1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሊቢያ፣ የስምንት ዓመት ትርምስ

ሰኞ፣ ጥር 11 2012

ሩሲያን በማዕቀብ የቀጡት-- የሚያወግዙት የጀርመን፣የፈረንሳይ፣የብሪታንያ መሪዎች እና የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ከሩሲያዉ ፕሬዝደንት ጋር ትናንት በርሊን ዉስጥ እንደ ወዳጅ መክረዋል።በሊቢያ እና በሶሪያ ጦርነት ተቃራኒ ኃይላትን የሚረዱት የቱርክ፣ የፈረንሳይ፣የሩሲያ እና የግብፅ መሪዎች እንደ እንደ ፖለቲካ ዲፕሎማሲዉ ወግ ተነጋግረዋል።

https://p.dw.com/p/3WVoz
Deutschland Libyen-Konferenz in Berlin hat begonnen | Übersicht
ምስል Reuters/H. Hanschke

የሊቢያው ጦርነት እና የሰላም ጥረት


የምዕራብ ምስራቅ ኃያላን መጋቢት 2011 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የከፈቱትን የሊቢያ ዶሴ፣ ሙዓር ቃዛፊ ጥቅምት ላይ ሲገደሉ ዘጉት።ቃዛፊ ከተገደሉ በኋላ ሊቢያ የጦር አበጋዞች፣ የየጎጥ ሚሊሺያ መፈንጪያ፣ የአሸባሪዎች መደራጂያ፣ የስደተኞች መገደያ፣ መሸጪያ፣ መደፈሪያ፣ መታገቻ ሆናለች።8 ዓመት ከመንፈቅ።የሊቢያ መዘዝ ለሳሕሎች ተርፎ ከማሊ እስከ ለኒዠር፣ ከቡርኪና ፋሶ እስከ ቻድ ሺዎች ተገድለዋል።ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል።ለስምንት ዓመታት ከተፋላሚ ኃይላት አንዱን እየረዳ እልቂት፣ጥፋት መከራዉን የሚያባብሰዉም፣ ጥፋቱን እንደ ሩቅ ጉዳይ የሚመለከተዉም የዓረብ፤ የምሥራቅ-ምዕራብ ኃያል ዓለም፤ ቱርክ ከሊቢያ ተፋላሚዎች አንዱን እንደምትረዳ ታሕሳስ ላይ ስታስታዉቅ አቧራ የጠገበ ዶሶዉን ገለጠ።ሞስኮ ላይ ድርድር፣ በርሊን ላይ ጉባኤ፣ ብራስልስ ላይ ዉይይት እያለ ይራወጥ ያዘ።ሰላም ያወርድ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
                             
በዩክሬን ጦርነት ሰበብ ሩሲያን በማዕቀብ የቀጡት፣ በሶሪያዉ ጦርነት ሩሲያን የሚያወግዙት የጀርመን፣ የፈረንሳይ፣ የብሪታንያ መሪዎች እና የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ከሩሲያዉ ፕሬዝደንት ጋር ትናንት በርሊን ዉስጥ እንደ ወዳጅ መክረዋል።በሊቢያ እና በሶሪያ ጦርነት ተቃራኒ ኃይላትን የሚረዱት የቱርክ፣ የፈረንሳይ፣ የሩሲያ እና  የግብፅ መሪዎች እንደ እንደ ፖለቲካ ዲፕሎማሲዉ ወግ ተነጋግረዋል።
የአንዲት ሊቢያ የአንድ ዘመን ትዉልዶች ግን የተፋላሚ ኃይላት መሪዎች ስለገዛ ሐገራቸዉ  መነጋገር ዓይደለም አንድ አዳራሽ ዉስጥ አብሮ መቀመጥም አልፈለጉም።ምክንያቱም «ልዩነታቸዉ ስር የሰደደ ስለሆነ---» ይላሉ የጉባኤዉ አስተናጋጅ የጀርመኗ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል።
«ከሁለቱም ጋር በተናጥል ተነጋግረናል።በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለዉ ልዩነት በጣም ሰፊ በመሆኑ አይነጋገሩም።የጉባኤዉ ተካፋዮችም አልነበሩም።ይሁንና እዚሁ በቅርብ ነበሩ፤ አንድ ክፍል ዉስጥ ግን አልነበሩም።እንዲያዉ የዉይይቱን ዉጤት በቅርብ እንድነግራቸዉ እዚሁ በርሊን ነበሩ።»
የሙዓመር ቃዛፊን ቤተ-መንግሥት የተባበሩት መግሥታት ድርጅት ያስረከባቸዉ ጠቅላይ ሚንስትር ፈይዝ አል-ሰራጅ እና ያን ዘመናይ ቤተ-መንግስት በኃይል ለመቀማት የሚዋጉት የጦር አበጋዝ ኸሊፋ ሐፍጣር የበርሊኑን ጉባኤ ለመታረቂያ ሳይሆን አስታጣቂ ረዳቶቻቸዉን ለመማፀኚያ ተጠቅመዉበታል።
የዓለም ኃያላን በርሊን ላይ ሥለ ሊቢያ ዉድመት ሲነጋገሩ የሐፍጣር ጦር 5 የነዳጅ ማምረቻና ማከማቻ ተቋማት ነዳጅ ዘይት እንዳሸጡ አግዷል።ተቋማቱ በየቀኑ 800 ሺሕ በርሚል ነዳጅ ለዉጪ ገበያ ይሸጣሉ።ለሊቢያ መንግሥት 55 ሚሊዮን ዶላር ያስገባሉ።ሐፍጣር እንደ ጦር አበጋዝ ወታደራዊ  እርምጃ ሲወስዱ አል ፈራጅ እንደ ሲቢል መሪ የተረፋቸዉን አማራጭ ቀሰቀሱ።የተቃዉሞ ሰልፍ።ትሪፖሊ።
የትሪፖሊ ነዋሪዎች ሐፍጣርን ያወግዛሉ።«ተኩስ አቁም ይደረግ መባሉን አልደግፍም።ምክንያቱም ተኩስ አቁሙን ወንጀለኛዉ ሐፍጣር ትሪፖሊን ለመቆጣጠር እና ተጨማሪ ደም ለማፍሰስ፣ ጦር መሳሪያ ለማከማችትና ወታደሮቹን ለማደራጀት ይጠቀምበታልና።»
ቤንጋዚዎች ባንፃሩ፣ አልሳራጅን ወይም ደጋፊያቸዉን ቱርክን ያወግዛሉ።«ተቃዉሟችን ለምዕራባዉያን፣ ለፀጥታዉ ምክር ቤትና ለአዉሮጳ ሕብረት  መልዕክት ለማስተላለፍ ነዉ።ቱርክ የኔቶ አባል ብትሆንም፣ የቱርኩ ፕሬዝደንት አጋጣሚዉን በመጠቀም ጦራቸዉን ወደሊቢያ ለማዝመት ይፈልጋሉ።
ወታደሩና አርክቴክቱ
የግብፃዊ እናት-የሊቢያዊ አባት ዉጤት ነዉ።ክልስ።ኸሊፋ ቤልቃሲም ሐፍጣር።በ1960 የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርቱን ለመከታተል ከሰሜን ምስራቃዊቱ የትዉልድ መንደሩ አጅዳቢያ፣ ሻል ወዳለችዉ ከተማ ደርና ገባ።17 ዓመቱ ነበር።በዚያዉ ዓመት ከጥንቷ ጣራቦሊስ ቅኝ ገዢ ከቱርክ ደም የሚወርሱት የንጉስ ኢድሪስ ሐብታም ሚንስትር መሐመድ አል ሳራጅ የወንድልጅ አባት ሆኑ።ስሙኑም ፋይዝ አሉት።
ፋይዝ እንደ ሐብታም ሚንስትር፣ ከቱጃሮቹ ትምሕርት ቤት ፊደል ሲቆጥር ወጣቱ ኸሊፋ  ጦር ትምሕርት ቤት ገባ።በ1969 ሻለቃ ሙዓመር ቃጣፊ በመሩት መፈንቅለ መንግሥት የንጉስ ኢድሪስን ዘዉዳዊ አገዛዝ ሲያስወግዱ ወጣቱ የጦር መኮንን ከቃዛፊ ቀኝ እጆች አንዱ ነበር።
ኸሊፋ እንደ ወታደር ምሽግ ገብቶ-እንደ ፖለቲከኛ ቤተንግስትን የሚያማትረዉን የናስር አስተምሕሮን ሲያቀነቅኑ ፋይዝ፣ ትምሕርት ቤት እያማረጡ ዩኒቨርስቲ ለመግባት ይዘጋጁ ነበር።በዉልደት ክልስ፣ ባመለካከት ቅይጥ የሆኑት የመስመር መኮንን ሶቭዬት ሕብረት ሔደዉ የአብዮታዊ የጦር መኮንንነትን ተምረዉ ተመለሱ።
በ1973 አረቦች እና እስራኤል ሲዋጉ ሲና በረሐ የነበረዉን የእስራኤል ጦር ምሽግ ሰብሮ የገባዉ የአረብ ጦር አባል በመሆናቸዉ ተሸልመዉ ተሾሙ።ኮሎኔል።
በ1980 ቻድን የሚወጋዉን ጦር እንዲያዙ ሲሾሙ፣ ፈይዝ አልሰራጅ በሥነ-ሕንፃ (አርክቴቸር)ትምሕርት ከዩኒቨርስቲ ተመረቁ።ኮሎኔል ሐፍጣር ለድል ሲጠበቁ ተማረኩ።ከምርኮ ሲለቀቁ ወደ ሐገራቸዉ ከመመለስ ይልቅ ሐገራቸዉንም መሪያቸዉንም ከድተዉ፣ ለአሜሪካኖች አድረዉ በዛኢር በኩል ኬንያ፣ ከዚያም ዩናይትድ ስቴትስ ገብተዉ የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን መንግስት ለማስወገድ ይጣጣሩ ገቡ።
የአሜሪካዉ ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት CIA መረጃ አቀባይ (ሰላይ) መሆናቸዉ በሰፊዉ መነገር የጀመረዉም ያኔ ነዉ።የኮሎኔል ማዕረጋቸዉን አዉልቀዉ ሲቢል ሆኑ።በሊቢያዊነታቸዉ ላይ አሜሪካዊ ዜግነት ደረቡበት።የሥነ-ሕንፃዉ ባለሙያ ፋይዝ አልሰራጅ ግን በዚህ ሁሉ መሐል የሊቢያ የቤቶች ጉዳይ ሚንስቴር ባልደረባ ሆነዉ ይሰሩ ነበር።
በ2011 የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጦር የኮሎኔል መዓመር ቃዛፊን መንግስት ሲያስወግድ ሊቢያዊዉ፣ አሜሪካዊዉ፣ ሱፍ ከራባት አጥላቂዉ ኸሊፋ ሐፍጣር የጄኔራልነት ማዕረግ ለጥፈዉ ቤንጋዚ ላይ ብቅ አሉ።
ከ2014 ጀምሮ አልሰራጅ የፖለቲካ ኃይልና ተጣማሪ እየቀያየሩ የትሪፖሊን ፖለቲካ ሲዘዉሩ ሐፍጣር ከቤንጋዚ ተቀናቃኞቻቸዉን ተራ በተራ እያጠፉ ኃይላቸዉን ያጠናከሩ ነበር።አልሰራጅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰየመዉን የብሔራዊ ስምምነት መንግሥትን የመሪነት ሥልጣን በ2015 ሲይዙ፤ ሐፍጣር ቶብሩክ የከተመዉ ምክር ቤት የጦር አዛዥ ሆነዉ የአልሰራጅን መንግስት ለማስወገድ ይዝቱ ገቡ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሊቢያ ተዋጊዎች ላይ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማዕቀብ ጥሏል።ግብፅ፣የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ዮርዳኖስ፣ እስራኤል፣ ፈረንሳይ እና ሩሲያ ሕግ ጥሰዉ ሕጋዊ እዉቅና ያለዉን መንግሥት የሚወጋዉን የኸሊፋ ሐፍጣርን ጦር ከማስታጠቅ የከለከላቸዉ ሕግ፣ደንብ ሥነ ምግባርም የለም።
እስከትናንት ድረስ ለአልሳራጅ መንግሥት ታዳላለች የምትባለዉ የቀድሞዋ የሊቢያ ቅኝ ገዢ ኢጣሊያ ብዙ ያሳሰባት የጎረቤቷ የፈረንሳ፣ የጥቅም አጋሪዎችዋ የግብፅ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ወይም የእስራኤል ጣልቃ መግባት አይደለም።የሩሲያ እንጂ።የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮብ ግን ይጠይቃሉ።
«በ2011፣ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤትን ዉሳኔን በመጣስ፣ ሊቢያ በቦምብ እድትደበደብ ሲወሰን ኢጣሊያ የትነበረች።እኔ እስከማዉቀዉ ድረስ ኢጣሊያ የተጫወተችዉ አብይ ሚና አልነበረም።(የያኔዎቹን) ጀብደኞቹን መሪዎች ማንነት ሁሉም ስለሚያወቀዉ እኔ መጥቀስ ያለብኝ አይመሰለኝም።ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሊቢያ ሐገረ-መንግሥትነት ጠፍቷል።አልተጠገነም።»
ላቭሮቭ «ጀብደኛ» ያሏቸዉ የ2011ዶቹ ወራሪዎች ሳርኮዚ፣ ካሜሩን እና ኦባማ ነበሩ።ከ2015 ወዲሕ ደግሞ ለየሕዝባቸዉና ባደባባይ ለዝንተ ዓለም እንደ ጠላት የሚወጋገዙት የእስራኤል እና የአረብ ገዢዎች፣ የፓሪስና የሞስኮ ተቀናቃኞችም ሐፍጣርን በመርዳት አንድ ሆነዋል።
ባለፈዉ ታሕሳስ የጥንቷ ጣራቦሊስ የጥንት ቅኝ ገዢ ቱርክ «ሕጋዊዉን የትሪፖሊ መንግስትን ከሐፍጣር ጦር ጥቃት የሚከላከል ጦር እንደምታዘምት ስታስታዉቅ ግን የምሥራቁም-የምዕራቡ ኃያል፣ ዓረቡም፣ የሁዲዉም ተነቃነቀ።
የአንካራና የሞስኮ መሪዎች የሊቢያ ተፋላሚ ኃይላትን ተኩስ እንዲያቆሙ ማስገደዳቸዉ፣ ንቅናቄዉ ለሰላም ወዳዶች «ሳይደግስ አይጣላም» ዓይነት ሆኖ ነበር።ይሁንና ባለፈዉ ሳምንት ተኩስ አቁሙን በፊርማ ለማፀደቅ ሞስኮ ላይ የተጠራዉን ድርድር የጦር አበጋዝ ኸሊፋ ሐፍጣር ማቋረጣቸዉ ተስፋ በተስፋ ያስቀረዉ መስሏል።
ትናት በርሊን የተደረገዉ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ደግሞ የሞስኮዉን ጅምር የሚያጠናክር የተኩስ አቁሙን የሚያፀና መሆኑ በሰፊዉ ተነግሯል።የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሐይኮ ማስ ከሚነገረዉም አለፍ ብለዉ ለሊቢያ ሰላም የሚወርድበት ቁልፍ አግኝተናል ይላሉ።
«የገንባንበት ጉባኤን ዓላማ ዛሬ ከግቡ ካደረስን በኋላ የሊቢያን ጦርነት የምንፈታበትን ቁልፉ አግኝተናል ማለት እችላለሁ።ከእንግዲሕ የሚደረገዉ ቁልፉን ከጋኑ መክተትና እንዲከፈት ማዞር ነዉ።»
የሰሜን አትላንቲክ ጦር በ2011 ሊቢያን መደብደቡን የተቃወሙት ብቸኛዉ የኔቶ አባል ሐገር ባለስልጣን የያኔዉ የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ ነበሩ ።እስካሁን በሊቢያዉ ቀዉስ በቀጥታ እጃቸዉን ካላስገቡ ትላልቅ የአዉሮጳ ሐገራት አንዷ ጀርመን ናት።ጀርመን የጨበጠችዉ፣ በማስ አገላለጥ «የመትሔ ቁልፍ»  የአዉሮጳ ሕብረት እንዲሆን የሕብረቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች እየመከሩ ነዉ።የቱርክ የረጅም ጊዜ ጠላት ግሪክ ግን የሕብረቱን የጋራ አቋም ለመሻር ትፎክራለች።ሊቢያዎችም ለመጠፋፋት ይዛዛታሉ።ምናልባት ለሌላ ዘመን።ቀጣይ እልቂት።

Konflikt in Libyen | Kämpfe
ምስል picture-alliance/dpa/A. Salahuddien
Libyen Tripolis Beerdigung getöteter Soldaten nach Anschalg
ምስል picture-alliance/AP Photo/H. Ahmed
Bildkombo Haftar und as-Sarradsch
Deutschland Libyen-Konferenz in Berlin hat begonnen
ምስል AFP/T. Schwarz

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ