1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለውኃ ዋጋ መስጠት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 14 2013

የዘንድሮው የዓለም የውኃ ቀን «ለውኃ ዋጋ መስጠት» በሚል መሪ ቃል ነው ትናንት በመላው ዓለም የታሰበው። በዕለቱ ለውኃ ሲባል ከሚከፈለው ገንዘብ በላይ ዋጋው የላቀ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በተለይ መላው ዓለም በወረርሽኝ በተጨነቀበት በዚህ ወቅት ሰዎች በተለያየ ስፍራ በቂ ውኃ አለማግኘታቸው ለበሽታ የመጋለጥ አጋጣሚውን እንዳያሰፋው ስጋት አለ።

https://p.dw.com/p/3r0sX
Taifun Vamco Philippinen 2020
ምስል Rouelle Umali/picture-alliance/Xinhua News Agency

የዓለም የውኃ ቀን ሲታሰብ

የተመድ በመጪዎቹ ዘጠኝና አስር ዓመታት ውስጥ ውኃና ተገቢው የንጽሕና መጠበቂያ ስልት ለሁሉም እንዲዳረስ በመንግሥታቱ ድርጅት ዘላቂነት ያለው የልማት ግብ እቅድ ይዟል። በተቃራኒው የውኃ እጥረት እየተባባሰ በመሄዱ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ በጎርጎሪዮሳዊው 2050 ዓ,ም የውኃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች እንደሚኖርም ተጠቁሟል። የውኃ እጥረቱን ካባባሱት ምክንያቶች ዋነኛው የውኃ አካላት መበከል መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የሮይተርስ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በብክለት ከተጎዱት የውኃ አካላት አንዱ በሳኦ ፖሎ ብራዚል የሚገኘው ቲተ ወንዝ አንዱ ነው። የብራዚል ትልቅ ከተማ በሆነችው ሳኦ ፖሎ የሚፈሰው ቲተ ወንዝ በየዕለቱ በብዙ መቶዎች ቶን የሚገመት የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ እና ቆሻሻ ይፈስበታል። በተመሳሳይ ባንዱንግ ኢንዶኔዢያ ውስጥ ያለው ሲታሩም የተሰኘው ወንዝ በቆሻሻ መሞላቱንም ሮይተርስ በፎቶ አስደግፎ ያመለክታል። በኢራቅ ናጃፍ ከተማ ያለው ኤፍራጥስ ወንዝም እንዲሁ በመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ ክፉኛ የተበከለ መሆኑን መረጃው ጠቁሟል።

በእርሻ ምርቶችም ሆነ በሰው የዕለት ከዕለት ኑሮ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለውን ውኃ አቅርቦት ለማስተካከል በአንዳንድ አካባቢዎች መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተለያዩ ጥረቶች እንደሚደረጉ በብሪታንያ ፖርትስማውዝ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢ ተፈጥሮና ልማት ጉዳይ ምሁር የሆኑት ዶክተር ጁሊያ ብራውን ይናገራሉ። ዶክተር ብራውን ምንም እንኳን እንዲህ ያለውን ጥረት ቢያደንቁም ድርጅቶቹ ውኃውን የማውጣት ሥራ አከናውነውና ፎቶ አንስተው ስለሚሄዱ ኅብረተሰቡ አስፈላጊውን ውኃ ለማግኘት ቧንቧዎቹን ለማደስም ሆነ በአግባቡ እንዲሠሩ ለማድረግ ኃላፊነቱ እንደሚተውለት፤ ይኽ ግን ብዙዎቹ ስለማይሳካላቸው ሁሌም በውኃ ችግር እንደሚሰቃዩ ያመለክታሉ።

ሞሪታንያ
ምስል Getty Images/AFP/A. Senna

በትናንትናው ዕለት የተመድ ይፋ ባደረገው መረጃ በመላው ዓለም 785 ሚሊየን የሚሆነው ሕዝብ መሠረታዊ የሚባለው የንጹሕ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት የለውም። በመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ መሠረትም ከአራት ዓመታት በኋላ ማለትም በጎርጎሪዮሳዊው 2025 ዓ,ም ከጠቅላላው የዓለም ሕዝብ ግማሹ የሚኖረው የውኃ እጥርት ባለባቸው አካባቢዎች ይሆናል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት አሚና መሐመድ በቀጣይ ያሰጋል የሚባለውን የውኃ አቅርቦት እጥረት አሁን ካለው ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተፅዕኖ ጋር በማያያዝ ተከታዩን ገልጸዋል።

«በ2040 ዓ,ም ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ከሚሆኑት አራት ልጆች አንዱ፤ 600 ሚሊየን የሚሆኑት  ማለት ነው እጅግ ከፍተኛ የውኃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ይሆናሉ። ኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዳስተማረን ውኃ እና የንጽህና መጠበቂያዎች ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ከሚያስፈልጉ ቁልፍ ነገሮች አንዱ መሆኑን አሳይቶናል። እንዲያም ሆኖ ዛሬም በተለይም በገጠርና ብዙም ባላደጉ ሃገራት የሚገኝ 3 ቢሊየን ሕዝብ መሠረታዊ ለሆነው እጅ መታጠብ እንኳ በቂ አቅርቦት በቤቱ የለውም።»

ማዳጋስካር
ምስል Laetitia Bezain/AP/picture alliance

ባለፈው ዓመት በወጣው መረጃ መሠረት የዓለም ሕዝብ ብዛት ከ7,7 ቢሊየን አልፏል። በአሁኑ ወቅት ዓለማችን ሦስት ቀውሶችን መጋፈጧ ነው የሚነገረው፤ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የብዝሃ ሕይወት ውድመት፣ እንዲሁም ብክለትና ቆሻሻ። የመንግሥታቱ ድርጅት የአካባቢ ተፈጥሮ መርሃግብር ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን እንደሚሉትም ይኽ ሁሉ ቀውስ ከባድ ጫናውን የሚያሳርፈው በወንዞች፣ በባሕር ውቅያኖሶችና በሐይቆች ላይ ነው። የዘርፉ ተመራማሪዎች ባካሄዱት ጥናት በ89 ሃገራት ውስጥ ካሉት 75 ሺሕ የውኃ አካላት ውስጥ ከ40 በመቶ የሚበልጠው የተበከለ መሆኑ ተደርሶበታል። በዚህም ምክንያት እስከ መጪዉ ዘጠኝ እና አስር ዓመት ዓለም ለተሸከመችው የሕዝብ ብዛት ደህንነቱ የተጠበቀ በቂ ውኃ ማቅረብ የሚሳካላት እንዳልሆነ እየተነገረ ነው። በዚያም ላይ የተመድ መረጃ እንደሚያመለክተው በመላው ዓለም ከ3 ቢሊየን የሚበልጠው ሕዝብ የሚጠቀምበትን ውኃ የተመለከተ በቂ መረጃ ባለመኖሩ ለበሽታ የተጋለጠ እንደሆነ ይገመታል።

የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝደንት የሆኑት ቱርካዊው ፖለቲከኛ ቮልካን ቦዚኪር በበኩላቸው ዓለም በኮሮና ወረርሽኝ በተጨነቀበት በዚህ ጊዜ ቢሊየኖች ተሐዋሲውን ለመከላከል እጃቸውን የሚታጠቡበት ውኃ ማግኘት እንዳልቻሉ ነው የተናገሩት።

«እውነታው በቢሊየኖች የሚቆጠረው ሕዝብ ራሱን ከወረርሽኙ ለመከላከል መሠረታዊ የሆነውን እጅ የመታጠቢያ ስልት አላገኘም። በዚህም ላይ በአንዳንድ በልማት ዝቅተኛ በሆኑ ሃገራት የሚገኙ የህክምና መስጫ ስፍራዎች የቧንቧ ውኃ የላቸውም። ይኽ ደግሞ በተለይ ውኃ በብዛት እያለንና የፈጠራ አቅሙም በዳበረበት በዚህ ዘመን ካለው እውነታ ጋር አብሮ አይሄድም። እንዲህ ያለው ዓይን ያወጣ መበላለጥ አንዳች ርምጃ እንድንወስድ ሊገፋን ይገባል።»

የውኃ ችግር በማዳጋስካር
ምስል Laetitia Bezain/AP photo/picture alliance

ሶማሊያ ውስጥ ከጠቅላላው ሕዝብ ሦስት አራተኛ የሚሆነው ቤተሰብ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ እንደማያገኝ ሕጻናት አድን የተባለው መቀመጫውን ብሪታንያ ያደረገው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ትናንት አስታውቋል። በምሥራቅ አፍሪቃ እየተጠናከረ የሄደው የአየር ንብረት ተፅዕኖ ፅንፍ የወጣ የአየር ጠባይን በማስከተሉ በአካባቢው የሚገኙት እንደ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ እና ኢትዮጵያ ያሉት ሃገራት ድርቅና ጎርፍ እየተፈራረቀባቸው መሆኑም ተገልጿል። እንዲህ ያለው አጋጣሚ ደግሞ ንጹሕ ውኃን የማግኘትን ዕድል ያመናምናል። በቅርቡ ሶማሊያ ውስጥ በሚገኙ 18 ወረዳዎች ውስጥ ባሉ ከ630 በሚበልጡ ቤተሰቦች ላይ የተካሄደው ቅኝት ባለፈው ዓመት በነበረው የዝናብ ወቅት 70 በመቶ የሚሆኑት ቤተሰቦች ምንም አይነት ንጹሕ ውኃ ማግኘት እንዳልቻሉ አሳይቷል።

ምሥራቅ አፍሪቃ ብቻም አይደለም ምዕራብ አፍሪቃም እንዲሁ የንጹሕ ውኃ አቅርቦት እጥረት እያሰቃየው መሆኑን የመንግሥታቱ የሕጻናት መርጃ ድርጅት UNICEF አመልክቷል። ድርጅቱ እንደሚለው 26,5 ሚሊየን የናይጀሪያ ሕጻናት በቂ ውኃ አያገኙም። ድርጅቱ የዓለም የውኃ ቀንን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ በመላው ዓለም 450 ሚሊየን ሕጻናት የውኃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች እንደሚኖሩ ጠቁሟል። ይኽም ማለት በዓለማችን ከአምስት ሕጻናት አንዱ በየዕለቱ ማግኘት የሚገባውን ያህል ውኃ አያገኝም። ከእነዚህ መካከልም 29 በመቶው የሚገኙት ናይጀሪያ ውስጥ ነው። በየዓመቱም በናይጀሪያ 100 ሺህ የሚሆኑ ልጆች ከውኃ ጋር በያያዙ በሽታዎች ይሞታሉ። ጎርፍ በሚከሰትበት ጊዜም በውኃ ወለድ በሽታዎች ግንባር ቀደም ተጎጂዎች እነሱው ናቸው። ውኃ ሲጠፋም እጃቸውን ለመታጠብ ዕድሉ ስለማይኖራቸው ለበሽታዎች የተጋለጡ ሆነዋል።

ቬንዝዌላ
ምስል Miguel Gutierrez/Agencia EFE/imago images

ይኽ በናይጀሪያ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያም ውስጥም ሆነ መሰል የንጹሕ ውኃ አቅርቦት እጥረት ባለባቸው ሃገራት የሚታይ እውነታ ነው። በአንጻሩ በአንዳንድ ሃገራት የሚገኙ ግዙፍ የውኃ አካላት ደግሞ ለብክለት ተዳርገዋል። በአፍሪቃ በትልቅነቱ ቀዳሚ የሆነውና ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ኬንያን የሚያዋስነው ቪክቶሪያ ሐይቅ ለከፍተኛ ብክለት ከተጋለጡት አንዱ ነው። ሐይቁ በአረም መወረሩ ሳያንሰው በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ እንዲሁም በብክለት መዘዝ ውኃው ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ። በኢትዮጵያም እንዲሁ ጣና ሐይቅ ብቻ ሳይሆን አሉ የሚባሉት ሌሎች በስምጥ ሸለቆ የሚገኙ ትላልቅ የውኃ አካላትም እንዲሁም በአረም መዋጣቸው ስጋት ሆኖ መነገር ከጀመረ ከርሟል።

ሌላው ትናንት የታሰበውን የዓለም የውኃ ቀን አስመልክቶ ከወጡ መረጃዎች አንዱ የአፍሪቃ ሃገራት በቅኝ ግዛት ዘመን የተደረጉ የውኃ ስምምነቶችን መጠቀም እንዲያቆሙ የሚያሳስበው መጣጥፍ ይገኝበታል። የዶቼ ቬለዋ ሀሪሰን ማውሪማ በጻፈችው አስተያየት የአፍሪቃ ሃገራት ያላቸውን የውኃ ሃብት ለመጋራት የቅኝ ግዛት ዘመንን ውል ከሚያነሱ ተባብረው በአህጉሪቱ በውኃ ምክንያት የተጋረጠውን ቀውስ ቢፈቱ እንደሚበጅ መክራለች። ጸሐፊዋ እንደምትለው ቅኝ ገዢ ኃይሎች ሰው ሠራሽ ድንበር በፈጠሩበት ጊዜ በየሃገራቱ ውስጥ የሚገኙ ወንዞችና ሐይቆችን የተፈጥሮ ድንበሮች ለማድረግ ሞክረዋል። የውኃ አካሉን ከአንድ በላይ ሃገራት የሚጋሩት ሲሆንም ሕዝቡን ሳያናግሩ የራሳቸውን የአጠቃቀም ውል ነድፈዋል። የቅኝ ግዛት ዘመን ሲያከትምም የአፍሪቃ ሃገራት በሌሎች የተሠመሩትን ድንበሮች እንዳሉ ወረሱ። አሁን ታዲያ በሃገራት መካከል የተፈጥሮ ሀብትን የተመለከተ የይገባኛል ውዝግብና ውጥረትን አስከተለ። በተለይ ውኃን የተመለከተው የቀድሞ ቅኝ ገዢ ኃይሎች ያዘጋጁት ውል አንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራት የራሳቸውን ጥቅም ማስከበሪያ መሣሪያ ሆኖ ይቀርባል። በ11 ሃገራት ውስጥ የሚፈሰው የአፍሪቃ ረዥሙ ወንዝ አባይ በቅርቡ ውጥረት ያስከተለ የውዝግብ መንስኤ ሆኗል። የወንዙ ተጠቃሚ የሆኑት ግብፅና ሱዳን በቀድሞ ቅኝ ገዢ ብሪታንያ የዘጋጀው ስምምነት እንዲጸና ይመኛሉ። ስምምነቱ ለሁለቱ ሃገራት ጠቀም ያለ የውኃ ፍሰት በመመደብ ግብፅ በወንዙ ላይ የሚሠራ ማንኛውንም ፕሮጀክት ድምፅን በድምፅ በመሻር ሚና እንዲኖራት ኃይል ይሰጣል። ኢትዮጵያ ከ11 ዓመታት በፊት በአባይ ወንዝ ላይ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ታላቅ ግድብ ለመገንባት መነሳቷን ይፋ አደረገች። ባለፈው ዓመት ክረምት ኢትዮጵያ ግድቡን በውኃ ለመሙላት ስትጀምር ግብጽ ተቃውሞዋን በማጠናከር የቅኝ ግዛት ዘመኑ ውልም እንዲጸናላት አጥብቃ መወትወቷን ቀጠለች። ኢትዮጵያም በአባይ የመጠቀም መብቷ እንዲጠበቅ ትሞግታለች። ቅኝ ገዢዎች አፍሪቃ ውስጥ የደነገጉት መሰል ውል ታንዛኒያና ማላዊንም እያወዛገበ ነው። ታንዛኒያውያን ናያሳ፤ ማላዊያን ደግሞ የማላዊ ሐይቅ በሚሉት ሁለቱ ሃገራት ሲነታረኩ ዓመታት ነጉደዋል። እዚህም ብሪታንያ ያዘጋጀችው ውል ማላዊ የሐይቁ ዋነኛ ተጠቃሚ እንድትሆን ያመቻቸ ነው። በአንጻሩ ታንዛኒያ ዓለም አቀፍ ሕግ ይታይልኝ እያለች ነው። የቅኝ ገዢዎችን ወደ አንድ ወገን ያደላ ውል ይዞ መሟገቱ የአፍሪቃ ሃገራት ላለባቸው የውኃ አቅርቦት ችግር መፍትሄ ስለማይሆን ጸሐፊዋ እንዲህ ያሉትን ውዝግቦች ለመፍታት የአፍሪቃ መንግሥታት በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልጋቸው ምክሯን ለግሳለች።

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ
ምስል DW/Negassa Desalegen

 ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ