1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለአፍሪቃ ቀንድ የሚተርፈው የግድብ ውዝግብ

ሰኞ፣ ሰኔ 15 2012

በአፍሪቃው ቀንድ የሚታየው የጦር ኃይል ክምችት ያሳደረው ስጋት እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በምትገነባው የኃይል ማመንጫ ግድብ ውስጥ ውኃ ለመሙላት መቃረቧን ማሳወቋ በአካባቢው ሌላ ውጥረት ጋብዟል።

https://p.dw.com/p/3e9A1
Karte Horn von Afrika Golfstaaten EN

ለአፍሪቃ ቀንድ የሚተርፈው የግድብ ውዝግብ

በእንግሊዝኛ ምኅጻሩ ሲፕሪ በመባል የሚታወቀው መቀመጫው ስቶክሆልም ስዊድን የሆነው ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም በአፍሪቃ ቀንድ ላይ እየተጠናከረ የመጣው የሌሎች ሃገራት የባሕር ኃይል ጦር መሥፈር ውሎ አድሮ በአካባቢው የደህንነትና መረጋጋት ጥያቄ ማስከተሉ እንደማይቀር ያመለክታል። ተቋሙ እንደሚለውም በዚህ አካባቢ የአውሮጳ፤ የዩናይትድ ስቴትስ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የአረብ ባሕረ ሠላጤና የእስያ ሃገራት ጦር ኃይላት ይንቀሳቀሳሉ። የአፍሪቃ የስልትና የፀጥታ ጉዳይ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስም ከሰሞኑ ይህንኑ የሚያጠይቅ ጽሑፍ ለንባብ አብቅተዋል። በእሳቸው ዕይታ በአፍሪቃ ቀንድ ላይ በየብስና በባሕር የሚታየው ዓለም አቀፋዊ የጦር ኃይል እንቅስቃሴ በአንድ ወይም በሌላም መንገድ ለኢትዮጵያ ማነቆ ሊሆን የሚችል ነው።

በ1860ዎቹ በቀይ ባሕር ላይ ይደረግ ለነበረው  እንቅስቃሴ አዛዥ ናዛዦቹ ታላቋ ብሪታንያና ኦቶማን ቱርክ ነበሩ። የያኔዋ ኢትዮጵያ ገዢዎችም በባሕሩ አማካኝነት ያደርጉት የነበረው ግንኙነት በዋናነት ለግብፅ በሚቀርቡት በቱርክ ፓሻዎች ቃፊርነት ነበር። ዛሬ ደግሞ ጅቡቲ ላይ ስድስት የውጭ ወታደራዊ የጦር ሰፈሮች፣ በተጨማሪም ሱዳን፣ ሶማሊያና ሶማሌላንድ ላይ የሌሎች በርካታ ሃገራት የጦር ሰፈሮች መኖር የአፍሪቃው ቀንድ ምን ያህል ስልታዊ ጠቀሜታ እንዳለው እንደሚያሳይ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ያስረዳሉ። ምንም እንኳ ግብፅና የመን በመልክአምድር አቀማመጣቸው ራቅ ቢሉም በቀይ ባሕር አካባቢ ያለው ውስብስብ የፀጥታ ይዞታ አካል መሆናቸውን በማመልከትም  የዓለም የንግድ መጓጓዣ የሆነውን ይህን ክፍል ቾክ ፖይንት ወይም ማነቆ እንደሚባል ጠቅሰዋል።

Mike Pompeo  in Äthiopien
ምስል Getty Images/A. Caballero-Reynolds

በአፍሪቃው ቀንድ የሚታየው የጦር ኃይል ክምችት ያሳደረው ስጋት እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በምትገነባው የኃይል ማመንጫ ግድብ ውስጥ ውኃ ለመሙላት መቃረቧን ማሳወቋ በአካባቢው ሌላ ውጥረት ጋብዟል። በጉዳዩ ላይ ለዓመታት ሲደራደሩና ሲወያዩ የሰነበቱት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ ከሰሞኑ ወሳኝ በሚባሉ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ቢግባቡም በሕጋዊ ጉዳዮች ላይ የሦስቱ ሃገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች እንዲነጋገሩበት ትተውታል። ግብፅ ግን ዛሬም ኢትዮጵያ የቀረበላትን ሃሳብ ውድቅ አድርጋብኛለች በሚለው ክሷ ገፍታለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ግብፅ በአንድ በኩል እየተደራደረች በሌላ ወገን ዓለም አቀፍ ድጋፍ በመሻት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር እየሠራች ነው ሲሉ ወቅሰዋል። 

ግብፅ ጉዳዩን ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በአንድ ወገን ብቻ ውሳኔ የሚከናወን ማንኛውም ርምጃ ድርድሩን ይጎዳል አቤቱታ አቅርባለች።  የዩናይትድ ስቴትስ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በምሥራቅ አፍሪቃ የሚገኙ 257 ሚሊየን ሕዝቦች ጥቅም ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ ፍትሃዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ በምትወስደው ርምጃ የሚወሰን በመሆኑ፤ ቴክኒካዊ ነገሮች መፍትሄ አግኝነተዋል፤ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት ስምምነት ይቀራል የሚል መልእክት በትዊተር ይፋ አድርጓል። መልእክቱ በኢትዮጵያውን በኩል በጎ ስሜት አለመፍጠሩን በዚያው በማኅበራዊ መገናኛው የተሰጠው ምላሽ በግልፅ ያሳያል፤ ጣልቃ ገብነቱም ክፉኛ ተወግዟል። የአፍሪቃ የስልትና የፀጥታ ጉዳይ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስም ዓለም አቀፍ ትኩረት በሳበው የዚህ ግድብ ጉዳይ ውዝግቡ በግብፅ እና ኢትዮጵያ ብቻ ሳይወሰን ለአፍሪቃው ቀንድ ይተርፋል ነው የሚሉት።

Äthiopien Luftbild Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre
ምስል DW/Negassa Desalegen

ከባሕር ዳርቻ ግዛቶቿ በአንድም በሌላም አጋጣሚና ምክንያት እየተገፋች ወደብ አልባ ከሆነች ሦስት አስርት ዓመታት ያስቆጠረችው ኢትዮጵያ ዛሬ የአረብ ሊግ አባላት በሆኑት ጎረቤቶቿ ወደብ ላይ ጥገኛ ናት። ስደተኞችን ከማስተናገድ አልፋ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት በማቅረብ ለአካባቢው የአረጋጊነት ሚና የነበራት ሀገር አሁን በውስጥ ጉዳይዋ ተወጥራለች። ከዚህ ቀደም በነበረው አብዛኛው የኢትዮጵያ ታሪክ በሀገር ውስጥ ምን መቆራቆስ ቢኖር ከውጭ ለሚመጣ ማናቸውም ጥቃት በጋራ የመቆም አካሄድ ታይቷል። አንዳንዶች ዛሬም የህዳሴው ግድብ ይህንኑ ታሪክ ሊያስደግም ይችላል በሚል ለሚታየው የፖለቲካ ውዝግብ ማብረጃ ገፀ በረከት አድርገው ይመለከቱታል። በአንፃሩ ይህ አጋጣሚ ከውጭ የገጠማትን ፈተና የምትቋቋምበት አቅም እንዳያሳጣት የሚሰጉ አልጠፉም። አልፎ ተርፎም ጦሱ ለአፍሪቃው ቀንድ ይተርፋል የሚል ስጋት አለ። በውጪ ግንኙነት ስትራቴጅክ ጥናት ኢንስቲትዩት የሰላምና ደህንነት ባለሞያው አቶ አበበ አይነቴ በውስጥ ጉዳይ የውጭ ጫና ሲጨመርበት ችግሩ ለሌሎችም ይተርፋል ባይ ናቸው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለቀውስ ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮችን የሚያጠናው ክራይስስ ግሩብ በቪዲዮ በአጭሩ ባቀረበው መረጃ ግድቧን በውኃ ለመሙላት የተቃረበችው ኢትዮጵያ ከቀሪዎቹ የተፋሰሱ ሃገራት ማለትም ሱዳንና ግብፅ ጋር ከስምምነት ካልደረሰች በአካባቢው ውጥረቱ ሊባባስ እንደሚችል ለማሳየት ሞክሯል። ለአፍሪቃ ቀንድ ብሎም ለምሥራቅ አፍሪቃ ሰላሟ እንደሚተርፍ የሚታመነው ኢትዮጵያ ቀደም ሲልም ቢሆን ከአፍሪቃውያን ውጭ ኃይል ስለምታመነጭበት ግድብ የሌሎች ጣልቃ ገብነትም መፍቀድ አልነበረባትም የሚሉት ዳዊት ወልደጊዮርጊስ አሁንም አፍሪቃን ከጎኗ ማሰለፍ ይኖርባታል ይላሉ።

ግብፅ አንዴ በድርድሩ እገፋለሁ እያለች በሌላው ወገን ደግሞ ዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነት በመሻት ጉዳዩን ከተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አድርሳለች። ኢትዮጵያ በአባይ ውኃ የመጠቀም መብቴን ከማንም ሳልጠብቅ ግድቡን በውኃ እሞላለሁ ብላለች። የኢትዮጵያ ራሷን ችሎ ይህን ታላቅ ፕሮጀክት ነድፎ መንቀሳቀስ ትኩረት መሳቡ እንዳለ ነው። ጉዳዩን በአንክሮ ሲከታተሉ የከረሙት ታዛቢም ይባሉ አደራዳሪ ኃይሎች አሰላለፍና አቋም ከሚለይበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ደርሷል። የስጋት ምንጭ መሆኑ የሚነገርለት በአፍሪቃው ቀንድ የተበራከተው የውጭ ኃይሎች የጦር ሰፈር ዓይነተኛ ተልዕኮና እንቆቅልሽ አብሮ ይፈታ ይሆን? 

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ