«FB» በጀርመን ያለዉ እንቅስቃሴ እንዲጠብ ተደረገ
ሐሙስ፣ ጥር 30 2011በፊደራል ጀርመን መሥርያ ቤቶች እና ድርጅቶች የተሰጣቸዉን ሥልጣን እና ኃላፊነት በአግባቡ መጠቀማቸዉን የሚመረምረዉ ባለሥልጣን መስርያ ቤት በጀርመንኛ አጠራሩ «Bundeskartellamt» «FB» ፌስቡክ የተጠቃሚዎችን መረጃ ካላግባብ ሰብስቧል ሲል በጀርመን ፌስቡክ ያለዉን እንቅስቃሴን ማጥበቡ ገለፀ። የዩናይትድ ስቴትስ የሆነዉ የ«FB» አገልግሎት በጀርመን ሃገር ያሉ ተጠቃሚዎቹን መረጃ ከሚገባዉ በላይ በመሰብሰብ እና በየፈርጁ በማስቀመጥ ያላግባብ ተጠቅሟል ሲሉ በጀርመን መሥራያ ቤቶች እና ድርጅቶችን የሚቆጣጠረዉ ባለሥልጣን መስራያ ቤት ዋና ተጠሪ አንድርያስ ሙንድ ዛሬ ተናግረዋል። ዋና መስራያ ቤቱን ቦን ከተማ ያደረገዉ ይህ የጀርመን ባለስልጣን መስራያ ቤት በጀርመን የፊስቡክ አገልግሎት በተለይ መረጃን በመሰብሰብ ረገድ ገደብ ተደርጎበታል ብሏል። በጀርመን እንደ «ሜሴንጀር« «ዋትስ አፕ» «የፎቶግራፍ ማከፓቻን» የመሳሰሉ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ሁሉ ፊስቡክ በመጠቅለሉ እና ከሁሉም አገልግሎቶች የሚገኘዉ መረጃ በአንድ ቋት በመከማቸቱ ፌስቡክ ገበያዉን በሞኖፖል መቆጣጠሩን ይፋ በማድረግ የጀርመኑ ባለሥልጣን ቢሮ ተቃዉሞታል። የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካዉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቡድን ፌስቡክ የጀርመን ባለስልጣን መስርያቤት ርምጃን በመቃወም ክስ መመስረት እንደሚፈልግ ተዘግቦአል።
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ