1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እርዳታ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 6 2012

ኮቪድ 19 በአውሮጳ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ማጥፋት ሲጀምር ነበር 6 በጄኔቫ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እኛስ ለወገኖቻችን ምን እናድርግ ብለው መነጋገር የጀመሩት።በጀርመን በኖርድ ራይን ቬስትፈለን ፌደራዊ ግዛት የነጃሺ ሙስሊም ማህበር በኩልም በራስ ተነሳሽነት የተለያዩ ማህበራትና በጎ አድራጊዎች የተሳተፉበት የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ እየተካሄደ ነው።

https://p.dw.com/p/3au1V
Stadtansicht von Genf mit der Fontaine im Vordergrund
ምስል dapd

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እርዳታ

ከ200 በላይ ሃገራት ውስጥ በተዛመተው በኮሮና ተህዋሲ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እያሻበቀ ነው።የአሜሪካኑ ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ዛሬ እንዳስታወቀው በዓለማችን በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ነጥብ 9 ሚሊዮን ሲበልጥ የሞቱት ቁጥር ደግሞ ከ120 ሺህ በላይ ሆኗል። የኮሮና ተህዋሲ ሕይወት ከመቅጠፍ ባሻገር እንቅስቃሴን ገድቦ የዓለምን ኤኮኖሚ አናግቷል፤ማህበራዊ ግንኙነቶችን ቀንሷል።በተህዋሲው ሰበብ በርካቶች ሥራ አጥ ሆነዋል።መንግሥታት በጣሉት የእንቅስቃሴ እገዳ በተለይ ኑሮአቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆነ የህብረተሰብ ክፍሎች ይበልጡን እየተጎዱ ነው።ምንም እንኳን በኢትዮጵያ በበሽታው የተያዘው ቁጥር ብዙ ባይሆንም በሽታው ቢስፋፋ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች በበሽታው ብቻ ሳይሆን በሚያስከትላቸው ተጽእኖዎች ችግር ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም። በዚህ መነሻነት መንግሥት ባቀረበው ጥሪ ልዩ ልዩ መስሪያ ቤቶች ድርጅቶች እና የህብረተሰብ ክፍሎች ከወዲሁ ለሚከናወኑ ቅድመ ዝግጅቶች ድጋፍ እየሰጡ ነው።በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በየሚኖሩባቸው ሃገራት ገንዘብ በማሰባሰብ ወደ ሀገራቸው እየላኩ ነው፤በዝግጅት ላይ የሚገኙም አሉ ።በተለያዩ ሃገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በኩል መከናወን ከጀመሩት የእርዳታ ማሰባሰቢያ ስራዎች በተጨማሪ በራሳቸው ተነሳሽነት ማህበራት እና በበጎ ፈቃድ ለዚሁ ዓላማ የተሰባሰቡ ግለሰቦች በየአካባቢያቸው ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የእርዳታ ጥሪ በማስተላለፍ የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣት ላይ ናቸው።ከመካከላቸው ስዊዘርላንድ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ ተጠቃሽ ነው። ኮቪድ 19 በአውሮጳ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ማጥፋት ሲጀምር ነበር 6 በጄኔቫ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እኛስ ለወገኖቻችን ምን እናድርግ ብለው መነጋገር የጀመሩት።ሃሳባቸውንም ለሌሎች አጋርተው ፣በጎ ዓላማቸው ተቀባይነት አግኝቶ የእርዳታ ገንዘብ አሰባስበው ወደ ሃገራቸው ልከዋል። አቶ ጆቴ ይማም ከአስተባባሪዎቹ አንዱ ናቸው።
እንደ «ኮቪድ 19 ኢትዮ ስዊዝ ድጋፍ አሰባሳቢ» ሁሉ በጀርመን በኖርድ ራይን ቬስትፈለን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት የነጃሺ ሙስሊም ማህበር በኩልም በራስ ተነሳሽነት የተለያዩ ማህበራት እና በጎ አድራጊ ግለሰቦችን ያሳተፈ የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ እየተካሄደ ነው።አስተባባሪው አቶ መሀመድ አብደላ ለዶቼቬለ በስልክ እንደተናገሩት የእርዳታው ሃሳብ የተጠነሰሰው ኮቪድ 19 በአውሮጳ እና በአሜሪካ ከባድ ጥፋት ማድረስ ከጀመረበት ጊዜ ነው። ለኢትዮጵያውያን ለቀረበው የእርዳታ ጥሪ የተገኘው ምላሽም ከጠበቁት በላይ ነበር። 
ለእርዳታው ጥሪ የተሰጠው ምላሽ እርሳቸው በሚገኙበት አካባቢ ያሉ ኢትዮጵያውያንን አንድነት ያሳየም ነበር እንደ አቶ መሐመድ።
በተለያዩ የውጭ ሃገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች አስተባባሪነትም ከኢትዮጵያውያን ልዩ ልዩ ድጋፎች እየተሰበሰቡ ነው። የ«ኮቪድ 19 ኢትዮ ስዊዝ ድጋፍ አሰባሳቢ» አባል አቶ ጆቴ እንደተናገሩት እነርሱ ገንዘብ ማሰባሰብ የጀመሩት በኤምባሲ በኩል ጥሪ ከመተላለፉ አስቀድሞ በመሆኑ በዚያ ውስጥ ባይሳተፉም በሚኖሩበት በስዊዘርላንድ ከሚገኘው ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር መረጃዎችን ይለዋወጣሉ።በነጋሺ ሙስሊም ማህበር በኩልም ገንዘብ ማሰባሰብ የተጀመረው ከኤምባሲ የእርዳታ ጥሪ ከመቅረቡ አስቀድሞ ነው።በዚህ ምክንያትም ለአሁኑ የገንዘብ እርዳታውን በእቅዳቸው መሰረት ለመላክ ነው የተዘጋጁት።ድጋፉ በዚህ ብቻ እንደማይወሰን የተናገሩት አስተባባሪው አቶ መሐመድ ወደፊት ከኤምባሲ ጋር ተባብሮ የመስራት እቅድ እንዳላቸው አስረድተዋል።የኮሮና ተህዋሲ በኢትዮጲያ ሊያስከትል ለሚችለው ችግር ከወዲሁ ለሚደረገው ዝግጅት ድጋፍ ያደረጉት የ«ኮቪድ 19 ኢትዮ ስዊዝ ድጋፍ አሰባሳቢ»ም ሆነ በጀርመን ኖርድ ራይን ቬስትፋለን  የነጃሲ ሙስሊም ማህበር፣ ሌሎች በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የነርሱን ፈለግ በመከተል ጊዜ ለማይሰጠው ለወገን ችግር በአፋጣኝ እንዲደርሱ አቶ መሐመድ አብደላ ጥሪ አቅርበዋል።አቶ ጆቴ ይማም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ልዩነታችንን ወደ ጎን በመተው በተለያዩ መንገዶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። 

Äthiopien Coronavirus
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Ayene

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ