1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የተ.መ.ድ. 65 ሚሊዮን ዶላር ሰጠ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 29 2013

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከለቀቀው ገንዘብ 40 ሚሊዮን ዶላር በትግራይ አስቸኳይ መጠለያ፣ ንጹህ ውኃ እና የጤና አገልግሎት ለማቅረብ፤ ወሲባዊ እና ጾታዊ ኹከትን ለመከላከል እንዲሁም የተቀረው 25 ሚሊዮን ዶላር በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሚከናወኑ ሰብዓዊ ሥራዎች የሚውል ነው።

https://p.dw.com/p/3t5Z0
UN Nothilfe Mark Lowcock
ምስል Fabrice Coffrini/AFP/Getty Images

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ 65 ሚሊዮን ዶላር መልቀቁን አስታወቀ። በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UNOCHA) ትናንት ሐሙስ ባወጣው መግለጫ እንዳለው ከገንዘቡ 40 ሚሊዮን ዶላር በትግራይ አስቸኳይ መጠለያ፣ ንጹህ ውኃ እና የጤና አገልግሎት ለማቅረብ፤ ወሲባዊ እና ጾታዊ ኹከትን ለመከላከል እና ለሰብዓዊ ምላሽ የቴሌኮምዩንኬሽን ድጋፍ ለማድረግ የታቀደ ነው።

ድርጅቱ እንዳለው በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 16 ሚሊዮን ሰዎች ሰብዓዊ ዕገዛ የሚፈልጉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 4.5 ሚሊዮን የሚገመቱት በትግራይ ክልል የሚገኙ ናቸው።

በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ዕርዳታ ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ “የኢትዮጵያውያን ሕይወት እና አኗኗር በድርቅ እየወደመ ነው። ሕፃናት በተመጣጠነ ምግብ እጦት እየተሰቃዩ ነው” ብለዋል።

ኃላፊው “ስድስት ወራት ባስቆጠረው የትግራይ ግጭት ሰላማዊ ሰዎች የገፈቱ ተሸካሚ ሆነው ቀጥለዋል። ሴቶች እና ልጃገረዶች የአሰቃቂ ወሲባዊ ጥቃት ዒላማ ሆነዋል። ሚሊዮኖች በተለይ ሙሉ በሙሉ ግንኙነታቸው በተቋረጠ ገጠራማ አካባቢዎች መሠረታዊ ግልጋሎቶች እና ምግብ ለማግኘት እየተቸገሩ ነው። የሰብዓዊ ምላሽ አሰጣጡን አሁኑኑ ማሳደግ አለብን” የሚል ጥሪ አቅርበዋል። 

በትግራይ ዕርዳታ የሚሹ ዜጎች ጋ መድረስ አሁንም ፈታኝ መሆኑን የጠቆመው በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የዕርዳታ ሰራተኞች ፈተናዎቹን ለመወጣት እና ከዚህ ቀደም መድረስ ያልተቻሉ በደቡብ ምሥራቅ ዞን የሚገኙትን ለማገዝ ከባለስልጣናቱ ጋር ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው ብሏል።

ባለፈው ሳምንት የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ሳምረ ወደ ተባለችው ከተማ አስቸኳይ ምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ማድረሳቸውን እንዲሁም በከተማው በሚገኝ ሆስፒታል ተንቀሳቃሽ የጤና ክሊኒክ ሥራ ማስጀመራቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

"በትግራይ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሁንም ተለዋዋጭ ነው። የዕርዳታ ሰራተኞች ዕገዛ የሚፈልጉ ሰዎች ጋ መድረስ አልቻሉም" ያለው ድርጅቱ በመቐለ ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል በኮቪድ-19 የተያዙ መኖራቸው ሪፖርት መደረጉንም አትቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከለቀቀው ገንዘብ 25 ሚሊዮን ዶላር በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሚከናወኑ ሰብዓዊ ሥራዎች የሚውል ነው። ከእነዚህ መካከል በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች ድርቅ ላስከተለው ተጽዕኖ የሚቀርብ ዕርዳታ ይገኝበታል።

ገንዘቡ "የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጦት የገጠማቸውን ሕፃናት ለማከም፣ የውኃ ማቅረቢያዎችን እንዲያገግሙ ለማድረግ፣ በድርቅ ለተጠቁ ማኅበረሰቦች ውኃ ለማቅረብ እና የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ሕይወት አድን አቅርቦቶችን አስቀድመው እንዲያከማቹ ለማድረግ ይውላል" ተብሏል።