1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሊያመልጥ የነበረ ወንጀለኛ መያዙ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 1 2011

ሰኞ ሐምሌ 29 2011 ዓም በተለያዩ  የወንጀል ድርጊቶች ተከሶ በሌለበት ወደ 40 ዓመት ገደማ የተፈረደበት ግለሰብ በሚከታተሉት ፖሊሶች ላይ ተኩስ ከከፈተ በኋላ ጥይት ጨርሶ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተሰማ። የቀድሞውን የሶማሌ ክልል ፕሬዝደንት ከእስር ለማስለቀቅ ተደረገ የተባለው ሙከራ ሀሰት መሆኑ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/3NWLS
Äthiopien Kaliti Gefängnis
ምስል DW/Y. Gebregziabher

«የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝደንትን ለማስፈታት ተሞከረ የተባለው ሀሰት ነው»

 ታምራት በቀለ ቶላ የተባለው ግለሰብ በወቅቱ ከፀጥታ ኃይሎች ለማምለጥ በከፈተው ተኩስ ሰበብ በስፍራው የትራፊክ እንቅስቃሴን ሲያስተናብሩ የነበሩ አንዲት የትራፊክ ፖሊስ ባልደረባ  ላይ ጉዳት መድረሱ ተነግሯል። ግለሰቡ በፖሊሶች ክትትል ውስጥ መሆኑን ሲረዳ ላዳ ታክሲ ተከራይቶ ከግብረ አበሮቹ ጋር ሲጓዝ ፖሊሶቹ እንዲቆም በማሰብ ላዳ ተሽከርካሪው ፊት ላይ ፒክ ተሽከርካሪያቸውን ሲያቆሙ ወንጀለኛው ታጥቆት የነበረውን ስታር ሽጉጥ በመጠቀም ተኩስ መክፈቱንና አሻፈረኝ በማለት ለማምለጥ መሞከሩን የቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ሃላፊ ኮማንደር ተክሉ ለታ በተለይም ለ ዶቼ ቬለ DW ተናግረዋል። በዕለቱ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት አካባቢ የተከሰተውን ግርግር  እስር ላይ የሚገኙትን የቀድሞውን የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ሙሃመድ ዑመርን ለማስለቀቅ የተሞከረ ድርጊት ነው ተብሎ የተነገረው የተሳሳተ መረጃ መሆኑን የቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ኃላፊ ኮማንደር ተክሉ ለታ በተለይ ለዶይቼ ቬለ DW ገልጸዋል። ኮማንደር ተክሉ በስም የተጠቀሰው ተፈላጊው ወንጀለኛ ጥይቱን ከጨረሰ በኃላ አንድ መጋዝን ጣራ ላይ በመውጣት ሮጦ ለማምለጥ ቢሞክርም ተይዞ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ለምርመራ ተልኮ በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል። በዕለቱ የፍርድ ቤት ቀጠሮ የነበራቸው እና በተለያዩ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ያሉት የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደሚገኙም ኮማንደር ተክሉ አክለው ተናግረዋል። ሰሎሞን ሙጬ ከአዲስ አበባ ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ