1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

26ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 23 2014

26ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ አምና ተስተጓጉሎ ዘንድሮ ግላስጎው ላይ መካሄድ ከጀመረ ሦስተኛ ቀኑን ይዟል። በጉባኤው ግንባር ቀደም ከባቢ አየር በካይዮቹን ጨምሮ ከ100 በላይ ሃገራት ይሳተፋሉ። በኢንዱስትሪ ያደጉት ሃገራት ዛሬም ሙቀት አማቂ ጋዞችን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ ቁርጠኝነት አለማሳየታቸው እያነጋገረ ነው።

https://p.dw.com/p/42SqR
Glasgow COP21 Wolodymyr Selenskyj Präsident Ukraine
ምስል Phil Noble/empics/picture alliance

«26ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ»

 

ካሳለፍነው እሁድ ጀምሮ ግላስጎ ስኮትላንድ ላይ 26ኛው የተመድ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ በይፋ መካሄድ ጀምሯል። በጎርጎሪዮሳዊው 1992 ዓ,ም ሪዮ ዲጄኔሮ ብራዚል ላይ ከተካሄደው የመሬት ጉባኤ የተወለደው የመንግሥታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ በየዓመቱ የሚያካሂደው የባለድርሻዎች ጉባኤ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ COP ን መስርቶ ተከታታይ ስብሰባዎች ሲያካሂድ ቆይቷል። ባለፈው ዓመት በኮቪድ 19 ምክንያት ባይስጓጉል ኖሮ ዘንድሮ 27ኛውን ጉባኤ ነበር የሚያካሂደው፤ ሆኖም ከትናንት በስተያ እሁድ ጀምሮ ለሁለት ሳምንታት በግላስጎው የሚካሄደው 26ኛው ጉባኤ ወሳኝ ያላቸውን ሦስት ነጥቦች ለማሳካት መሰባሰቡን መድረኩን የሚያስተባብረው የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሥልጣናት እየተናገሩ ነው።

Indonesien | Suralaya Kohlekraftwerk
ምስል Bay Ismoyo/AFP/Getty Images

የጉባኤ ተሳታፊዎች በተለይም ለከባቢው አየር በሙቀት አማቂ ጋዞች መበከል ቀዳሚውን ሚና ያላቸው በኢንዱስትሪ የበለጸጉት ሃገራት የዓለም የሙቀት መጠን ከ1,5 ዲግሪ እንዳይበልጥ ፈጣን ርምጃዎች መውሰድ፤ በግልጽ የሚታይ የበካይ ጋዞች ቅነሳ ርምጃዎችን እንዲወስዱ ግፊት ማድረግ፣ እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ እየተጎዱ ያሉ ሃገራት ከለውጡ ጋር ተላምደው እና ለውጡን ተቋቁመው ለመኖር እንዲችሉ እንዲያግዝ ታስቦ ቃል የተገባው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ እውን ሆኖ ቢያንስ ግማሹ እንኳን ለዚህ ተግባር እንዲውል የሚሉት ዋነኛ መነጋገሪያ ነጥቦች ናቸው። ከ26ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ተመልካቹ ጉባኤ ጎን ሮም ጣሊያን ላይ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ለሁለት ቀናት የተካሄደው ቡድን 20 የሚባሉት ሃገራት ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችሉ ርምጃዎችን ለመውሰድ ቃል ቢገባበትም አባላቱ ቁርጠኝነት እንደማይታይባቸው ተነግሯል። በጉባኤው ላይ የተገኙት የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ወደ ግላስጎው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከመጓዛቸው አስቀድሞ በትዊተር ገጻቸው በጻፉት መልእክት የቡድን 20 አባላት በስብሰባቻው ማጠቃለያ ለመፍሄትው ቁርጠኛነታቸውን መግለጻቸውን በደስታ ቢቀበሉም ከሮሙ ጉባኤ ተስፋ ያደረጉበት ሳይሟላ ከተማዋን ለቅቀው መውጣታቸውን አመልክተዋል። በቡድን 20 ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግርም መሪዎች ከቃል በዘለለ ተግባራዊ ርምጃዎችን ካልወሰዱ ዓለም እየጨመረ በሚሄደው የሙቀት መጠን ምክንያት አደጋ ላይ መሆኗን ጉተሬሽ አጽንኦት ሰጥተዋል።

COP26 Gipfel in Glasgow
ምስል Alastair Grant/Pool/Getty Images

«እስካሁን ያለው የዓለም መሪዎች ቁርጠኛ ርምጃ አሁንም ዓለም በ2,7 ዲግሪ ጭማሪ አደጋ ላይ እያሳየ ነው። በቅርቡ ቃል የተገቡት ርምጃዎች ግልጽ እና ተአማኒ ቢሆኑ እንኳን በዚያም ላይ አንዳንዶቹ ላይ እውነተኛ ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነው አሁንም ወደ አየር ንብረት ውድመት እያጋደልን ነው። ለዚህ ተጨባጭ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ የሙቀት መጠኑ ከ2 ዲግሪ በላይ ከፍ ማለቱ ነው። ይኽ ደግሞ አደጋ ነው።»

አንቶኒዮ ጉተሬሽ በኢንዱስትሪ የበለጸጉት እና በዚህ ረገድ እያደጉ ያሉት ሃገራት ለእርምቱ ቀዳሚውን ሚና መውሰድና በየበኩላቸው ማስተካከያውን ባፋጣኝ እንዲያደርጉ አጥብቀው አሳስበዋል። «የሚያምታታ እና ያልተጨበጠ ሳይሆን እውነተኛ ስኬት በዚህ ረገድ ማግኘት የምንፈልግ ከሆነ የበለጠ ፍላጎት እና ተግባራዊ ርምጃ ያስፈልገናል። ይኽን ለማሳካት ደግሞ የተጠናከረ የፖለቲካ ፈቃደኝነትን ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ በቁልፍ ተዋናዮች መካከል መተማመን ያስፈልጋል። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ መተማመን ተጓድሏል። የተዓማኒነት ከፍተኛ ችግር አለ። በትላልቆቹ ኃይሎች መካከል አደገኛ አለመተማመን እያየን ነው። ይኽ ደግሞ በቡድን 20 አባላት መካከል፤ በአደጉ እና በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት መካከል እየወጡ ያሉትን ጨምሮ ይታያል። እናም የዚህ የቡድን 20 ዋነኛ ግብ መተማመንን እንደገና መፍጠር መሆን አለበት።»

በኢንዱስትሪ ያደጉት እና በማደግ ላይ ያሉት ሃገራት መካከል ያለው ፉክክር ላለፉት በርካታ ዓመታት የበካይ እና ሙቀት አማቂ ጋዞች ቅነሳ በታሰበለት መንገድ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። በዓለም ከፍተኛውን የካርቦን ዳይኦክሳይድ ክምችት ወደ ከባቢ አየር ከሚለቅቁ ቀዳሚ አምስት ሃገራት ቻይና፤ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ሕንድ፣ ሩሲያ እንዲሁም ጃፓን በቅደም ተከተል ሲሆኑ በጎርጎሪዮሳዊው 2018 ዓ,ም በተመዘገበው መሠረት የቻይና ብቻ 10,6 ቢሊየን ሜትሪክ ቶን ደርሷል። እንዲያም ሆኖ በቡድን 20 ጉባኤ ላይ እስከ መጪው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2050 ድረስ እንኳን ተጨማሪ የካርቦን ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ የኃይል ማመንጫ ስልቶችን ከመጠቀም ለመታቀብ ፈቃደኝነትና ቁርጠኝነት ሳያሳዩ ነው ወደ ግላስጎው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የተጓዙት።

England | Fridays For Future Demonstration in London | Greta Thunberg
ምስል Frank Augstein/AP Photo/picture alliance

የግላስጎው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የበርካታ ሃገራት መሪዎች በአካል የሚገናኙበት መድረክ እንደመሆኑ የተሻለ ውጤት የሚጠብቁበት ባይጠፉም ትርጉም ያለው መግባቢያ ላይ መድረሱ አንድ ነገር ሊሆን እንደሚችልም የሚናገሩ አሉ። የጉባኤው አስተናጋጅ ብሪታኒያ በዚህ መድረክ አንዳች ውጤት መገኘት አለበት፤ ሞት ወይ ሽረት አይነት ማሳሰቢያ እያቀረበች ነው። ያለፉትን ትተን በዚህ በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በ2021 ብቻ በመላው ዓለም በተለያየ መልኩ የተገለጸው የተፈጥሮ ቁጣ ለዚህ ጉባኤ ተሳታፊዎች ተጨባጭ ማመላከቻ እንደሆነ ነው የተመድ ያመለከተው። በዚህም ምክንያት ጉባኤው ሲጠበቅ የቆየው የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊታይበት የሚገባው የመጨረሻ ዕድል ተደርጎ ተወስዷል። ምንም እንኳን ከጉባኤ አስቀድሞ አንዳንድ ሃገራት ቁርጠኝነታቸውን እያደሱ መሆኑን ቢያመላክቱም የዛሬ  ስድስት ዓመት ፓሪስ ላይ መንግሥታት የተስማሙበት የበካይ ጋዞች ቅነሳ ተግባራዊ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ካልተደረገ በቀር በምዕተ ዓመቱ አጋማሽ ማለትም በ2050 የመሬት ሙቀት 2,7 ዲግሪ ሊደርስ እንደሚችልም አስጠንቅቋል።

የዘርፉ ምርምር በግልጽ እንዳሳሰበው በዓለም የሙቀት መጨመር ምክንያት የተፈጥሮ አደጋዎች በከፍተኛ ፍጥነት ከመከሰት አልፈው እየተደጋገሙ ነው። በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ የሰደድ እሳት፤ ድርቅ እና ጎርፍ በየቦታው መከሰታቸው ተባብሷል። ከሰሃራ በስተደቡብ ያሉም ሆኖ የደሴት ሃገራት ለእነዚህ የተፈጥሮ ቁጣዎች ተጋላጭነታቸው ጨምሯል። በዚህ ምክንያት በሚሊየኖች የሚገመቱ ሰዎች ከአካባቢያቸው ለመፈናቀል ተገደዋል። ሰዓቱ መድረሱን እያመለከተ መሆኑን ያሳሰበው የተመድ በቀጣይ ስምንት ዓመታት ውስጥ ዓለም የበካይ ጋዞችን ልቀት በግማሽ መቀነስ ካልቻለ መዘዙ የከፋ እንደሚሆንም አስጠንቅቋል። በተፈጥሮ አደጋዎች እየተጎዳች የምትገኘው አፍሪቃ ለዚህ ጉባኤ ድምጿን ከፍ አድርጋ ማሰማት ከጀመረች ከርማለች። 54ቱ የአፍሪቃ ሃገራት ለከባቢ አየር ብከላው በጥቅሉ ያላቸው አስተዋጽኦ ከ8 በመቶ እንደማይበልች ነው የሚነገረው። ሆኖም ግን የመዘዙ ከፍተኛ ተጠቂዎች መሆናቸው በተግባር እየታየ ነው። የዓለም ሜቴሬዌሎጂ ድርጅት በቅርቡ እንዳመለከተው በሙቀት መጨመሩ ምክንያት አፍሪቃ ውስጥ ያሉ ግግር በረዶዎች እንደሚቀልጡ  ምልክቶች መታየት ጀምረዋል። ለማሳያም 5,200 ሜትር ከፍታ ያለው የኬንያ ተራራ ላይ የሚገኘው ግግር በረዶ እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2040 ድረስ እንደሚጠፋ ጠቁሟል።

UK Glasgow | Protest vor COP26
ምስል Andrew Milligan/PA Wire/picture alliance

በጎርጎሪዮሳዊው 2009 ዓ,ም በኢንዱስትሪ የበለጸጉት ሃገራት በአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ የተጋለጡ ድሀ ሃገራት ለውጡን ተላምደውን ተከላክለው ለመኖር እንዲችሉ በየዓመቱ የ100 ቢሊየን ዶላር ርዳታ ለመስጠት ቃል ገብተዋል። ገንዘቡንም እስከ 2020 ድረስ ለማሰባሰብ ነበር የታሰበው። ሆኖም እስከ 2019 ድረስ የተሰባሰበው 80 ቢሊየን ዶላር ብቻ ነው። ከዚህ ገንዘብ 43 በመቶው ለእስያ ሃገራት የሚሰጥ ሲሆን ለአፍሪቃ 26 በመቶው ይደርሳታል። 17 በመቶ ደግሞ ለላቲን አሜሪካ ሃገራት ነው የሚሰጠው። ሆኖም የታሰበው ገንዘብ ሊሟላ የሚችለው በ2023 መሆኑ ነው የተሰማው። የተገባው ቃል መዘግየት አፍሪቃን እንዳሳዘነ ነው። በአንድ ወገን ድርቅ በሌላው በኩል ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ፣ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝን ጨምሮ የተለያየ የተፈጥሮ ቁጣ ለሚፈራረቅባት አፍሪቃ ሊደረግ የሚገባው ድጋፍ ከተጠቀሰው የገንዘብ መጠንም ከፍ ሊል እንደሚገባ የሚከራከሩ ወገኖች አሉ። በዩጋንዳ የማካራሬ ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብረት ምርምር ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ዴቪድ መፍቱሙኩዛ ጉዳዩ የሞት ሽረት መሆኑን ይናገራሉ።

«ይኽ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ተከታታይ ጥፋት እና ውድመት እየደረሰብን ነው፤ ከድርቅ ጋር የተያያዙ ሌሎች እንደ ጎርፍ ያሉት እየደረሱ ነው። ይኽ ደግሞ ተራ ወሬ ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚታይ ነው። ስለምግብ ነው የምናገረው፤ ስለዚህ በዚህ ምክንያት ለበርካታ ሰዎች የሚሆን ምግብ ማቅረብ የማንችልበት ከፍተኛ ስጋት መኖሩን ነው የምንናገረው።»

Südafrika Global Ideas | The Karoo
ምስል Henner Frankefeld/DW

በቅርቡ የወጣ መረጃ እንደሚያሳው የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው ድርቅ አፍሪቃ ውስጥ ከጎርጎሪዮሳዊው 1970 ዓ,ም ጀምሮ ከ700 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በአሁኑ ጊዜም ከ400 ሚሊየን በላይ ሕዝብ በአህጉሪቱ በድህነት ሕይወቱን ይገፋል። የአየር ንብረት ለውጥ በተፋጠን መጠን ደግሞ ይኽ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ነው የዓለም ሜትሪዎሎጂ ድርጅት ያመለከተው።

እናም ከሁለት ሳምንቱ ድርድር እና ውይይት በኋላ የሚተላለፈው ውሳኔ ይጠበቃል።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ