1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለደንበኞቹ 130 ሺሕ ጥቅሎች ከታዘዘበት ያደረሰውን እሺ ኤክስፕረስ ያውቁታል?

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 27 2014

እሺ ኤክስፕረስ በጎ ፈቃደኞች የለገሱትን ደም፣ የባንኮች ሰነዶች፣ አበቦች እና አልባሳትን ጨምሮ 130 ሺሕ ጥቅሎችን በደንበኞቹ ከታዘዘበት ያደረሰ ጀማሪ ኩባንያ ነው። ከአራት አመታት በፊት በ1.3 ሚሊዮን ብር ገደማ የተቋቋመው እሺ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአዳማ እና በሐዋሳ ከተሞች አገልግሎት ይሰጣል። እሺ እንዴት እዚህ ደረሰ?

https://p.dw.com/p/45BsR
Äthiopien Start-Up l Eshi Express
ምስል Eshi Express

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ ለደንበኞቹ 130 ሺሕ ጥቅሎች ከታዘዘበት ያደረሰውን እሺ ኤክስፕረስ ያውቁታል?

ከአራት አመታት በፊት የተመሠረተው እሺ ኤክስፕረስ ባለፈው ሣምንት ለደንበኞቹ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ያደረሳቸው ጥቅሎች ቁጥር 130 ሺሕ ደረሰ። ኩባንያው እስካሁን ሥራውን የሚያከናውነው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአዳማ እና በሐዋሳ ከተሞች ነው። የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጥጋቡ ኃይሌ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ባለፉት አመታት እሺ የሕክምና ተቋማት ለምርመራ የሚፈልጓቸውን ናሙናዎች እና ውጤቶች፣ አበባዎች፣ የተለያዩ ሰነዶች፣ ደረሰኞች፣ አልባሳት እና ጫማዎች በደንበኞቹ ትዕዛዝ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ አድርሷል።

"ከደም ባንክ ጋር ባለን ውል መሠረት በአዲስ አበባ የተለያዩ የደም ልገሳ ማዕከሎች የሚለገሱ ደሞችን ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት የምናደርስላቸው እኛ ነን። ከአንድ አመት በፊት የምርጫ ወቅት ነበር። የምርጫ እንቅስቃሴ ላይ አስቸኳይ ነገሮችን ለሚዲያዎች፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች በየጊዜው የምናደርስላቸው እኛ ነበርን" ሲሉ ስለ ደንበኞቻቸውና የኩባንያው ሥራ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ኩባንያው "ለህብረተሰቡ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች" ማጓጓዝ ላይ እንደሚያተኩር የገለጹት አቶ ጥጋቡ እስካሁን መጠጥ እና ጫት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ የማድረስ አገልግሎት አይሰጥም። 

እሺ የደንበኞቹን ጥቅል ኤክስፕረስ በተባለ ፈጣን አገልግሎቱ በአዲስ አበባ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲያደርስ የክፍያው መነሻ 20 ብር ሆኖ በኪሎ ሜትር 12 ብር እየጨመረ ይሔዳል። ጠዋት የተቀበለውን ጥቅል በተመሳሳይ ቀን ከሰዓት በኋላ ደንበኞቹ ካዘዙበት ቦታ ለሚያደርስበት ሁለተኛ አገልሎት 90 ብር ያስከፍላል። ዛሬ የተቀበለውን ትዕዛዝ በ24 ሰዓታት ውስጥ ለሚያደርስበት ሶስተኛ አገልግሎት በአንጻሩ ክፍያው 70 ብር  ነው።

የእሺ ኤክስፕረስ ድረ-ገጽ ኩባንያው የደንበኞቹን ትዕዛዝ ከሚቀበልባቸው ሶስት መንገዶች መካከል አንዱ ነው። ደንበኞች በእጅ ስልኮቻቸው በሚጭኑት መተግበሪያ አሊያም ወደ 670 በመደወል አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ። እሺ ኤክስፕረስ የተሰማራበት ሥራ ለኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የተተወ፤ ለግሉ ዘርፍም የማይፈቀድ አድርጎ የማየት ዝንባሌ እንዳለ የሚናገሩት አቶ ጥጋቡ በገበያው ከፍ ያለ ፍላጎት መኖሩን ታዝበዋል።"ከክፍለ ሀገር ወደ አዲስ አበባ፤ ከአዲስ አበባ ወደ ክፍለ ሀገር ነው እንጂ ዕቃ የሚሔደው ከጎንደር ወደ አርባ ምንጭ የንግድ እንቅስቃሴ የለም። ይኸ መሆን ያልቻለው እንደ እኛ አይነት ይኸንን የንግድ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር የሚያደርጉ ድርጅቶች ወይም የጥቅል ዕቃ አድራሾች ስለሌሉ ነው" የሚሉት አቶ ጥጋቡ ይኸን ክፍተት ለመሙላት እሺ ወደ ሥራ እንደገባ አስረድተዋል።

Äthiopien Start-Up l Eshi Express
የእሺ ኤክስፕረስ ተባባሪ መሥራቾች ሐበን ገብሬ እና ጥጋቡ ኃይሌምስል Eshi Express

እሺ ኤክስፕረስ የሚያቀርበውን አገልግሎት "ማስለመዱ በጣም ከባድ ነው። ሥራው እምነት ይጠይቃል። ከዚህ በተጨማሪ አገልግሎቱን ካልሞከርከው ጠቀሜታውን አትረዳውም። የተጠቀሙ ሰዎች በጣም ደስተኛ ሆነው ለዘላቂው ይቆያሉ። ምንም ያልሞከሩ ሰዎች ደግሞ ሲሆኑ ለማስሞከር በጣም ከባድ ነው። ለዚህም ጥቅሙን አገልግሎቱን አይተው እንዲረዱ ለየትኛውም ሰው የመጀመሪያውን ትዕዛዝ በነጻ እናደርስ ነበር" የሚሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ባለፉት አራት አመታት ለውጥ ቢኖርም "አሁንም ገበያውን ዘልቀን ገብተናል፤ በጣም ሰው እየለመደ ነው ለማለት ያስቸግራል" ሲሉ ይናገራሉ።

በአሁኑ ወቅት የእሺ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት አቶ ጥጋቡ ኃይሌ የሕግ ምሩቅ ናቸው። የ26 ዓመት ወጣት ሳሉ ወደ 3 ሺሕ ገደማ የሙያ ማኅበራት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ አገር በቀል እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚያስተባብር ቢሮ በኃላፊነት መርተዋል። በሥራቸው ጥሩ ደሞዝ እና ዓለም አቀፍ ጉዞ የማድረግ ዕድል የነበራቸው አቶ ጥጋቡ የራሳቸውን ኩባንያ ለማቋቋም የደረሱበት ውሳኔ በቤተሰቦቻቸውም ሆነ በጓደኞቻቸው "ጤናማ" ተደርጎ እንዳልታየ ያስታውሳሉ።

እሺ የተመሠረተው የገበያውን ጉድለት ከታዘቡት ከአቶ ጥጋቡ የግል ቁጠባ በተጨማሪ በዝምድና በሚያውቋቸው እና በጋራ ቢዝነስ ስለመስራት ይነጋገሩ በነበሩ ግለሰቦች 1.3 ሚሊዮን ገደማ ብር ነው። አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ፣ በሥራው ለሚገጥሙት እንከኖች መፍትሔ ለመፈለግ ግፋ ሲልም አዳዲስ ደንበኞች ለማበጀት እሺ ኤክስፕረስ በቅርቡ ከተቋቋመው ከአዲስ አበባ ኤንጅልስ ኔትወርክ ድጋፍ አግኝቷል። አዲስ አበባ ኤንጅልስ ኔትወርክ በኢትዮጵያ ችግር ፈቺ ሐሳቦች ይዘው ብቅ በሚሉ ጀማሪ ኩባንያዎች ላይ ኢንቨስት የሚያደርግ በባለወረቶች የተቋቋመ ነው።

Video Still TV Magazin The 77 Percent
እሺ ኤክስፕረስ እስካሁን ሥራውን የሚያከናውነው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአዳማ እና በሐዋሳ ከተሞች ነው። ምስል DW

የእሺ ኤክስፕረስ አገልግሎት ቀስ በቀስ እየተለመደ ሲሔድ ሥራውን ለማሳደግ ገንዘብ ያስፈልገው ነበር። ኩባንያው የሚያሳየውን ለውጥ ከታዘቡ መካከል የአዲስ አበባ ኤንጅልስ ኔትወርክ ሰዎች ነበሩበት። "ከእነሱ ጋር በገነባንው ግንኙነት እና በነበረን ውይይት እሺ ላይ ኢንቨስት ቢያደርጉ ለእነሱም አዋጪ ነው ብለው ስላመኑበት የተወሰነ ገንዘብ ኢንቨስት ማድረግ ችለዋል" ሲሉ አቶ ጥጋቡ አዲስ አበባ ኤንጅልስ ኔትወርክ የእሺ ኤክስፕረስ ባለድርሻ መሆኑን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በቅጡ የሚሰራ የጎዳና ስያሜ እና የመኖሪያ ቤት አድራሻ በሌለበት አገልግሎት መስጠት ግን ለእሺ ሰራተኞች ሁልጊዜ ቀላል አይቀለም። ከደንበኛ የተላከን ጥቅል ለማድረስ ተቀባይን ፍለጋ ስልክ በተደጋጋሚ መደወል ወጪን ይጨምራል፤ ጊዜም ያባክናል። እሺ ኤክስፕረስ ይኸን ችግር ለማቃለል ከሌላ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጋር በመተባበር የራሱን መፍትሔ እያበጀ መሆኑን አቶ ጥጋቡ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። ጥቅሎች ተቀብለው ለደንበኞች ከሚያቀብሉ መደብሮች ጋር አብረው ለመሥራትም ጥረት እያደረጉ ነው። አቶ ጥጋቡ እሺ ኤክስፕረስ የሚያከናውነው "ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ትኩረት የሚሻ" የሥራ አይነት እንደሆነ ያምናሉ። ለእንዲህ አይነቱ ሥራ ክህሎት ያለው ግን ደግሞ በዝቅተኛ ደሞዝ ሊቀጠር የሚችል ባለሙያም ማግኘት ጀማሪውን ኩባንያ ይፈትነዋል።

"እንደ ጀማሪ ኩባንያ በጣም ጎበዝ ሰዎች ነገር ግን በትንሽ ደሞዝ ነው የምትፈልገው። እነዛን ሰዎች ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ብዙ ልታሰራቸው ትፈልጋለህ። ምክንያቱም ሥራው በጣም ብዙ ጥረት ይጠይቃል፤ የተለየ ክህሎት ይጠይቃል" ሲሉ እሺን የመሰሉ ጀማሪ ኩባንያዎች የሚገጥማቸውን ፈተና አቶ ጥጋቡ ያስረዳሉ። እሺ ኤክስፕረስን ለመሰሉ ጀማሪ ኩባንያዎች የሚሆን የመድን ዋስትና አለመኖር ሌላው አቶ ጥጋቡ የጠቀሱት ፈተና ነው። ይኸንን እሺ ኤክስፕረስ የራሱን ሥርዓት በማበጀት መፍትሔ ለመፍጠር ሙከራ አድርጓል። የኢትዮጵያ የታክስ ሥርዓት፣ የንግድ አሰራር ሒደት እና በመንግሥት ተቋማት ዘንድ ያለው ግንዛቤ ለጀማሪ ኩባንያዎች አመቺ አለመሆናቸውን የእሺ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ይጠቅሳሉ።

"ቢዝነስ በአንድ አገር ውስጥ ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት፤ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ መሣሪያ ሆኖ እያለ በተለያየ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ያለው እይታ ቢዝነስ ያለው ሰው ለራሱ የሚያስብ፤ አጭበርባሪ፤ እነሱ ደግሞ እየተቆጣጠሩ ያሉ የሚመስል በጣም የተሳሳተ አመለካከት በመኖሩ ማገዝ በሚኖርባቸው  ቦታ ላይ እንቅፋት እየሆኑ ያለህን የዕድል ፍጥነት ይፈታተነዋል" ሲሉ መዋቅራዊውን ፈተና ይገልጹታል።

Äthiopien Start-Up l Eshi Express
በቅጡ የሚሰራ የጎዳና ስያሜ እና የመኖሪያ ቤት አድራሻ በሌለበት አገልግሎት መስጠት ግን ለእሺ ሰራተኞች ሁልጊዜ ቀላል አይቀለም።ምስል Eshi Express

እሺ ኤክስፕረስ በአሁኑ ወቅት 27 የሙሉ ጊዜ ሰራተኞች አሉት። ከተቀጣሪዎቹ በተጨማሪ የራሳቸው ተሽከርካሪ አሊያም ሞተር ብስክሌት ያላቸው 18 ሰዎች ከኩባንያው ጋር በጋራ በመሥራት ላይ እንደሚገኙ አቶ ጥጋቡ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ኩባንያው በአንድ አመት ውስጥ በተለያዩ ክልሎች ወደ ሚገኙ ተጨማሪ ከተሞች ሥራውን ለማስፋፋት ጥረት በማድረግ ላይ ነው። እሺን መሰል ኩባንያዎች የኢትዮጵያን የንግድ ሥርዓት በማቀላጠፍ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪን የማስቀረት ላቅ ያለ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ የሚያምኑት አቶ ጥጋቡ ህልማቸው ከፍ ያለ ነው።

"በሺ የሚቆጠሩ ጥቅሎች ስናደርስ በሺ የሚቆጠር የሥራ ዕድል ለወጣቶች እንፈጥራለን ብለን እናስባለን። ለማህበረሰቡ ደግሞ የዕቃ ዋጋን በተቻለ አቅም በሚቀንስ መልኩ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎችን አዎንታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል ብለን እናስባለን" ሲሉ አቶ ጥጋቡ ይናገራሉ። ይኸን ዓላማ ለማሳካት "በአገር ውስጥ የተገነባ ጠንካራ ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል። አሁን ያለን ቴክኖሎጂ የተገደበ ነው። በሰፋ መልኩ ያንን አሻሽለን ቅድም ያልኩህን ነገሮች በሚያካትት መልኩ ለማስፈጸም ትልቅ ፍላጎት እና ዕቅድ አለን" ሲሉ አስረድተዋል።

አቶ ጥጋቡ ለአራት አመታት ሥራ ላይ የቆየው እሺ ኤክስፕረስ ትርፋማ እንዳልሆነ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። "ለተወሰነ አመታትም [ትርፋማ] ላይሆን ይችላል" የሚሉት አጥጋቡ ሥራው ብዙ ማስፋፊያ፣ ጥረት፣ ባለሙያ እና ገንዘብ የሚጠይቅ መሆኑን በምክንያትነት አቅርበዋል። በኩባንያው ሥራ እና ዕቅድ እምነት ከሚኖራቸው ግለሰቦችም ሆነ በቅርቡ በኢትዮጵያ ይቋቋማል ተብሎ ከሚጠበቀው የካፒታል ገበያ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ማሰባሰቡ እንደማይቀር አቶ ጥጋቡ ኃይሌ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ