1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኦሮሚያ ክልል ቀውስ የሰላም መፍትሄ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 19 2015

ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ላለፉት አራት ዓመታት ገደማ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ስር ሰዶ የቆየው የሰላምና መረጋጋት እጦት ለበርካታ ዜጎች ሕይወት መቀጠፍ እና መፈናቀል ሰበብ ሆኗል ። አሁንም ድረስ ግን ችግሩ ሙሉ በሙሉ አለመቀረፉ ይነገራል ።

https://p.dw.com/p/4POXO
Äthiopien Parlament Addis Abeba
ምስል Solomon Muche/DW

«ከማንም በላይ የከፋው የአከባቢው ማኅበረሰብ ሰቆቃ ነው»

ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ላለፉት አራት ዓመታት ገደማ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ስር ሰዶ የቆየው የሰላምና መረጋጋት እጦት ለበርካታ ዜጎች ሕይወት መቀጠፍ እና መፈናቀል ሰበብ ሆኗል ።  አሁንም ድረስ ግን ችግሩ ሙሉ በሙሉ አለመቀረፉ ይነገራል ። በዚሁ የፀጥታ ችግር የተፈተኑ ነዋሪዎችም እና ለችግሩ የሰላም መፍትሄ ያሻዋል ያሉ የተለያዩ የማኅበረሰብ አካላት በተደጋጋሚ ምሬታቸውን ሲገልጹና ጥሪም ሲያቀርቡ ይደመጣል ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህምድ ዛሬ ለህ/ተ/ም/ቤት በተለያዩ ሃሳቦች ማብራሪያ ሲሰጡ «ሸኔ» ያሉት በኦሮሚያ ነፍጥ አንግቦ ከሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ጋር ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግስታቸው ኮሚቴ አዋቅሮ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመለክተዋል ። አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ባለሞያ ኦሮሚያ ውስጥ ስር ሰዶ ለአራት ዓመታት ገደማ ሲካሄድ የነበረውን ውስብስብ ባህሪ የያዘን ቀውስ ለመፍታት ጊዜ ያሻዋል ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ። 

ውልደትና እድገታቸው በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ የሆነው አንድ የአከባቢው ተወላጅ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ወደ አከባቢው አምርተው ከቤተሰባቸው ጋር ከተገናኙ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በተለይም በአራቱ የወለጋ ዞኖች ስር ሰዶ በቅርብ ጊዜያት ለነዋሪው የአስከፊ ህይወት ጋረጣን የደቀነው ግጭት ዓመት በዓመታት ብተኩም ከተስፋ ውጪ ቢያንስ እስከ ዛሬዋ ቀን ይህ ነው የሚባል ተጨማጭ እልባት አልተስተዋለም፡፡ እኚህው አስተያየት ሰጪ እንደሚሉትም እልባት አልባ ሆኖ እየቀጠለ ባለው አለመረጋጋት ከማንም በላይ የከፋው የአከባቢው ማህበረሰብ ሰቆቃ ነው፡፡

ጎጆ ቤቶች በኦሮሚያ ክልል፦ ፎቶ ከማኅደር
ጎጆ ቤቶች በኦሮሚያ ክልል፦ ፎቶ ከማኅደርምስል Fischer/Bildagentur-online/picture alliance

“ታውቃለህ ከቀን ቀን ነገሩ እተወሳሰበ ነው እዚህ የደረሰው፡፡ ለጥቅሙ በዚያ ውስጥ የሚሳተፍ ይኖራል፤ የፖለቲካ ዓለማ ያነገበም ይኖራል፡፡ በዚህ መሃል ትልቅ መስዋዕትነት እየከፈለ ያለው ሰላማዊው ማህበረሰቡ ነው፡፡ ወጥቶ አምርቶ መጠቀም መከራ ሆኗል፡፡ ያ ህዝብ እያለፈበት ያለው መከራ እንዲሁ በቃል ሚገለጽ አይደለም፡፡ ሰው እኮ እንደ ድሮው ተመልሶ ድንጋይን ከድንጋ ጋር እያፋጨ ነው እህል ፈጭቶ ሚመገበው፡፡ እንዴትም ይሆን በየት ሰው አሁን የሚፈልገው ቀዳሚው ነገር ሰላም ነው፡፡ በጉልበተኛ ከብቶቹንም ጭምር መዘረፍ መሮታል ህዝቡ፡፡ ህብረተሰቡ እንደአሙሩና ጃርደጋ ጃርቴ ካሉ ከ100 ኪ.ሜ. በላይ ርቀት ካላቸው አከባቢዎች የዞን ከተማ ሻምቡ በእግር ሄደው ነው 10ም ትሁን 100 ብር እንኳ ጥሬ ገንዘብ ማግኘት የሚቻለው፡፡ የራስህን ብር እንኳ ለማግኘት ዋጋ ትከፍላለህ ማለት፡፡”

በኦሮሚያ እንደነዚህ ያሉትን የከፋ ማህበራዊ ቀውስ እያስከተሉ የሚገኙትን ግጭት አለመረጋጋቱን በሰላማዊ መንግድ ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዛሬው እለት ለህ/ተ/ም/ቤት በሰጡት ማብራሪያ አረጋግጠዋል፡፡ ለሰላሙ የመንግስታቸውን ቁርጠኝነት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች ተስፋ ሰጪ እምርታ ላይ የደረሰው የሰላም ድርድሮች በኦሮሚያም እውን እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ ከሚጠራው እና መንግስት ሸነ ከሚለው ታጣቂ ቡድን ጋር ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከ10 ጊዜ ያላነሰ ሙከራ ተደርጓል፡፡ “ነገር ግን ቡድኑ ውስጥ ያሉ ሰዎች የተለያየ ሃሳብ ይዘው ስለሚመጡ መሳካት አልቻለም፡፡ የሆነ ሆኖ የኦሮሚያ ክልልም ባለፈው ያቀረበው ጥሪ እንደ እንደ ፓርቲም የተነጋገርንበትና የተስማማንበት ነው፡፡ በርካቶችን እየጎዳ እያፈናቀለ ያለውን ይህን ግጭት ለማስቆም የሚረዳን ሰላም የሚጠላም ኢትዮጵያዊ አለ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ጉዳዩ በሰላም እንዲፈታ አበክረን እየሰራን ተጨማሪ መፈናቀለም እንዳይከሰት የፀጥታ ሃይል ስመምሪት አድርገናል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎት ከማንም ጋር የሚፈልገው ጉዳዮችን ወደ ምክክር ማምጣት ነው፡፡ ይ የሸነ ጉዳይም በተመለከተ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተንቀሳቀሰ ስለሆነ ውጤቱን በጋራ የሚናይ ይሆናል” ብለዋል፡፡

መልክአ ምድር በኦሮሚያ ክልል፦ ፎቶ ከማኅደር
መልክአ ምድር በኦሮሚያ ክልል፦ ፎቶ ከማኅደርምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

የኦሮሚያውን ግጭት በሰላም የመፍታት ጥረቶች ከንግግር የዘለለ ወደ ተግባር ለመግባቱ ምልክቶች አልታዩም በሚል ጥርጣሬያቸውን የሚገልጹ አካላት አሉ፡፡ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሰለሞን ተፈራ ግን በዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ጊዜው ገና ነው ይላሉ፡፡ “በአንድ አገር ውስጥ የሚካሄድን የእርሰበርስ ጦርነት ለመፍታ ነገሮች ቀላል አይሆኑም፡፡ ጊዜ መግዛትን ይሻሉ፡፡ ከግጭቱ ጀርባ ፍላጎታቸውን የሚያራምዱ አካላት አለመትፋታቸው በራሱ የሽምግልና ሂደቶችን ፈታኝ ያደርገዋል፡፡”
ባለሙያው እንደሚሉት በቀጣይም ተፈላጊውን ዘለቄታ ያለውን ሰላም ለማምጣትም የሁለቱም ወገኖች ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ “ከአደራዳሪነትም ምርጫ በላይ ማንም ያደራድር ማን የሁለቱ አካላት ቁርጠኝነት ለዘላቂ ሰላም ሚናው የላቀ ነው፡፡”

በቅርቡ ከኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ አከባቢ የተወከሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴዎች የኦሮሚያውን ግጭት እንዲያሸማግል ለአፍሪቃ ኅብረት ጥያቄ አቅርበው ለተለያዩ አካላትም ጥሪ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡  

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር