1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የተሰጠው የሄሰን የሰላም ሽልማት

ረቡዕ፣ መስከረም 14 2012

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የዚህ የሰላም ሽልማት 25ተኛው አሸናፊ ናቸው።ለሽልማቱ የተመረጡትም ለዓመታት በጠላትነት ሲተያዩ በነበሩት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ታሪካዊ የተባለ የሰላም ስምምነት በመፈፀማቸው መሆኑ ትናንት በሄሰን ግዛት ዋና ከተማ በቪስዳን ምክር ቤት በተካሄደው የሽልማት አሰጣጥ ስነ ስርዓት ላይ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/3QBMH
Hessischer Friedenspreis  an Abiy Ahmed Ali
ምስል DW/H. Melesse

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የተሰጠው የሄሰን የሰላም ሽልማት

 

በጀርመንዋ በሄሰን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ዋና ከተማ በቪስባደን ትናንት በተካሄደው ዓመታዊው የሄሰን የሰላም ሽልማት አሰጣጥ ስነ ስርዓት ላይ የዘንድሮው ተሸላሚ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አልተገኙም። የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በርሳቸው ስም ሽልማቱን ተቀብለዋል።ከ16ቱ የጀርመን ፌደራል ክፍለ ግዛቶች  አንዷ የሆነችው ሄሰን ከ6 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች አሏት ። ግዛቲቱ የአውሮጳ የንግድ ማዕከል የሚባለው ትልቁ የፍራንክፈርት ከተማ መገኛ ናት። በዚህች ግዛት የተሰየመ የሰላም ሽልማት፣በሃገራት መካከል መግባባትና ሰላምን በማስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሰዎች በየዓመቱ ይበረከታል።ሽልማቱን የቀድሞ የሄሰን ጠቅላይ ሚኒስትር አልበርት ኦስቫልድ በጎርጎሮሳዊው ጥቅምት 1993 ነው የመሰረቱት።የሽልማቱ አሸናፊ25 ሺህ ዩሮ ይሰጠዋል።የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የዚህ ሽልማት 25ተኛው አሸናፊ ናቸው።ለሽልማቱ የተመረጡትም ለዓመታት በጠላትነት ሲተያዩ በነበሩት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ታሪካዊ የተባለ የሰላም ስምምነት በመፈፀማቸው መሆኑ ትናንት በሄሰን ግዛት ዋና ከተማ በቪስዳን ምክር ቤት በተካሄደው የሽልማት አሰጣጥ ስነ ስርዓት ላይ ተገልጿል። የሸላሚው የአልበርት ኦስቫልድ ድርጅት የባለ አደራ ቦርድ ሊቀመንበር ካርል ሽታርዛአህር በሽልማቱ ስነ ስርዓት ላይ በንባብ እንዳሰሙት ይህም ለዶክተር ዐብይ አህመድ በተሰጠው ምስክር ወረቀት ላይ ሰፍሯል።

«የሄሰን የሰላም ሽልማት ተቋም የአልበርት ኦስቫልድ ድርጅት የባለአደራ ቦርድ የ2019 ዓምን የሄሰን የሰላም ሽልማት ለክቡር ዐቢይ አህመድ ሰጥቷል።የባለ አደራ ቦርዱ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል እርቀ ሰላም እንዲወርድ  ያደረጉትን የሰላም ጥረት፣ በዚህም አካባቢውን በማረጋጋት ብሎም በሃገር ውስጥም ፖለቲካውን  ኤኮኖሚውን ነጻ ለማድረግ ላከናወኑት ተግባር አክብሮቱን ይገልጻል ቪስባደን መስከረም 23፣ 2019፣ ቦሪስ ራይን የሄሰን ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እንዲሁም ካርል ሽታርስአኽር የሄሰን የሰላም ሽልማት ተቋም የአልበርት ኦስቫልድ ድርጅት የባለአደራ ቦርድ ሊቀመንበር ።»

Äthiopien President Somalia Mohammed Abdulahi, Eritreas Präsident Isayas Afeworki, Äthiopiens Premierminister Abiy Ahmed
ምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

በዚህ ሥነ ስርዓት ላይ የሄሰን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ጠቅላይ ሚኒስትር ፎልከ ቡፍየ ባሰሙት ንግግር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን የሰላም ጥረት እና ስኬት አድንቀዋል። ይህም ከሌሎች እንደሚለያቸውም የገለጹት ሚኒስትሩ ተግባራቸውን አርቆ አሳቢነት ብለውታል።

«ስሥልጣን በያዙ በ3 ወራት ይህን ማሳካታቸው በእውነቱ በጣም ድንቅ ነው።ቁርጠኝነታቸው አስደምሞኛል።የቀድሞው ወታደርና  የደህንነት መስሪያ ቤት አባል ብዙዎች የሚሄዱበትን የጭቆናና እና ባሲልም ኃይል የተቀላቀለበት መንገድ አልመረጡም። ይልቁንም ከዛ ተቃራኒ የሆነውን መንገድ ነው የመረጡት የሰላም እጃቸውን ዘርግተዋል። ይሄ ልዩ ያደርጋቸዋል።ይህም ቁርጠኝነት እና አርቆ አሳቢነት ነው።»

በጎው ጥረት የውስጥም የውጭ ፈተና እንዳላጣው ጠቅላይ ሚኒስትር ቡፍየ በንግግራቸው ጠቅሰዋል። ቡፍዬ የኢትዮጵያ የሰላም ጥረት ሌሎች ችግር ውስጥ የሚገኙ የአፍሪቃ ቀንድ ሃገራትንም የሚያካትት መሆኑን አስታውሰው ችግሩም ከምሥራቅ አፍሪቃም አልፎ አውሮጳም ድረስ የሚዘልቅ መሆኑን አንስተዋል።

Hessischer Friedenspreis wird an Abiy Ahmed Ali verliehen
ምስል DW/H. Melesse

«የኢትዮጵያ የሰላም ጥረት በኤርትራ ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ሰላም በራቃቸው በሶማሊያ እና በደቡብ ሱዳን እንዲሁም በሱዳንም ጭምር ነው። ግራ የሆነ ነገር የሰፈነበት ሰላም የራቀው የዓለማችን ጥግ ነው። ችግሩ እኛም በአውሮጳ በጀርመን እዚህም በሄሰን ያለን እየተሰማን ነው።ወደኛ የሚመጡ ስደተኞችን ስንቆጥር በአውሮጳ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ከኤርትራ የሚመጡት ናቸው።ያ ማለት የኢትዮጵያ ስኬት ለሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት አነቃቂ ነው። ልዩ ትኩረት የተሰጠው ለምንድነው? እኔ እስካየሁት ድረስ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው።በኔ አመለካከት ይህ የሰላም ጥረት ከውጭ የመጣ አይደለም። የወታደራዊ እርምጃም ውጤት አይደለም። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄደ ጉባኤ ውጤትም አይደለም። ከውስጥ የመጣ እንጂ።»

ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተበረከተውን የሄሰን የሰላም ሽልማት በቪስባደን ምክር ቤት ተገኝተው በስማቸው የተቀበሉት የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያትም በሥነ ስርዓቱ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተላከውን መልዕክት በንባብ አሰምተዋል።

«ዛሬ በመካከላችሁ መገኘት ባልችልም ለሰጣችሁኝ እውቅና ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን እና አድናቆቴን እባካችሁ ተቀበሉኝ።ሽልማቱ አሁን በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ላለው ለውጥ እውቅና እንደመስጠት ነው የምቆጥረው።የሄሰን የሰላም ሽልማት በአካባቢው ሰላምን ለማስፈን ለሚደረጉ አስተዋጽኦዎች እውቅና ይሰጣል። ግን ሥራው  በራሱ ለሰላም መስፈን የሚጥሩ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ውጤት ነው።ሰላም ለኢትዮጵያ ለአፍሪቃ ቀንድ እና ለአህጉሩ ጠቃሚ ሲሆን የሁሉንም ቁርጠኝነትም ይፈልጋል።»  

 ወይዘሮ ሙፈርያት ከሽልማቱ ሥነ-ስርዓት በኋላ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ሽልማቱ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውን ትልቅ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል።

Hessischer Friedenspreis wird an Abiy Ahmed Ali verliehen
ምስል DW/H. Melesse

በጀርመን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ወይዘሮ ሙሉ ሰሎሞንም ሽልማቱ ለዶክተር ዐብይ በመበርከቱ የተሰማቸው ደስታ ለዶቼቬለ ገልጸዋዋል።

የጀርመን መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ታዋቂ ሰዎች የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች እና የተለያዩ ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት በዚህ ስነ ስርዓት ላይ ከታደሙት መካከል አድራ ለተባለ በኢትዮጵያ ውስጥ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን ለሚያከናውን የጀርመን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባልደረባ አቶ ዳዊት መሃሪ ይገኙበታል።በዶክተር ዓቢይ መሸለም ደስተኛ ናቸው።ዓብይ ሥራቸውን ከዳር እንዲያደርሱ ግን ድጋፍ ያሻቸዋል ይላሉ።

የሄሰን የሰላም ሽልማት የተበረከተላቸው ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከሽልማቱ ያገኙትን 25ሺህ ዩሮ ለመልካም ወጣት ማዕከል ግንባታ ሰጥተዋል። ከሄሰኑ የሰላም ሽልማት ተቀባዮች መካከል የቀድሞ የፊንላንድ ፕሬዝዳንት ማርቲ አህቲሳሪ እና የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳዮች ሃላፊ ፌደሪካ ሞጎሮኒ ይገኙበታል።

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ