታቸው ፈረንሳይ ሀገር ሳሉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።  

African Roots  | Léopold Sédar Senghor

ሌዮፖልድ ሴዳር ሴንጎር

ሌኦፖልድ ሴዳር ሴንጎር እንዴት ይታወሳሉ?
ሌኦፖልድ ሴዳር ሴንጎር ሰላም እና ሰብዓዊነት የተላበሱ እና ሁሉን ነገር በጥራት መስራት የሚፈልጉ ሰው ነበሩ። ለቋንቋዎች ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ታላቅ ምሁርም ነበሩ። የታዋቂው የፈረንሳይኛ ቋንቋ ምክር ቤት አካዳሚ ፍራንሴስ አባል ሆነው በፀሀፊነት የተመረጡ የመጀመሪያው ጥቁር ሰውም ነበሩ። በተጨማሪም እ.ጎ.አ. በ 1984 በራሳቸው ፍላጎት ከስልጣናቸው የለቀቁ የመጀመሪያው አፍሪቃዊ መሪም ናቸው።
የትኞቹ አለመግባባቶች ናቸው በሴንጎር ህይወት ላይ ተፅዕኖ የፈጠሩት?
እ.ጎ.አ. ከ 1962 እስከ 1968 ሌኦፖልድ ሴዳር ሴንጎር ሴኔጋል ውስጥ ታዋቂውን ግንባር ለማሸነፍ ባደረጉት ትግል በርካታ የፖለቲካ ስህተቶችን ሰርቷል፡፡ ሴንጎር የ 1968 የማርክስዝም ተማሪዎች እና የተማሪ እንቅስቃሴዎችን ብቻቸውን መጋፈጥም ነበረባቸው፡፡
ሌኦፖልድ ሴዳር ሴንጎር ምን አይነት ክብር አግኝተዋል?
ሴንጎር በርካታ እውቅናዎች እና የክብር ሽልማቶችን ተቀብለዋል። ከእነዚህም መካከል የፈረንሣይ የክብር ሽልማት ፣ የ 1968 የጀርመን የመፅሀፍ የሰላም ሽልማት እና ከተለያዩ እውቅ የዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው የክብር ዲግሪዎች አግኝተዋል። በርካታ ቦታዎችና ተቋማትም በእሳቸው ስም ይጠራሉ። ለምሳሌ ያህል የ ሌኦፖልድ ሴዳር ሴንጎር ፋውንዴሽን ፣ ሴኔጋል ውስጥ የሚገኝ ስታዲዮምና አውሮፕላን ማረፊያ ይገኙበታል። ከዚህም ሌላ በግብፅ አሌክሳንድሪያ የሚገኝ የፈረንሳይኛ ቋንቋ የሴንጎር ዩኒቨርሲቲ እና ፖርቹጋል ውስጥ የሚገኘው የሴንጎር ተቋም ናቸው።

ሌዮፖልድ ሴዳር ሴንጎር

ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ዝግጅት ነው። የዘገባው ሳይንሳዊ ምክር የተገኘው ከፕሮፌሰር ጉዳዬ ኮናቴ፣ ሊሊ ማፌላ Ph.D እና ፕሩፌሰር ክሪስቶፈር ኦግቦግቦ ነው።