1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

ቅዱስ አንተነህ

ዓርብ፣ መስከረም 29 2013

ቅዱስ አንተነህ በሚኖርባት እና በሚማርባት ዮናይትድ ስቴትስ አንድ የአስጠኝ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ከፍቶ እየሰራ ይገኛል። ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ ውስጥ ከቤተሰቦቹና አጋሮቹ ጋር በመሆን ገጠር ውስጥ ትምህርት ቤት ከፍቶ ህፃናትን ያስተምራል።

https://p.dw.com/p/3jfb9
Kidus Anteneh Student University of Maryland
ምስል Privat

ቅዱስ አንተነህ

ቅዱስ አንተነህ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኘው ዮንቨርስቲ ኦፍ ሜሪላንድ የሶስተኛ ዓመት የኮምፒውተር ሳይንስና የሂሳብ ተማሪ ነው። ወጣቱ የራሱ የሆነ ሜሪላንድ ቱቶሪንግ ሰርቪስስ የተባለ የአስጠኚ አገልግሎት መስጫ ተቋም ከፍቷል። «ከህፃናት መዋያ እስከ ኮሌጅ ላሉ ተማሪዎች በሚፈልጉበት የትምህርት ዓይነት እና ሰዓት የማስጠናት አገልግሎት እንሰጣለን።» ይላል። በኦንላይን እና በአካል ወደ ደንበኞቻቸው በመጓዝ ይህንን አገልግሎት እንደሚሰጡ የሚናገረው ቅዱስ የሚያስጠኗቸው ተማሪዎችም ይሁኑ አስጠኚዎቹ የግድ ኢትዮጵያውያን ብቻ እንዳልሆኑ እና ዘርፈ ብዙ እንደሆኑ ገልፆልናል። ቅዱስ ይህንን የጥናት አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሁለት አመቱ ነው። ከዚህ በፊት ራሱ አስጠኚ ሆኖ ሌላ መስሪያ ቤት ውስጥ ይሰራ ነበር።  አሁን 30 የሚጠጉ አስጠኚዎች በትርፍ ሰዓታቸው አብረውት ይሰራሉ። እሱ እንደሚለው «በብዛት አስጠኞቹ የኮሌጅ ተማሪዎች ፣ በትምህርታቸው ጎበዝ የሆኑ እና የማስጠናት ችሎታ ያላቸው ናቸው። » 

የቨርጂኒያ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ቅድስት የ15 ዓመት ልጅ አላቸው። በተለይ ትምህርት ቤቶች በኮሮና ምክንያት ተዘግተው በነበሩበት ወቅት ለልጃቸው የጥናት አገልግሎት አመቻችተውለት ነበር። የቅዱስ ተቋም ወጣቱን ሂሳብ እና እንግሊዘኛ በማስጠናት ያግዘው እንደነበር የገለፁልን ወይዘሮ ቆንጂት « ልጄ ተጠቃሚ ነበር። ወዶቷል። ምንም እንኳን አገልግሎቱ በኦንላይን ብቻ ቢሆንም ጠቅሞታል።» ይላሉ። ዩናይትድ ስቴትስ እስካሁን በኮቪድ 19 በሞተና ኮሮና በተያዘ ሰው ቁጥር ከዓለም ቀዳሚዋ ሀገር ናት። በዚህ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ቤት ለቤት ተዘዋውሮ ማስጠናቱን እነ ቅዱስም የሚመርጡት አይደለም። « እኛም በዚህ በኮቪድ ጊዜ ሰው ቤት ላለመሄድ ነው የምንፈልገው» ይላል ቅዱስ። ይሁንና አስጠኚዎቹ ወደ ደንበኞች የሚሄዱበት አንዳንድ አጋጣሚዎችም አሉ። ለምሳሌ «በኦንላይን ትኩረታቸውን ሰብስበው መማር የማይችሉ ተማሪዎች ካሉ ወይም ልዩ ድጋፍ የሚሹ ተማሪዎች ከሆኑ።» ከዚህ ውጪ  ቅዱስ በአካል ተገኝተንም ይሁን በኦንላይ የምንሰጠው ድጋፍ ላይ ምንም አይነት ልዩነት የለም ባይ ነው። እንደዚህ አይነት የማስጠናት አገልግሎቶችም ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ መሆን እንደሚችሉ ወጣቱ ያምናል። 
ቅዱስ ከኢትዮጵያ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከሄደ ገና አራት ዓመቱ ነው። ምንም እንኳን ወጣቱ ጎበዝ ከሚባሉት ተማሪዎች ተርታ ቢሰለፍም፤ ወደ ውጪ ለመሄድ እድል ያገኘው በስፖርት ተሳትፎው ነው። «ቅርጫት ኳስ ድሮ እጫወት ነበር። እና በዚሁ አጋጣሚ ተጻፅፌ ነው ይህንን እድል ያገኘሁት።» ይላል። አሁን በትምህርቱ ሙሉ የነፃ እድል አግንቶ እየተማረ ይገኛል።

የቅዱስ ትምህርት ቤት ተማሪዎች
የቅዱስ ትምህርት ቤት ተማሪዎችምስል Kidus Anteneh

ቅዱስን ለየት የሚያደርገው ሌላም ነገር አለ። ከቤተሰቦቹ እና ሌሎች የሚያግዙት ሰዎች ጋር በመሆን ከአንድ ዓመት በፊት ደብረ ሊባኖስ ውስጥ አንድ ትምህርት ቤት አቋቁሞ 35 የሚሆኑ ህፃናትን ያስተምራሉ። ትምህርት ቤቱም የሚጠራው በራሱ በቅዱስ ስም ነው። « ገጠር ውስጥ ትምህርት ቤት የሌለበት አካባቢ ሄድን ከቀበሌው ጋር ተባብረን እነሱ ቦታ ሰጥተውን እኛ አስፈላጊዎችን ነገሮች አሟልተን የሚማሩበትን ሁኔታ አመቻችተናል» ይላል አሁን ግን በኮቪድ 19 ስጋት የተነሳ ትምህርት ቤቱ እንደተዘጋ ነው። ቢሆንም ተማሪዎች የቤት ስራ እየተሰጣቸው እቤት ሆነው የሚማሩበትን መንገድ እንዳለ ቅዱስ ይናገራል።
አቶ አሰፋ ታፈሰ ወደ ቅዱስ ትምህርት ቤት ልከው የሚያስተምሩት የ 9 ዓመት ልጅ አላቸው። ሁለተኛ ልጃቸው ደግሞ ዘንድሮ ትምህርት ይጀምራል። ከዚህ በፊት ልጃቸውን ወደ ትምህርት ቤት ልከው ለማስተማር አማራጭ አልነበራቸውም። « ልጆቹ ትምህርት ቤት ሩቅ ስለሆነ እቤት ቁጥ ብለው ነበር። ይህኛው ትምህርት ቤት ግን ቅርብ ስለሆነ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ህብረተሰብም ብዙ ጥቅም አለው» ሲሉ ለዶይቸ ቬለ DW ገልፀዋል።  ቅዱስ የ 22 ዓመት ወጣት ነው። የስኬቱ ሚስጥር በራስ መተማመን እንደሆነ ገልፆልናል። ወደፊት ደግሞ ከትምህርት ጋር የተያያዘ እና በሰው ሰራሽ መሣሪያ ወይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዘ ድርጅት መክፈት ነው። ቅዱስ ከቤተሰቦቹ ጋር ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያስተምራቸውንም ህፃናት ልጆች ቁጥር ከፍ የማድረግ እቅድ እንዳለው አጫውቶናል። 

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ