ለጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናት የተሐድሶ ማዕከል
ረቡዕ፣ ሰኔ 12 2011በአማራ ክልል በተለያ ምክንያቶች ከመኖሪያ ቀያቸው ወደ ከተማ የሚገቡ ሕጻናት ቁጥር እጨመረ ነው፡፡ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናትን ከኅብረተሰቡ ጋር በመነጋገር ወደመጡበት እንደሚልክ ቢናገርም ወደ ከተማ የሚፈልሱ ሕጻናት ቁጥር ግን አሁነም አልቀነሰም፡፡
ዓለምነው መኮንን ሰሞኑን ከሰሜን ጎንደር ዞን አካባቢ ወደ ባሕር ዳር የገቡ ሕጻናትን አግኝቶ ለምን አንደመጡ በጠየቃቸው ጊዜም ፤ ከቤተሰብ አለመስማማት፣ የወላጅ ሞት እና ሌሎች ምክንያቶች ለጎዳና ሕይወት እንደዳረጋቸው ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የሕጻናት መብት እና ደህንነት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሻግሬ ዘውዴ ለዶይቼ ቬለ DW እንደተናገሩት ደግሞ የጎዳና ሕጻናት ተመልሰው ወደ ከተማ እንዳይገቡ እና ሌሎችንም እንዳይስቡ የሚያስችል የተሀድሶ ማዕከል ለመገንባት ታቅዷል።
በበጀት ዓመቱ ከ234ሺህ በላይ በችግር ላይ ያሉ ሕጻናትን እና ከ4600 በላይ የጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናትን የመለየት እና የመመዝገብ ሥራ መከናወኑን አብራርተዋል። ለችግር ከተጋለጡት ሕጻናት መካከል 150ዎቹን በአገር ውስጥ አሳዳጊዎች መሰጠታቸውን፣ በርካቶቹ ደግሞ የስፖንሰር ሺፕ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
ከተለዩ የጎዳና ተዳዳሪዎች መካከልም 270 ሕጻናት ወደየቤተሰቦቻቸው መቀላቀል መቻሉን አቶ አሻግሬ ተናግረዋል። የ ሕጻናቱን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከባለሀብቱ፣ ከመንግሥት ሠራተኛውና ከኅብረተሰቡ ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡንም አመልክተዋል።
እንደዚሁም የ108 የመንግሥት ቢሮ ሠራተኞች ከወር ደመወዛቸው እቆረጡ 520 ሕጻናት ያለምንም ችግር የትምህርት ቤት ወጪ ተሸፍኖላቸው እንዲማሩ እየተደረገ እንደሆነ አቶ አሻግሬ ተናግረዋል።
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
ተስፋለም ወልደየስ