1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለህዳሴ ውዝግብ በጀርመን ተቋም የቀረበ አማራጭ ሃሳብ

ረቡዕ፣ መጋቢት 2 2012

የህዳሴውን ግድብና የአባይን ፍትሃዊ የውኃ አጠቃቀም ውዝግብ ለመፍታት የጀርመን የሳይንስ የፖለቲካና ዓለም አቀፍ የደህንነት ጉዳዮች ተቋም አዲስ አማራጭ ምክረ ሃሳብ አቀረበ። ተቋሙ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ለገባችበት የህዳሴው ግድብ የዉኃ ሙሌት ውዝግብ የካሳ ክፍያ ድጋፍ እንዲደረግ ሃሳብ አቅርቧል:: 

https://p.dw.com/p/3ZDMs
Äthiopien Addis Abeba | Diskussion Blue Nile & Renaissance-Damm | Flaggen
ምስል DW/G. Tedla

የካሳ ክፍያ ድጋፍ እንዲያደረግ ሃሳብ አቅርቧል

የህዳሴውን ግድብና የአባይን ፍትሃዊ የውኃ አጠቃቀም ውዝግብ ለመፍታት የጀርመን የሳይንስ የፖለቲካና ዓለም አቀፍ የደህንነት ጉዳዮች ተቋም አዲስ አማራጭ ምክረ ሃሳብ አቀረበ። ተቋሙ ግድቡ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪውን ክፍለ ኢኮኖሚ ዘርፍ ለማጠናከርና ልማትን ለማስፋፋት ወሳኝ እንደሆነና የግብፅም ህልውና በአባይ ዉኃ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ሁለቱንም አገራት ተተቃሚ ይሆኑበታል ያለውን የካሳ ክፍያ ሥርዓት በአማራጭነት አቅርቧል:: በዋናነት ጀርመን እና የአውሮጳ አገራት ችግሩን በሰላማዊና የህግ ማዕቀፍ ለመፍታት እንዲያደራድሩ የጠየቀው ይኸው ጥናት በተለይም የአየር ፀባይ ለውጥን ተከትሎ በሚከሰተው ድርቅ እና የዝናብ እጥረት ኢትዮጵያ የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በግድቡ የዉኃ ሙሌት እና አለቃቅ ሂደት ላይ ማሻሻያ እንድታደርግ በአንጻሩም ግብፅ ኢትዮጵያ ለሚደርስባት ኪሳራ ተመጣጣኝ የማካካሻ ክፍያ እንድትከፍል የሚጠይቅ ነው:: ተቋሙ አደራዳሪዎቹ የአውሮጳ መንግስታት በአሁኑ ወቅት የፋይናንስ እጥረት ያለባት ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ለገባችበት የህዳሴው ግድብ የዉኃ ሙሌት ውዝግብ የካሳ ክፍያ ድጋፍ እንዲያደርጉም ሃሳብ አቅርቧል::  

Äthiopien großer Renaissance Damm GERD
ምስል DW/A.Mekonnen

ካለፈው ዓመት ማብቂያ ጀምሮ በአሜሪካ እና የዓለም ባንክ አደራዳሪነት በኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን መካከል ሲካሄድ የቆየው የህዳሴው ግድብ ወዝግብና የአባይ ዉኃ አጠቃቀም ውይይት ውጤት ሳያመጣ መቋረጡን ተከትሎ ከሰሞኑ የጀርመን የሳይንስ የፖለቲካና ዓለማቀፍ የደህንነት ጉዳዮች ተቋም አዲስ አማራጭ ምክረ ሃሳብ ይዞ ቀርቧል:: በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሃይል እጥረት መኖሩን የጠቆመው ጥናቱ የኢንዱስትሪውን ክፍለ ኢኮኖሚ ዘርፍ ለማጠናከርና ልማትን ለማስፋፋት የህዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያ ወሳኝ እንደሆነና የግብፅም ህልውና በአባይ ዉኃ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያብራራል:: በመሆኑም አገራቱ የሚወዛገቡበትን የዉኃ ሙሌት እና ፍትሃዊ የዉኃ አጠቃቀም ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት መፍትሄው ውጤት አልባ ድርድር ሳይሆን የካሳ አከፋፈል ሥርዓትን ገቢራዊ ማድረግ መሆኑንም የተቋሙ ባለሙያዎች

በጥናቱ ላይ አመልክተዋል:: የበርካታ ባለሙያዎችን አስተያየቶችንና ታሪካዊ ሰነዶችን መነሻ አድርጎ የተዘጋጀ ነው የተባለው ጥናቱ በተለይም የአየር ፀባይ ለውጥን ተከትሎ በሚከሰተው ድርቅ እና የዝናብ እጥረት ኢትዮጵያ የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ አስገብታና አሁን የያዘችውን አቋማን አለዝባ በግድቡ የዉኃ ሙሌት እና አለቃቅ ሂደት ላይ ማሻሻያ እንድታደርግ በአንጻሩም እንደ አየሩ ፀባይና እንደ ጊዜው ርዝመት እየተሰላ ግብፅም ኢትዮጵያ ለሚደርስባት ኪሳራ ተመጣጣኝ የማካካሻ ክፍያ እንድትከፍል የሚጠይቅ ነው:: ድርጅቱ የአገራቱን የዉኃ ውዝግብ ለመፍታት በዋና አደራዳሪነት ሊሳተፉ ይገባል ያላቸው ጀርመን እና አጋሮቿ የአውሮጳ ህብረት አገራትም በአሁኑ ወቅት የፋይናንስ አቅም እጥረት ያለባት ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ለገባችበት የህዳሴው ግድብ የዉኃ ሙሌት ውዝግብ የካሳ ክፍያ ድጋፍ እንዲያደርጉም ሃሳብ አቅርቧል:: በዚህ ጥናት ውስጥ የዓለማቀፉ የጀርመን የደህንነት ተቋም ባለሙያዎች ሉካ ሚኸስቴፋን ሮል እና ቶቢያስ ፎን ሎሶው ተሳታፊ ሆነዋል:: በተቋሙ የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪቃ ጉዳዮች የምርምር ቡድን ሃላፊ የሆኑት ሚስተር ሚኸ በአሜሪካ እና የዓለም ባንክ እንዲሁም በአባይ ተፋሰስ አገራት የትብብር መድረክ በኩል እስካሁን የዉኃ ውዝግቡን ለመፍታት የተደረጉት ጥረቶች ውጤት አለማምጣታቸውን ገልፀው አሁን ላይ የሁለቱንም አገራት ተጨባጭ ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት ድርጅቱ የደረሰበት የጥናት መፍትሄ የካሳ ስምምነትን ገቢራዊ የማድረግ አማራጭ ዘዴ መሆኑን በተለይ ለዶይቼ ቨለ "DW" አብራርተዋል::

"ሁለቱ አገራት በተለይም የህዳሴው የግድብ ዉኃ ሙሌት ላይ መግባባት ተስኖዋቸዋል:: ግብፅ የግድቡ ሙሌት ጊዜዉ ከ12  እስከ 21 ዓመት እንዲሆን ስትጠይቅ ከ4 እስከ 7 ዓመት ይሁን የሚል ሃሳብ አቅርባ የነበረው ኢትዮጵያም ባለፈው ዓመት ማብቂያ70 በመቶ ያህል የግድቡ ግንባታ በመጠናቀቁ በያዝነው ዓመት ሙሌቱ ተከናውኖ የማመንጨት ስራው በቅርብ ጊዜያት እንደሚጀምር እየገለፀች ነው::በዋሽንግተን የተካሄዱት ሶስት ዙር ድርድሮች ያለውጤት ተጠናቀዋል::ከዚህ በኋላ የአሜሪካው ድርድር ተስፋ ያመጣል ተብሎ አይታሰብም:: በአውሮጳ ህብረት ድጋፍ የሚደረግለትና እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 1999 ዓ.ም የተመሰረተው ናይልን ለማልማት ተስማምተው በፊርማቸው ያጸደቁት የአባይ ተፋሰስ ሃገራት የትብብር መድረክ /የናይል ቤዚን ኢኒሼቲሽም/ ቢሆን የተፋሰሱ አባል ሃገራት በፍትሃዊ የዉኃ ሃብት አጠቃቀም እና የግጭቶች አፈታት ዙሪያ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች እስከዛሬ ይህ ነው የሚባል ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ እንዳልቻለ ተገንዝበናል:: በዚህ ምክረ ጥናት መሰረት ጀርመን እና የአውሮጳ አገራት በቀጣናው በዉኃ ውዝግብ ምክንያት የሰፈነውን ውጥረት ለማርገብና ግጭት እንዳይፈጠር የሚያደርጉት ጥረት በሰብአዊ ቀውስ ምክንያት የሚከሰት የስደተኞችን ቁጥር ፍልሰት እንዳይጨምር ይረዳቸዋል:: ዛሬ ላይ የፍልሰተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሻቀብ , የልማት ዕድሎች መዳከምና የመጠጥ ዉኃ እጥረት ለአውሮጳ ተልቅ ተግዳሮት ሆነዋል::ይሁንና የአውሮጳ አገራት ከካይሮ መንግስት ጋር የሚፈፅሙት የፋናንስ ትብብር ውል አጠቃላይ የዉኃ ሃብት ልማትና የመንግስት አስተዳደርን ለማሻሻል ጥቅም ላይ መዋሉን በጥብቅ ሊቆጣጠሩ ይገባል:: ከዚህ ሌላ አገራቱ በ 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን መካከል በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የተፈጠረውን ውጠረት ለማርገብ በካርቱም የተፈረመው አስር አንቀጾች ያሉት "የመርህ መግለጫ" /principles of Declaration/ ውል የሚነሱ ውዝግቦች በሃገራቱ የቴክኒክ ቡድኖች ውይይትና ድርድር እንዲያገኝ የሚተነትን ሲሆን ይህ ሁሉ ጥረት ተደርጎ ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ ግን በመጨረሻው አንቀፅ አስር መሰረት በአገራቱ መራሄ መንግስታት የፖለቲካ ውሳኔና በሌሎች አካላት አደራዳሪነት መፍትሄ ለማፈላለግ የወጣ በመሆኑ ይህንኑ የመጨረሻ አማራጭ የመጠቀሚያው ጊዜ አሁን ነው ብለን እናስባለን " ነው ያሉት የጥናቱ አስተባባሪ ::

አሁን በሚታየው ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ሕግ ላይ የተመሰረተና እውነተኛ መተማመን ያለበት ድርድር ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት የሚያመጣ ባለመሆኑ በጊዜ ብዛት ኢትዮጵያ በግድቡ ዉኃ ሙሌት ልታጣ የምትችለው ኪሳራ ተሰልቶ በካሳ መልክ ሊከፈላት ይገባል ይላል የዓለማቀፉ የጀርመን የደህንነት ተቋም ባለሙያዎች ምክረ ጥናት :: ጀርመን እና አውሮጵያውያኑ ሊመሩት ይገባል ባለው የመጨረሻው ድርድርም ከካይሮ በተጓዳኝ በአሁኑ ወቅት የአባይን ዉኃ በመጠቀም በግብፅ መጠነ ሰፊ የግብርናና የኢንቨስትመንት ልማት እንቅስቃሴ የሚያከናውኑት የመካከለኛው ምስራቅ አገራትንም ማሳተፍ ጠቃሚ መሆኑን ባለሙያዎቹ ይመክራሉ:: ግብፅ በአሁኑ ወቅት የኒውክለር ማብላያና ማበልፀጊያ ግንባታን ጨምሮ በጦር መሳሪያ ምርቶችሸመታ ላይ ተጠምዳለች ያለው ጥናቱ የስጋቷ ሌላው ምንጭ ከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ በአባይ ዉኃ ላይ ተመስርታ እያከናወነች መሆኑንም በዝርዝር ጠቁሟል:: የጥናት ቡድኑ መሪ ሚስተር ሚኸ በአስዋን ግድብ አቅራቢያ ግብፅ ሰፊ የግብርና ልማት እንቅስቃሴ መጀመሯንም ገልፀዋል::በዚሁ የልማት መርሃግብር የመጀመሪያ ምዕራፍ ከፍተኛ የአገሪቱን የቆዳ ስፋት የሚሸፍን መሬት ለልማት መዘጋጀቱን ,ከይዞታው ግማሽ ያህሉንም እንደ ሳዑድ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ያሉ የመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት ኩባንያዎች ለግብፅ መንግሥት የዉኃ የኃይልና የመሬት ሊዝ ኪራይ እየከፈሉ ልዩ ልዩ የምግብና የጥራጥሬ ሰብል ምርቶችን ለአገራቸው ፍጆትና ለጎረቤቶቻቸው በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ነው ያብራሩት:: እነዚህ የባህረ ሰላጤው አገራት ደግሞ የሶስቱም የአፍሪቃ አገራት ዋንኛ ወዳጆችና አጋሮች በመሆናቸው በድርድሩ ሊሳተፉ ይገባል ሲልም የጀርመኑ ጥናት ያትታል:: በፕሬዝዳንት አልሲሲ አስተዳደር በዓለም ሶስተኛዋ የጦር መሳሪያዎች ሸማች አገር በተባለችውና በ 25 ቢልዮን ዶላር ወጪ የኒውክሌር ማብላያና ማበልፀጊያ ተቋም በበረሃማው ግዛቷ በገነባችው ግብፅ የመንግሥት የዉኃ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ችላ ተብሏል ሲልም ተችቷል:: ይኸው ጥናት አፍሪቃውያን የናይል ተፋሰስ አገራትን አግልሎ የመካከለኛው ምስራቅ አገራትን በድርድሩ እንዲካተቱ መጠየቁ ብሎም ኢትዮጵያ ብሄራዊ ሃብቷን ህጋዊ በሆነ መልኩ እንድትጠቀም ዘላቂነት ያለው ፍትሃዊ ዕልባት ከመስጠት ይልቅ ለግብፅ እና ለመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጥቅም የወገነ ያስመስለዋል የሚል ትችት እየተሰነዘረ ነው ,ለዚህ ምን ምላሽ አሎት ስንልም ለሚስተር ሚኸ ጥያቄ አንስተንላቸው ነበር:: "አገራቱ በድርድሩ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በጥናታችን ውስጥ የጠቆምነው በአንድም በሌላም መልኩ ከውዝግቡ ጋር ቁርኝት ስላላቸው ነው:: ከሦስቱም አገራት ጋር ባላቸው ጠንካራ ወዳጅነትም የዉኃ ውዝግቡን አርግቦ ችግሩን በሰላም ለመፍታት ጠቃሚነት ይኖረዋል ከሚል ግንዛቤም በመነጨ ነው:: እርግጥ ነው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት እንዳለና የአብዛኛው ማህበረሰብ የኃይል ፍጆታ መጨመሩን እንዲሁም ለአገሪቱ የገቢ ምንጭ ዕድገት የሚኖረውን ፋይዳ በመገንዘብ የግድቡ መገንባትና ስራውን በተገቢው ሁኔታ መጀመር ትልቅ መፍትሄ ያመጣል ብለን ስለምናምን ሃሳቡን በጥናቱ ውስጥ አካተናል:: በአጠቃላይ የሁለቱንም ጥቅም በእኩል መልኩ በሰጥቶ መቀበል ስሌት ማስጠበቅን ዓላማው ያደረገው የመፍትሄው ምክረ ሃሳብ በተለይም የካሳ ክፍያ ሥርዓቱ በድርድሩ ወቅት ኢትዮጵያ የሚኖራትን ሚና ከፍ የሚያደርግ እንጂ የሚያሳንስ አይደለም:: በግብፅ እና ኢትዮጵያ መካከል ለወደፊቱ በመተማመን ላይ የተመሰረተ ትብብርን ለመገንባትም የሚረዳ ነው" ሲሉ አብራርተዋል::

Ägypten Schifffahrt auf dem Nil
ምስል picture-alliance/AP Photo/A. Nabil

እንዳልካቸው ፈቃደ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ