1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታኅሳስ 22 ቀን 2014 ዓም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 22 2014

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ትናንት በሰጡት መግለጫ አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ከመወያየት ይልቅ በተደጋጋሚ ከሌሎች አገራት ጋር መነጋገርን መርጣለች ብለው "አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መወያየት ከፈለገች እኛ ሁሌም ዝግጁ ነን፤ በእኛ ጉዳይ ላይ ከእኛ ጋር መወያየት አለባት" ሲሉ አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/450jN
Äthiopien Hawassa | Ambassador Dina Mufti
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የታኅሳስ 22 ቀን 2014 ዓም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት


በዚህ ሳምንት አጋማሽ የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን አጽድቋል፣የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ ጋር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተነጋግረዋል።በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጥሪ ወደ ሀገራቸው በመግባት ላይ ላሉት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይፋዊ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። የዛሬው ዝግጅታችን በነዚህ ሶስት ጉዳዮች ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን ያስቃኘናል።
የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንና የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ በዚህ ሳምንት ማክሰኞ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተነጋግረዋል ። የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በሰጡት መግለጫ ኬንያታና ብሊንከን የኢትዮጵያው ጦርነት እንዲቆም ፣ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ፣የሰብዓዊ እርዳታ ያለ ምንም እንቅፋት እንዲቀርብ፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችና በደሎች እንዲቆሙ እና ጦርነቱም በድርድር መቋቻ እንዲያገኝ መስማማታቸውን ገልጸዋል። በዚህ መግለጫ ላይ በማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። ገዝሽ ላቭ በሚል የፌስቡክ ስም ጥያቄ ቀርቧል። «ኬንያታ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስቴር ሆኑ እንዴ?የሚልጆን ሳላ ቦይ «የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ እንጂ ኬንያታ አይደለም።ሲሉ ጽፈዋል። ፍሬህወት ታርኮም  «እኛ ሳናውቀው ኡሁሩ ኬንያታ ኢትዮጵያን መምራት ጀመሩ እንዴ ሲሉ ጠይቀዋል። አብርሃም ኃይሉ ደግሞ «በኢትዮጵያ ጉዳይ ባንዳና ቅኝ ገዥዎች ሳይስማሙ ቀርተው አያውቁም ግን ምንም አያመጡም። የኢትዮጵያ ጉዳይ በኢትዮጵያውያን ብቻ ነው የሚፈታው» በማለት አጭር አስተያየታቸውን በፌስቡክ አስፍረዋል። «አሜሪካ በዚሕ ዘመንም እንደ አለቃ ትታያለች የእኛዎችም እንደ አለቃ ያይዋታል ብዙዎች የተሻሉ ልንከተላቸው የሚገቡ ረዳቶች ስላሉን ትቅር» የሚሉት ደምሰው እሸቱ « ኢትዮጵያ በእግዚአብሔር ጥበቃ እንጅ በአሜሪካ አልኖረችም ፤አትኖርም በቃ »ሲሉ ሃሳባቸውን ደምድመዋል። ነጋ መኮንን በበኩላቸው ጦርነቱ መቋጨት ያለበት በህግ የበላይነት ብቻ ነው! ወንጀለኛ ተጠያቂ እንዳይሆን የሚያደርግ አካሄድ ዘላቂ ሰላም አያመጣም» ብለዋል። ሙሉጌታ ነብዩ ደግሞ «ኬኒያ በኢትዮጵያ ጉዳይ ምን አገባት ከህውሀት ጋር የምትደራደረው ኬኒያ ናት እንዴ የተኩስ አቁሙንስ ቢሆን ኬኒያ ናት እንዴ ከወራሪው ጋር የምትነጋገረው ይገርማል ዘንድሮ የአሜሪካ ነገር፤ ሲሉ ትዝብታቸውን አጋርተዋል።
ብርሀኑ መሰለ  እኛጋ መምጣትና ከእኛ መሪዎችጋ ተቀምጦ ማውራት ምንድን ነው ያስፈራቹ እኛኮ ምህረት ከጠየቃቹ ልባችን በይቅርታ የተሞላ ነው ኢትዮጵያ እና ኬንያ ወዳጆች ብንሆንም የየራሳችን መሪዎች ያለን አገሮች ነን ዙሪያ ጥምጥም መሄድ አያስፈልግም በር እንዲከፈትላቹ ከፈለጋቹ አንኳኩ እንደአመጣጣቹ ልንከፍትላቹ እንችላለን ስትመጡ ግን ንፁህ ልብ ይዛቹ ኑ ሲሉ አሳስበዋል። የኢትዮጵያ መንግሥትም የአሜሪካ መንግሥት በእኛ ጉዳይ ከሌሎች ሀገራት ሳይሆን ከእኛ ጋር መወያየት አለበት ሲል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል አስታውቋል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ትናንት በሰጡት መግለጫ አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ከመወያየት ይልቅ በተደጋጋሚ ከሌሎች አገራት ጋር መነጋገርን መርጣለች ብለው "አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መወያየት ከፈለገች እኛ ሁሌም ዝግጁ ነን፤ በእኛ ጉዳይ ላይ ከእኛ ጋር መወያየት አለባት" ሲሉ አስታውቀዋል።
በዚህ ሳምንት ረቡዕ ነበር የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተነጋግሮ አዋጁን ያጸደቀው። ከአንድ ሳንምት በፊት ለምክር ቤቱ ቀርቦ የነበረው ይኽው ረቂቅ አዋጅ በምክርቤቱ ከመጽደቁ በፊት ለሕግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቶ ኮሚቴውም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ካላቸው አካላት ጋር ከመከረ በኋላ ምክር ቤቱ እንዲወስንበት ማቅረቡን ነበር ያሳወቀው ።በዚሁ መሠረት ምክር ቤቱ በአንደኛ ዓመት ሁለተኛ ልዩ ስብሰባው በረቂቁ ላይ ተወያይቶ በ13 ተቃውሞና በ1 ድምጸ ተዐቅቦ  አዋጁን አጽድቆታል። አዋጁ ከጸደቀ በኋላ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። 
መቶ በመቶ  ለአገሪቱ ምክክርና መግባባት የግድ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ሰዉ በጦርነት በእስር ቤት እየተሰቃየና ሀገር እየወደመ ሰው እየሞተ ነው። ካልሆነ ከዚህ የበለጠ ሞትና ውድመት ይመጣል። ፈጣሪ ይርዳችው በርቱ፤ የአንድ ብሔርና ክልል የበላይነት እኔ ብቻ ያልኩት ይሁን የሚሉ ሀገርን ወደማትወጣበት አዝቅት እና ውድመት ከተዋታል ይህ ሊቆም ይገባል የሚለው ዱግዋ በሚል ስም የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት ነው።
ኦብሴ ደምባል ደግሞ ችግሩን ለመፍታት በቅድሚያ ሊወሰዱ የሚገቡ ያሏቸውን እርምጃዎች ጠቁመዋል። አብሴ «የሃገሪቱ ችግር በ ምክክር በውይይት ይፈታ ከተባለ የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ይፈቱ፤ ያለበለዚያ ይሄ ማደንዘዣ ፣ እድሜ ማራዘሚያ እንጂ የ ሃገሪቱን ችግር አ ይፈታም »ብለዋል። ታደለ የእናቱ ልጅ በሚል ስም የሰፈረ አስተያየት ደግሞ «ምንም ብትሉ ምን፣ ህገ መንግስቱ እስካልተሻሻለ ድረስ የዚህችን ሃገር ችግር መፍታት በፍፁም አይቻልም። ህገ መንግስቱ ሁሉን ነገራችንን አበላሽቶታል ይላል።
ቸሬ ዘጉራጌ ኢትዮጵያዊ በሚል የፌስቡክ ስም «በእርግጥ ሀገሪቱ ምክክር ያስፈልጋታል ። ነገርግን ዛሬም እንደትናንቱ እያንዳንዱ ውሳኔና አዋጅ በገዢው ፓርቲና ባለሟሎቹ ብቻ የሚዘወር ከሆነ ለውጥ አይኖረውም! ሁሉንም አካታች የሆነና  ገለልተኛ ተቋም ነው መገንባት ያለበት ባይ ነኝ»የሚል አስተያየት ተሰጥቷል
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ፣በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውንና  ትውልደ ኢትዮጵያውያን የገናና የጥምቀት በዓላትን ለማክበር ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ጥሪ ካቀረቡ ሳምንታት አልፈዋል። ዳያስፖራውም በግብዣው መሰረት, ወደ ሀገሩ እየሄደ ነው። መንግሥት በዚህ ሳምንት በአዲስ አበባው የወዳጅነት አደባባይ ለዳያስፖራዎች ይፋዊ አቀባበል አድርጓል። በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋቸዋል። ይህ አቀባበል ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አነጋጋሪ ሲያነጋግር ነበር።
ሱልጣን አህመድ አብደላ እንኳን ቤታችሁ ወደሆነችው ሀገራችሁ መጣችሁ ብለዋል ዳያስፖራውን። በየነ አሊሾ ደግሞ እንኳን ወደ ሀገራችሁ በደህና መጣችሁ ።ደስተኛ ሁኑ፣የሀገራችሁን ገጽታ ቀይሩ ሲሉ መክረዋል። 
አሚና ሰኢድ ግን ቅሬታ አላቸው።«ኢትዮጵያዊያን ሳይሆን ማለት ያለባችሁ ባለ ዶላሮቹን አስገባን በሉ ኢቶጵያዊያኖች ካላችሁ እኛ በሳውድ እስር ቤት የምንገኘው ምንድ ነን ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል። አላኽ ከሪም በሚል የፌስቡክ ስምም ተመሳሳይ አስተያየት ተጽፏል። «የኢትዮጵያን ወዳጆች የሚለውን ትታችሁ ዶላረ ያላችሁ በሚል ይስተካከል… ለኢትዮጵያ ልጆች ቢሆን ሀሳቡ በሳኡድ እስረኞች እያለቁሡ ባልቀሩ ነበረ »ይላል አስተያየቱ።
ቀን ጥሏቸው ነው እንጂ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ወገኖቻችንም ዲያስፖራ ነበሩ። ያውም ከማንም በላይ በችግር ወቅት ቀድሞ ደራሾች! የምንፈልገው ጊዚያዊ ጥቅምን ካልሆነ በስተቀር ለነርሱም ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። ፍትህ ፍትህ እኔም ድምፅ ነኝ ይህ ደግሞ የሰዒድ ዘሀበሻ መልዕክት ነው።
«ለሀገር ፡ በሚደረግ ፡ መልካም ፡ ነገር ፡ የሚሰነዘሩት ፡ አስተያየቶች ፡ ያሳፍራሉ ፡ ወደሀገር ፡ ቤት ፡ እየገባ ላለ ፡ ወገን ፡ መብትና ፡ ነፃነት ፡ ይጋፋል ፡ በእርግጥ በሌሎች ፡ ሀገር ፡ ስለአሉ ፡ ወገኖች ፡ ማስታወስ በስርአት ፡ የነሱም ፡ ጉዳይ ፡ በመንግሥትም በህዝብም ፡ በኢትዮጵያዊ፡ ጨዋነት ፡ ማቅረብሲቻል ፡ ውርጅብኙ ፡ የኢትዮጵያውያንን ፡ ችግር አስታኮ፡ ጠላቶችን ፡ ለማስደሰት ፡ መሆኑ ፡ ፍንትው ፡ያለነው። የሚለው ደግሞ የተክሌ ጋሻ አስተያየት

Atalanta Diaspora bei Benefizveranstaltung für Binnenvertriebene in Äthiopien
ምስል Tariku Hailu/DW
Raychelle Omamo und Antony Blinken
ምስል Andrew Harnik/Pool/AP/picture alliance

 

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ