1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለአርሶ አደሮች ወቅታዊ የገበያ መረጃን የሚያደርሰው መተግበሪያ

ረቡዕ፣ ግንቦት 9 2015

በወሎ ዩንቨርሲቲ እና ፋርም አፍሪካ በተባለ በግብርና ላይ በሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አማካኝነት በጋራ የተሰራው ይህ መተግበሪያ «ኢትዮፋርም አፕ» በመባል የሚጠራ ሲሆን፤አርሶ አደሮች በግብርና ምርቶች ላይ ወቅታዊ የገበያ መረጃ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።

https://p.dw.com/p/4RVyD
Äthiopien Farm Mobile Anwendung
ምስል Solomon Aydagn @privat

መተግበሪያው ገበሬዎች ምርቶቻቸውን በተሻለ ዋጋ እንዲሸጡ አስችሏል


የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በግብርና ምርቶች ላይ ለአርሶ አደሮች ወቅታዊ የገበያ መረጃን የሚያቀብል መተግበሪያን ያስተዋቃል ።
ግብርና በኢትዮጵያ ትልቁ የኢኮኖሚ ምሰሶ ሲሆን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 40%፣ ከወጪ ንግድ ደግሞ 80% ይይዛል። 75% የሚሆነው የሀገሪቱን የሰው ሃይልም በዚሁ ዘርፍ የተሰማራ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ያም ሆኖ  የሀገሪቱ የግብርና ዘርፍ ደካማ የገበያ ትስስር ያለው በመሆኑ፤ ብዙ ጊዜ የገበያ ሰንሰለት የሚፈጠረው እና  ዋጋ የሚወሰነው በደላሎች እና በነጋዴዎች ይሆናል።ይህም አርሶ አደሮች ምርታቸውን በተፈለገው ዋጋ መሸጥ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል።
ይህንን ችግር  የተገነዘበው የወሎ  ዩኒቨርሲቲ ችግሩን ለመቀነስ  አዲስ የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ መስራቱን በዩንቨርሲቲው የኮምቦልቻ የቴክኖሎጅ ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር  አቶ ለሚ አማኑኤል ይገልፃሉ።
በወሎ ዩንቨርሲቲ እና ፋርም አፍሪካ በተባለ በግብርና ላይ በሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አማካኝነት በጋራ የተሰራው ይህ  መተግበሪያ «ኢትዮፋርም አፕ» በመባል የሚጠራ ሲሆን፤አርሶ አደሮች በግብርና ምርቶች ላይ ወቅታዊ የገበያ መረጃ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው። ይህም አርሶ አደሩ በብዙ ልፋት ያመረተውን ምርት ቀጥታ ለገበያ ማቅረብ ሲገባው ደላሎች በሚፈጥሩት ተገቢ ያልሆነ የገበያ ሰንሰለት  ምርቱን በሚፈልገው ዋጋ እንዳይሸጥ ይፈጠር የነበረውን መሰናክል ያስቀራል።በዚህም ከተጠቃሚ ከገበሬዎቹ ጥሩ ግብረመልስ መገኘቱን አቶ ለሚ አመልክተዋል።
በወሎ ዩንቨርሲቲ የሶፍትዌር ምህንድስና መምህር የሆኑት አቶ ሰለሞን አይዳኝ መተግበሪያውን በማበልፀግ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው።እሳቸው እንደሚሉት ይህ ቱክኖሎጅ ሶስት መሰረታዊ ክፍሎች አሉት። 

Äthiopien Ato Solomon Aydagn
ምስል privat

«የገበያ መተጃ የሚያደርሰው መተግበሪያ ሶስት መሰረታዊ «ፕላትፎርሞች» አሉት።አንደኛው የዌብ ወይም ፖርታል ሰርቪስ አለው።የሞባል አፕሊኬሽኖቹ አስፈላጊውን መረጃ ለመውሰድ እንጠቀምበታለን።ከሞባይል «አፕሊኬሽኖቹ» የሚላኩትን መረጃዎች ደግሞ ለአስተዳደራዊ ፍጆታ የሚሆኑ ለአስተዳደር አካላት መረጃ  መስጠት እና ማፅደቅ ስራ የምንሰራበት «የዌብ ፖርታል» አለ።» ካሉ በኋላ ከዚያ ውጭ ሁለት መተግበሪያዎች እንዳሉ ገልፀዋል። አንደኛው በየገበያ ቦታው ባለሙያዎች የገበያ ዋጋ የሚሰበሰብበት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ገበሬዎች መረጃ የሚያገኙበት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ስማርት ስልክ ለሌላቸው ገበሬዎች 611 በሚባል  በሚባል ቁጥር  በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መረጃ እንደሚሰጥ አመልክተዋል።እንደ አቶ ሰለሞን ይህ መተግበሪያ ለሙከራ በተመረጡ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎና የከሚሴ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር  ዞኖች በሚገኙ አምባሰል ፣ተሁለደሬ እና ዳዋጨፋ በተባሉ ወረዳዎች ከአንድ ዓመት በላይ ስራ ላይ ውሏል። በእነዚህ አካባቢዎች  ለሚገኙ አርሶ አደሮችም በሳምንት አራት ቀናት በመተግበሪያው  አማካኝነት ወቅታዊ የገበያ መረጃ በእጅ ስልካቸው  እንዲደርሳቸው ሲደረግ መቆየቱንም ተናግረዋል።እንደ ባለሙያው ገለፃ መረጃው ከየወረዳው በተውጣጡ የንግድ ፅህፈት ቤት ባለሙያዎች አማካኝነት የሚሰበሰብ ሲሆን፤ መረጃው ከትክክለኛ ቦታ መምጣት አለመምጣቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል መተግበሪያው የራሱ ዘዴዎች አሉት።«ማንም ሰው ወይም ዳታ ኮሌክተሮቹ እነዚያ ባለሙያዎች ሲልኩ ከየት እንደሆነ ስልኩ ያውቃል።ለምሳሌ አምሳል ጉልቦ የሚባል ገበያ ላይ ከሆነ እየሰራን ያለነው ።የዚህን ቦታ ካርታ ያስገባን ስለሆነ ከዚያ ውጭ ከላኩ መረጃው ታዓማኒነት እንደሌለው  ራሱ ያጋልጣል ማለት ነው።» በማለት አብራርተዋል።

Äthiopien Farm Mobile Anwendung
ምስል Solomon Aydagn @privat

መተግበሪያው በመጀመሪያ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጄ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን የኦሮምኛ ቋንቋን ለማካተት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በመተግበሪያው እና በጥሪ ማዕከሉ  በሚገኘው የገበያ መረጃም አርሶ አደሮች  ምርታቸውን በወቅቱ ገበያ ሸጠው መጠቀም መቻላቸውን አስረድተዋል። ከተጠቃሚዎቹ መካከል በከሚሴ ዙሪያ ልዩ ስሙ 07 ቀበሌ በሚባለው አካባቢ የሚኖሩት አርሶአደር  መሀመድ አብዱ አንዱ ናቸው።እሳቸው እንደሚሉት መተግበሪያው የግብርና ምርቶቻቸውን በተሻለ ዋጋ እንዲሸጡ አስችሏዋል።
በዚህ ሁኔታ እንደ አቶ መሀመድ አብዱ ያሉ 1 ሺሕ 300 አርሶአደሮች  ተጠቃሚ መሆናቸው ተገልጿል።ይህም ለቴክኖሎጅው ውጤታማነት ማሳያ ይላሉ ባለሙያው። 
በሌላ በኩል የቴክኖሎጅ ተቋሙ ከዚህ ቀደምም የተለያዩ ሶፍትዌሮችን በማልማት ለዩንቨርሲቲው ማህበረሰብ ግልጋሎት እንዲሰጥ ማድረጉን ሀላፊው አቶ ለሚ አማኑኤል ገልፀዋል።ሌሎች ግብርናውን ለማዘመን የሚግዙ የቴክኖሎጅ ስራዎች መሰራታቸውንም አመልክተዋል።በቅርቡ የሙከራ ጊዜውን ያጠናቀቀውን ይህ  መተግበሪያም ለወደፊቱ የአገልግሎት ተደራሽነቱን  በማስፋት ለበርካታ የክልሉ አርሶ አደሮች ወቅታዊ የገበያ መረጃ በማቅረብ  አርሶ አደሩ ምርቱን ተደራድሮ እንዲሸጥ ለማስቻል ታቅዷል።ይህንን  ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግም ዩንቨርሲቲው ሃላፊነት ወስዶ እየሰራ መሆኑን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።

Äthiopien Farm Mobile Anwendung
ምስል Solomon Aydagn @privat

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ