1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ICC» የነባግቦን ክስ አቋረጠ

ማክሰኞ፣ ጥር 7 2011

ዘ ሄይግ ኔዘርላንድ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት (ICC) የቀድሞው የኮትዴቩዋር ፕሬዝደንት ሎሮ ባግቦ ላይ የመሠረተውን ክስ አቋረጠ። ሁለቱም ተጠርጣሪዎች ጠበቆች ለቀረበባቸው ክስ በቂ ማስረጃ ባለመገኘቱ ዳኞቹ ክሱን እንዲያነሱላቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል። 

https://p.dw.com/p/3Bbl4
Kombibild - Charles Blé Goudé und Laurent Gbagbo

ዘ ሄይግ ኔዘርላንድ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት (ICC) የቀድሞው የኮትዴቩዋር ፕሬዝደንት ሎሮ ባግቦ ላይ የመሠረተውን ክስ አቋረጠ። ፍርድ ቤቱ በጎርጎሪዮሳዊው 2010 ዓ.ም በሀገሪቱ ከተካሄደው ምርጫ በኋላ ከተፈጠረ ውዝግብ ጋር በተገናኘ  ለተፈፀሙ ወንጀሎች ባግቦን እና በወቅቱ የወጣቶች ሚኒስትር የነበሩት ሻርል ቤሌ ጉዴን ተጠያቂ አድርጎ ክስ መሥርቶባቸው ነበር። በዛሬው ዕለት ግን አቃቤ ሕግ በቂ ማስረጃ ማቅረብ እንዳልቻለ ያመለከቱት የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለቱንም ከክሱ ነፃ ብለዋቸዋል። የመሐል ዳኛው ኩኖ ታፎስር ውሳኔውን እንዲህ አሰምተዋል፤
«በእነዚህ ምክንያቶች ፍርድ ቤቱ በአብላጫ ድምፅ አቃቤ ሕግ ያቀረበውን ክስ የሚደግፍ ማስረጃ በሮም ውሳኔ አንቀፅ 66 መሠረት ማቅረብ አለመቻሉን በመግለጽ ወስኗል። ሎሮ ባግቦ እና ሻርል ብል ጉዴንም በመከላከያው መሠረት ከቀረቡባቸው ክሶች ሁሉ ነፃ በማለትም በአንቀጽ 81 መሠረት ባስቸኳይ እንዲለቀቁም አዝዟል።»
የዳኞቹ ውሳኔ በፍርድ ቤቱ ውስጥ የተቃውሞ እና ደስታ ጉምጉምታን አስከትሏል። ደጋፊዎቻቸውም ከፍርድ ቤቱ ውጭ ሲጨፍሩ ታይተዋል። የሁለቱም ተጠርጣሪዎች ጠበቆች ለቀረበባቸው ክስ በቂ ማስረጃ ባለመገኘቱ ዳኞቹ ክሱን እንዲያነሱላቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል። 

ሸዋዬ ለገሰ

አዜብ ታደሰ