1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሀሌታ ቱቶርስ፤የድረ-ገፅ የተማሪዎች አስጠኝ መድረክ

ረቡዕ፣ መስከረም 18 2015

በአሁኑ ወቅት ኑሮን ለማሸነፍ በሚደረገው የህይወት ውጣ ውረድ ሳቢያ ወላጆች ልጆቻቸው ከትምህርት ቤት የሚሰጣቸውን የቤት ስራ ለማገዝ በቂ ጊዜ የላቸውም።ጊዜ ቢኖራቸው እንኳ በትምህርቱ ይዘት ላይ በቂ እውቀት ላይኖራቸው ይችላል። ይህንን ችግር የተገነዘቡ ሶስት ወጣቶች ታዲያ ሀሌታ ቱቶርስ የተባለ የድረ-ገፅ አስጠኝ መድረክ ፈጥረዋል።

https://p.dw.com/p/4HTOD
Haleta Tutors
ምስል privat

አገልግሎቱ የእያንዳንዱን ተማሪ የትምህርት አቀባበል ደረጃ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚሰጥ ነው


በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጅ ልክ እንደ ሌሎቹ ዘርፎች ሁሉ የትምህርት አሰጣጥን በማሻሻል የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን በማሳደግ ረገድ  አሰተዋፅኦው ከፍተኛ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅትም ከወደ አዲስ አበባ  በሶስት ወጣቶች የተመሰረተ እና በድረ-ገፅ ተማሪዎችን በሚያስጠና አንድ ዲጅታል መድረክ ላይ ያተኩራል ።
በኢትዮጵያ የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ የተሻለ ውጤት ቢመዘገብም የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ ግን ብዙ ስራ የሚጠይቅ እና ብዙ ተግዳሮት ያለው መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። የትምህርት ጥራት ፈተናዎች  ተብለው ከሚጠቀሱት ነጥቦች መካከልም ንቁ የመማር ማስተማር ዘዴን በአግባቡ አለመተግበር፣ ውጤታማ የክትትልና የግምገማ ልምዶች አለመኖር፣  የተማሪዎች የመማር ፍላጎት ዝቅተኛ መሆን እና የመምህራን  የተነሳሽነት ማነስ  መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ  ያወጣው መረጃ ያሳያል።
ለነዚህ ችግሮች መነሻ ደግሞ የመምህራን -ተማሪዎች ጥመርታ ከፍተኛ መሆን፣ የመፃህፍት  እጥረት እንዲሁም ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ የሆነ አካባቢ አለመኖር  ይጠቀሳሉ።
ይህንን ችግር የተገነዘቡ ሶስት ወጣቶች ታዲያ  የበኩላቸውን ለመወጣት ሀሌታ ቱቶርስ/Haleta Tutors/ የተባለ የድረ-ገፅ  አስጠኝ መድረክ ፈጥረዋል።ሀሌታ ቱቶርስ ናትናኤል ዘውዱ፣ ቅዱስ ዮሀንስ እና ናትናኤል የወንድወሰን በተባሉ የቴክኖሎጅ ባለሙያዎች  በነሀሴ 2012 ዓ/ም የተመሰረተ ሲሆን፤ መነሻቸው እነሱ ያጋጠማቸው ችግር  መሆኑን  የመድረኩ  መስራች እና ስራ አስኪያጅ ወጣት ናትናኤል ዘውዱ ይገልፃል።
ሶስቱም ወጣቶች ሙያቸው ከኮምፒዩተር ሳይንስ እና ከሶፍትዌር ቴክኖሎጅ ጋር  የተያያዘ በመሆኑ ዲጅታል መድረኩን መመስረት ለእነርሱ ከባድ ባይሆንም፤ ወደ ስራ ሲገቡ ግን በርካታ ችግር ገጥሞን ነበር ይላል።
በዚህ ሁኔታ ችግሮችን አልፎ ስራ የጀመረው ሀሌታ ቱቶር አስጠኝ መድረክ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች እና በተለያዩ የጊዜ ሰሌዳዎች በሙያው ጥሩ ልምድ እና ዕውቀት ባላቸው አስጠኝዎች ከአፀደ ህፃናት /የኬጂ ተማሪዎች/  እስከ 12ኛ ክፍል ለሚገኙ ተማሪዎች የአንድ ለአንድ የማስጠናት አገልግሎት ይሰጣል። 
አገልግሎቱ የእያንዳንዱን ተማሪ የትምህርት አቀባበል ደረጃ ታሳቢ ባደረገ መልኩ  እና ተማሪዎች በሚፈልጉት መንገድ ባሉበት ቦታ ሆነው  አንድ ለአንድ የሚሰጥ በመሆኑ  የተማሪዎችን የመማር ተነሳሽነት በመጨመር እና የተማሪ -መምህር ጥመርታ ችግርን በመቅረፍ ረገድ አስተዋፅኦ አለው ይላል ።
በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት ኑሮን ለማሸነፍ በሚደረገው የህይወት ውጣ ውረድ ሳቢያ የወላጅ እና የልጆች ግንኙነት ውሱን እየሆነ መጥቷል።በዚህ የተነሳ ወላጆች  ልጆቻቸው ከትምህርት ቤት የሚሰጣቸውን የቤት ስራ ለማገዝ በቂ ጊዜ የላቸውም።ጊዜ ቢኖራቸው እንኳ በትምህርቱ  ይዘት ላይ  በቂ እውቀት ላይኖራቸው ስለሚችል ልጆቻቸውን ለማገዝ ይቸገራሉ።
ስለሆነም ይህ የድረ-ገፅ የትምህርት ማጠናከሪያ  አገልግሎት  ወላጆች በመቶዎች የሚቆጠሩ አስጠኝወችን የሚያገኙበት እና ለልጆቻቸው ተስማሚ የሆነውን ስዓት እና የትምህርት አይነት የሚመርጡበት በመሆኑ ናትናኤል እንደሚለው በእጅጉ ረድቷቸዋል።
በመድረኩ የእያንዳንዱ አስጠኝ ዝርዝር መግለጫ ስም፣ፎቶ የትምህርት ደረጃ እና ልምድ፣ የአገልግሎት ዋጋ እና የአስጠኝው ፍላጎት እና ለሙያው ያለው ፍቅር  አብሮ የሚቀመጥ በመሆኑ  ወላጆች አስጠኝዎችን በዋጋ፣ በርዕሰ ጉዳይ፣ በክፍል ደረጃ እና በጊዜ ሰሌዳ እንዲያጣሩ ያስችላቸዋል። ትምህርቱ ከተጀመረ በኋላም አስጠኝዎች በእያንዳንዱ የትምህርት ሂደት ላይ ዝርዝር  ግምገማ የሚያቀርቡ በመሆኑ ወላጆች የልጆቻቸውን መሻሻል እንዲከታተሉ ያስችላቸዋል።ያ በመሆኑ ውጤታማነቱን በተመለከተ ከወላጆች ጥሩ ምላሽ ማግኘታቸውን ይገልፃል።
በአሁኑ ወቅት ከ1000 በላይ ተማሪዎችን በማስጠናት ላይ የሚገኘው  ሀሌታ ቱቶርስ፤ ለአስር ሰዎች ቋሚ ለ450 አስጠኝዎች ደግሞ ጊዜያዊ የስራ ዕድል ፈጥሯል። በዚህ ስራው አድናቆት ያተረፈው ከተማሪ ወላጆች ብቻ ሳይሆን በ2022 በግዙፉ የነዳጅ ኩባንያ ቶታል ኢነርጂ ባዘጋጀው ውድድርም  ምርጥ የዓመቱ ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያ ዘርፍ አሸናፊ በመሆን የ370,000 ብር ሽልማት  አግኝቷል።ይህ ሽልማትም በዘርፉ የበለጠ እንዲሰሩ እንዳበረታታቸው ይናገራል። 
ናትናኤል እንደሚለው ሦስቱ ወጣቶች በመጪዎቹ አመታት  የጀመሩትን የማስጠናት ስራ  ትልቅ እና አስተማማኝ የማስተማሪያ  መድረክ በማድረግ በአፍሪቃ ደረጃ  የመስፋፋት ፍላጎት አላቸው።ለዚህ ይረዳቸው ዘንድም አገልግሎቱን የበለጠ ለማዘመን ከድረ-ገፅ  አገልግሎቱ በተጨማሪ የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ በማበልፀግ በአሁኑ ወቅት ሙከራ ላይ መሆናቸውንም አመልክቷል።ባህር ማዶ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ቋንቋ የማስተማር ዕቅድ ይዘዋል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ጥራት ያለው ትምህርት ለማረጋገጥ ለትምህርቱ ዘርፍ የሚመደብ በጀት፣ የተማሪ-መምህር ጥመርታ ፣ በሙያው የሰለጠኑ መምህራን ፣ ጤናማ እና ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢ፣ ክትትል እና ግምገማ እንዲሁም በተማሪዎች የትምህርት አቀባበል ላይ የተመሰረተ ተስማሚ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ይህንን ማሟላት  ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ በሆኑ ሀገራት አዳጋች ነው።ስለሆነም የበይነ-መረብ አስጠኝ መድረኮች  በተመጣጣኝ ዋጋ ተማሪዎች ባሉበት ቦታ ሆነው  የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ ችግሩን በተወሰነ መልኩ እንደሚፈታ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።ከዚህ አኳያ እንደ ሀሌታ ቱቶርስ ያሉ መድረኮች ተጠናክረው ቢቀጥሉ በኢትዮጵያ በትምህርቱ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የተወሰነ ድርሻ ሊያበረክቱ ይችላሉ።

Haleta Tutors
ምስል privat
Haleta Tutors
ምስል privat
Haleta Tutors Logo
ምስል privat
Haleta Tutors Logo
ምስል privat

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 
ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ