1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኢትዮጵያ ቅርሶች እዉቅና የታገሉት ምሁር ሲታወሱ

ሐሙስ፣ ጥር 14 2012

ኢትዮጵያ ዉስጥ የጥምቀት በዓል እንዴት እንደመጣ፤ አከባበሩ፤ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ምን አይነት መልክ እንደነበረዉ ሁሉ ይናገር ነበር። ጥምቀት በዓል ብዙዎችን ያስተሳስራል፤ አንድነት ይፈጥራል፤ የፆታ ልዩነት የለዉም፤ በፍቅር በማስተሳሰር፤ የሰዉ ልጆች እሴቶች በዓል ነዉ እያለ የጥምቀት በዓል እንዲመዘገብ ከብዙ ዓመታት ጀምሮ ጥረት ሲያደርግ ነበር።

https://p.dw.com/p/3Wiqt
Äthiopien Hailemelekot Agizew
ምስል DW/T. Belete

የቅርስ ጥበቃ ጉዳይ ከፍተኛ ተመራማሪ ኃይለመለኮት አግዘዉ

በዓለም የቅርስ መዝገብ የሰፈረዉ የጥምቀት በዓል ዘንድሮ በደመቀ ሁኔታ ተከብረዋል። ምንም እንኳ የጥምቀት በዓል አከባበር ማዕከል በሆነችዉ ጎንደር በበዓሉ ወቅት አደጋ ቢከሰትም፤ በምዕራብ ኢትዮጵያም አንዳንድ አካባቢዎች ግጭት ቢታይም የዘንድሮ የጥምቀት በዓል በሃገር ዉስጥም ሆነ በዓለም ዙርያ ባሉ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ በድምቀት ነዉ የተከበረዉ።

በዓለም የቅርስ መዝገብ የሰፈረዉ የጥምቀት በዓል ዘንድሮ በደመቀ ሁኔታ ተከብረዋል። ምንም እንኳ የጥምቀት በዓል አከባበር ማዕከል በሆነችዉ ጎንደር በበዓሉ አከባበር ወቅት አደጋ ቢከሰትም፤ በምዕራብ ኢትዮጵያም አንዳንድ አካባቢዎች ግጭት ቢታይም የዘንድሮ የጥምቀት በዓል በሃገር ዉስጥም ሆነ በዓለም ዙርያ ባሉ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ በድምቀት ነዉ የተከበረዉ። የጥምቀት ክብረ በዓል፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምሕርት፥ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም «ዩኔስኮ» የዓለም የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ከተመዘገበ ዓመት ሆነዉ። ሃይማኖታዊ ማኅበረሰባዊ ባህላዊ ክብረ በዓል በዩኔስኮ እንዲመዘገብ የአንበሳዉን ድርሻ የያዘዉ የታሪክ የቋንቋ ባለሞያና የቅርስ ጥበቃ ጉዳይ ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ኃይለመለኮት አግዘዉ ነዉ። አቶ ኃይለመለኮት አግዘዉ ለወራቶች ታሞ ባለፈዉ ዓመት መጨረሻ ጳጉሜ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ተለይቶአል። ይሁንና ለአገሩ ያበረከተዉ ከፍተኛ አስተዋፆ ህያዉ አድርጎታል። አቶ ኃይለመለኮት አግዘዉ በአዲስ አበባ ሙዚየም የኤግዚቢሽን አስተባባሪ፣ የትምህርት ኦፊሰር እና ዳይሬክተር፣ በኢኳቶሪያል ቢዝነስ ግሩፕ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ፣ በኢትዮዽያ ፕሬስ ድርጅት የ “Ethiopian Herald” ጋዜጣ አዘጋጅ፣ በኢትዮዽያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለ ስልጣን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ከፍተኛ ባለሙያ በመሆንም አገልግሏል። የ «DW» የዶቼ ቬሌ የረጅም ዓመታት አድማጭ በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ቅርስ እና ታሪክን በተመለከተ ለዓመታቶች ተሳታፊም ነበር። የዘመን አቆጣጠር መምህርና ጋዜጠኛ ሄኖክ ያሬድ ፈንታ አቶ ኃይለመለኮት እንደ ስሙ ኃይለ ቅርሳችን ነዉ ይላል።

Ägypten Epiphanie Feier in Gondar
ምስል Reuters/T. Negeri

«ኃይለመለኮት ከስሙ በመነሳት ኃይለ ቅርስ እለዋለሁ። አንደኛ የታሪክ ባለሞያ ነዉ። ሁለተኛ ከቅርስ ጋር በተያያዘ ፤ እስከ ድህረ ምረቃ ድህረ ትምህርቱን ያጠናቀቀ፤ በቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዉስጥ ለረጅም ዘመናት ያገለገለ ነዉ። በአንድ በኩልም “Ethiopian Herald” ላይ ጋዜጠኛ ሆኖ ይፅፍ ነበር። በተለይ በኢትዮጵያ ማንነት በኢትዮጵያ መገለጫ ጋር የሚያያዙ ተፈጥሮዋዊ እና ሰዉ ሰራሽ ቅርሶችን በተመለከተ እጅግ የሚቆረቆር ነዉ ለዚህ ነዉ ኃይለ ቅርስ ያልኩት። በተያያዘ በተለይ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለስልጣን፤ የዓለም ቅርስ ምዝገባ የወካይ ቅርስ ምዝገባ ተብሎ በሚካሄደዉ እንቅስቃሴ ላይ እንደ አንድ ባለሞያ አስተዋፆ ሲያደርግ እንደነበረም አዉቃለሁ። በተለይ በዉጭ ቋንቋ ሰነዶችን በማዘጋጀት ከባለስልጣኑ ባለሞያዎች ጋር አንድ ላይ ሆኖ ትልቅ ስራ መስራቱን አዉቃለሁ። በዩኔስኮ ለተመዘገቡት ቅርሶች ረገድ እዉቅናም ተሰቶታል። በኢትዮጵያ ሚሌንየም አካባቢ የኢትዮጵያ የቅርስ ባላደራ ማኅበር፤ በተለይ አዲስ አበባ ዉስጥ ብዙ ቅርሶች እየፈረሱ ሲመጡ፤ ትልልቅ ጉባዔዎች ይካሄዱ ነበር። ከቅርሶቻችን ጋር ጦርነት መክፈት የለብንም ። አሻራዎቻችንን መያዝ አለብን። እነዚህን አሻራዎቻችንን ካልጠበቅን፤ መጭዉ ትዉልድ እንዴት ማንነቱን ሊረዳ ይችላል? በሚለዉ ላይ አንዱ ተሟጋች እሱ ነበር። ለምሳሌ የለገሃር ባቡር ጣብያ ሕንፃ ይፈርሳል በተባለበት ጊዜ የቅርስ ባላደራ ማኅበር ባዘጋጀዉ መድረክ ላይ፤ ሽንጡን ገትሮ ሲከራከር የነበረ ነዉ። ለምን ሌላ አማራጭ አይደረግም በሚል ሃሳብ ያነሳዉም አንዱ ኃይለመለኮት ነበር። መናገር ብቻ ሳይሆን በጽሑፍም በማስተዋወቅ ተጠቃሽ ነዉ።

Äthiopien Hailemelekot Agizew
ምስል DW/T. Belete

ለኢትዮጵያዉያን ኩራት የሆነዉ ጥምቀት ክብረ በዓል፤ አሁን በዓለም መድረክ የታወቀ ሆንዋል በዚህም ኃይለመለኮትን እናወድስ ያለዉ፤ የአሃዱ ሬድዮ እና ቴሌቭዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፤ ኃይለመለኮት አግዘዉ በሚጽፋቸዉ ጽሑፎች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምሕርት፥ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም ላይ ትልቅ ተጽኖ ያሳረፈ ምሁር ነበር፤ ብሎአል።  

አቶ ኃይለመለኮት የኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛዎችም ሆነ የህትመት ሚዲያዉ የኢትዮጵያ ቅርስ ይዞታና ጥበቃን በተመለከተ ቅርስ እንዲጠበቅ ለማኅበረሰቡ በቂ ግንዛቤና መረጃን አይሰጥም ሲል ይወተዉት ነበር ሲል የሚያስታዉሰዉ ጋዜጠኛ ሄኖክ ያሬድ ፈንታ፤ የኦሮሞ ገዳ ሥርዓቶች እና በጌዲዮ ዉስጥ ያሉ፤ የኮንሶ አካባቢን የመጠበቅ ስርዓት ሁሉ እየዞረ ጥናት ያደርግ ነበር። ጎበዝ እንጊሊዘኛ ቋንቋ ፀሐፊ ነዉ። ለልዩ ልዩ ተቋማት በዩኔስኮ ላይ ተፅኖ ሊፈጥሩ ለሚችሉት ይፅፍላቸዉ ነበር። ይሄ መደበኛ ከሆነዉ የመንግሥት አሰራር ዉጭ፤ ተፅኖ ሊፈጥሩ ይችላሉ እዉቀት ሊኖራቸዉ ይገባል፤ ብሎ ለሚያያምናቸዉ ሁሉ ይፅፍ ነበር፤ ይልክላቸዉም ነበር።  ጥምቀትን በተመለከተ ደግሞ ፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ የጥምቀት በዓል እንዴት እንደመጣ፤ ጥምቀት አከባበሩ፤ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ምን አይነት መልክ እንደነበረዉ፤ መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ በመጥቀስ ፤ ወደ ኢትዮጵያዊዉ ክርስትና መቼ እንደገባ ሁሉ በመዘርዘር ስለጥናቱ ይናገር ነበር። ጥምቀት በዓል ብዙዎችን ያስተሳስራል፤ አንድነት ይፈጥራል፤ የፆታ ልዩነት የለዉም፤ ፍቅርን ያመጣል እያለ ጽፎአል። እንደ ኃይለመለኮት ይህን የዘረዘረበት ምክንያት ሲጠቅስ፤ ዩኔስኮ የፆታ ልዩነት የሚያደርጉ ባህሎችን አይቀበልም።  ጥምቀት ግን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ልጆችን ክርስትና በማንሳት ፤ ማኅበረሰባዊ አንድነትን በመፍጠር ፤ ትዉዉቅን እና መከባበርን በመፍጠር፤  ጋብቻን በመፍጠርና በማስተሳሰር፤ የሰዉ ልጆች እሴቶች በዓል ነዉ እያለ በመፃፍ የጥምቀት በዓል እንዲመዘገብ ከብዙ ዓመታት ጀምሮ ጥረት ሲያደርግ ነበር። ኃይለመለኮት አግዘዉ በሞያዉ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የማይዳሰሱ ቅርሶች ከፍተኛ ምሁር ነበር።           

የአቶ ኃይለመለኮት አግዘዉ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናታዊ ጽሑፎችን ሰባስቦ በመጽሐፍ መልክ ለአንባቢ ይፋ ለማድረግ ሃሳብ እንዳለዉ የነገረን የአሃዱ ራድዮ ስራ አስኪያጅ ጥበቡ በለጠ ተናግሯል።

Äthiopien Hailemelekot Agizew
ምስል DW/T. Belete

ጳጉሜ 6፤ 2011 ዓ.ም ባደረበት ህመም በ50 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየዉ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ኅይለመለኮት አግዘዉ የአንድ ሴት ልጅ አባት ነበር።  አቶ ኃይለመለኮት አግዘዉ በኢትዮዽያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለ ስልጣን የሀገራችንን የማይዳሰሱ ቅርሶችን በተመለከተ የተዘጋጁ ሁለት ባለ 300 ገፅ መፃህፍት በተባባሪ አዘጋጅነት ለህትመት እንዲበቁ አድርጓል። በተጨማሪም ለድሬ ሼኽ ሁሴን፣ ሶፍ ዑመር እና ለጌዴኦ ቅይጥ ባህላዊ እና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች ዓለም አቀፍ የቅርስ አስተዳደር ዕቅድ ማዘጋጀቱ ተዘግቦአል።

ዶቼ ቬለ«DW»ን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃኖች፤ የህትመት፣ የኤሌክትሮኒክስና የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ዕውቀቱን በፅሁፍም በአካልም አጋርቷል። አዲስ አበባ በሚካሄዱ የመፅሀፍ ዳሰሳ መድረኮች ላይ ጥናታዊና ሂሳዊ ፅሁፎችን በሳል ሀሳቦች በማቅረቡ አክብሮትና ተወዳጅነትን አትርፎአል። ፀባየ መልካሙ ኃይለመለኮት አግዘዉ ለሃገሩ ያበረከተዉ ጥሩ ምግባር ሕያዉ አድርጎት ይኖራል። 

ሙሉ ቅንብሩን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!

 

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ