1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለአደጋ የተጋለጡት የጎንደር አብያተ መንግሥታት

ረቡዕ፣ ጥቅምት 19 2012

በየጊዜው የሚደረጉ ጥቃቅን ጥገናዎች የቅርሱን ችግር በመሰረታዊነት የሚፈቱ አይደሉም ሲሉ የጎንደር አፄ ፋሲል አብያተ መንግስታት ቅርስ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ አብያተ መንግስታቱን በዘላቂነት ለማደስ እቅድ መያዙን ደግሞ የአማራ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ዐስውቋል፡፡

https://p.dw.com/p/3SCCj
Äthiopien Gondar
ምስል DW/A. Mekonnen

ጥቃቅን ጥገናዎች የቅርሱን ችግር በመሰረታዊነት አይፈቱም ተባለ

በየጊዜው የሚደረጉ ጥቃቅን ጥገናዎች የቅርሱን ችግር በመሰረታዊነት የሚፈቱ አይደሉም ሲሉ የጎንደር አፄ ፋሲል አብያተ መንግስታት ቅርስ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ አብያተ መንግስታቱን በዘላቂነት ለማደስ እቅድ መያዙን ደግሞ የአማራ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ዐስውቋል፡፡

የጎንደር አብያተ መንግሥታት ከ17ኛው እስከ 18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተለያዩ የጎንደር መንግሥታት የተገነቡ ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቅርስነት በተመዘገቡት በእነዚህ ቤተመንግሥታት  10 የሚደርሱ የተለያዩ አገልግሎቶች ይሰጡ የነበሩ ግንቦች ይገኛሉ፡፡ አብያተ መንግሥታቱን በርከት ያሉ የተለያዩ የአገርና የውጪ ጎብኝዎች በየዓመቱ ይጎበኛሉ፡፡

ቅርሱ እድሜ ጠገብ ከመሆኑ አንፃር መሰረታዊ ጥገናዎች ያልተደረጉለት በመሆኑ ለአደጋ እየተጋለጠ እንደሆነ የጎንደር ዓለም አቀፍ ቅርስ አስተዳደር አስተዳዳሪ አቶ ጌታሁን ሥዩም ሰሞኑን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ አሁንም አነስተኛ ጥገናዎች እየተደረጉለት መሆኑንና ለዚህም 40 ሚሊዮን ብር በጀት መጠየቁንና ምላሽ እየጠበቁ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

የቅርሱን የውስጥ ክፍሎች ተዘዋውረን ማየት እንደቻልነው ተገቢ ያልሆኑ ጽሁፎች በጎብኝዎች እንደተፃፉባቸው፣ ንጽህናው እንደማይጠበቅና ግዴለሽነት እንደሚታይበት ወደ ቦታው በተንቀሳቀስንበት ጊዜ ለመመልከት ችለናል፡፡

Äthiopien Fasil Ghebbi, Festungsstadt in der Region Gonder | Graffiti
ምስል DW/A. Mekonnen

ይህን አስመልክተው የቅርሱ አስተዳዳሪ አቶ ጌታሁን እንዳሉት አጠቃላይ የአብያተ መንግስቱ የሰው ኃይል መዋቅር ያልተሟላ በመሆኑ በቂ የቁጥጥርና የጽዳት ሥራዎች በተሟላ ሁኔታ እየተካሄዱ እንዳልሆነ አምነዋል፡፡

የአማራ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ጥቃቅን ጥገናዎች በቅርሱ አስተዳደር እየተካሄዱ መሆኑን እንደሚውቁ፣ ሆኖም መንግስት ለቅርሱ መሰረታዊ ጥገና ለማድረግ ጥናቶችን ማድረጉንና በቅርብ ጊዜ ወደ ተግባር እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በጀትን በተመለከተም ከሚሰበሰበው ገቢ 70% ለአብተ መንግስቱ አስተዳደር ገቢ አንደሚሆንና ይህ መሰረት ተደርጎ የጠየቁት በጀት እንደሚፈቀድ ተናግረዋል፡፡ የሰው ኃይል አደረጃጀትን በተመለከተም ጥያቄው ለክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መላኩንና ምላሽ እየተጠበቀ እንደሆነ አብራርተዋል።

ለሀገር ውስጥ ጎብኝዎች 10 ብር እንደሚያስከፍሉ የተናገሩት የቅርሱ አስተዳዳሪ የውጭ አገር ጎብኝዎች የተሻለ እንደሚከፍሉና አመታዊ ገቢውን አብራርተዋል፡፡

በተለምዶ የፋሲለደስ ግንብ ተብሎ የሚጠራው አብያተ መንግስት ከያዛቸው ቤተ መንግስታት መካከል የፋሲለድስ፣ የዓለምሰገድ ፋሲል፣ የአዕላፍ ሰገድ ፃዲቁ ዮሐንስ፣ የአድም ሰገድ ዳዊት፣ የአድያም ሰገድ እያሱ፣ የመሲህ ሰገድ በካፋ፣ የብርሐን ሰገድ ቋረኛው እያሱና የእቴጌ ምንትዋብ ግንቦች ይገኙበታል፡፡

የጎንደር ቤተመንግሥታት በዩኔስኮ በዓለምአቀፍ ቅርስነት የተመዘገቡት እ. ኤ. አ. በ1979  ነው፡፡

ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ