1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

25 ኛዉ የሆሎኮስት መታሰብያ

ሐሙስ፣ ጥር 27 2013

አይሁዳዉያን ማሰቃያ ጣብያ ከናዚ ቁጥጥር ነፃ የሆነበት 76ኛ ዓመት ባለፈዉ ሳምንት በዓለም አቀፍ ደረጃ ታስቦአል። ይህ ቀን በህግ ፀድቆ ጀርመን ዉስጥ ሲታሰብ ዘንድሮ 25ኛ ዓመቱን ይዞአል። ለምን እንዲህ ዘገየ? መልሱን የሚሰጡን ምሑር አነጋግረናል።

https://p.dw.com/p/3otp9
Deutschland Holocaust Gedenktag Bundestag Berlin
ምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

 

ጥር 20 ፤ 2013 ዓ.ም ሃሙስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሆሎኮስት ቀን ታስቦ ዉሎአል። አይሁዳዉያን በናዚ በግፍ የተጨፈጨፉበት ግዙፍ የሚባለዉ የናዚ እና ግብራበሮቹ የሰዎች ማሰቃያ ጣብያ ከናዚ ቁጥጥር ነፃ የሆነበት 76ኛ ዓመት ቀን ነዉ።  ከጎርጎረሳዉያኑ 1933 እስከ 1945 ዓ.ም ድረስ በናዚ ጀርመን ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑ የአዉሮጳ ይሁዲዎች ተጨፍጭፈዋል። ጀርመን ይህን ግፍ ሁለተኛ እንዳይደገም ሲል ፤ ወጣቱ ትዉልድ ከዚህ ጥቁሩ የሰዉ ልጅ ታሪክ እንዲማር በየዓመቱ የሆሎኮስት መታሰብያ ቀን ስትል በሕግ ደንግጋ ማሰብ ከጀመረች ይህዉ ዘንድሮ 25 ኛ ዓመት ተቆጥሮአል።  ዘንድሮ በጀርመን ፓርላማ ቡንደስታግ በተካሄደዉ ሥነ-ስርዓትም በናዚ ጀርመን የተጨፈጨፉ ስድስት ሚሊዮን ይሁዲዎች ብቻ ሳይሆን የታሰቡት ፤ በጀርመን ይሁዲዎች መኖር የጀመሩበት 1700 ኛ ዓመትም በደማቅ ተከብሮአል። ሆሎኮስት ግን ምንድ ነዉ? በጀርመን ታዋቂ ደራሲ የሆኑት ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አሥራተ ካሳ፤ በጀርመን የአፍሪቃና የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች አማካሪ ናቸዉ፤ ሆሎኮስት ምንድን ነዉ ስንል ጠይቀናቸዋል።

Deutschland Holocaust Gedenktag Bundestag Berlin
ምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

« የሆሎኮስት መታሰብያ ተብሎ የሚታሰበዉ እለት ፤ ከዛሬ 25 ዓመት ጀምሮ በመታሰብያነት በሕግ ፀድቆ እየታሰበ ያለ ቀን ነዉ። በጀርመን ሃገር ለመታሰብያ እንዲሆን በህግ እንዲወጣ ያደረገዉ በዝያን ጊዜ የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ሮማን ሄርዞግ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአዶልፍ ሂትለር ጁንታ መንግሥት እና የናሽናል ሶሻሊዝምን አፀያፊ ተግባር የቆመበት የመጨረሻዉን ቀን ነዉ።   ከሁለም በላይ ጀርመን ሃገር ዉስጥ በብዛት ከሚገኘዉ፤ የማጎርያ ጣብያዎች ትልቁን ቦታ ይዞ የሚገኘዉ አዉሽቪትዝ የሚባለዉ ቦታ የተለቀቀበት ነዉ። አዉሽቪትስ የሚገኘዉ በፖላንድ ሲሆን ወደ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ የአዉሮጳ አይሁዶች በግፍ የተጨፈጨፉበት ቦታ ነዉ።  ስለዚህ ይህን ቦታ እና ሟቾችን ለማሰብ ለመዘከር፤ ነዉ ሆሎኮስት ማለት በናዚ ጀርመን የተጨፈጨፉ አይሁዶች መታሰብያ ቀን ማለት ነዉ።»

Deutschland Holocaust Gedenktag Bundestag Berlin
ምስል Odd Andersen/REUTERS

በዚህ በሆሎኮስት ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑ አይሁዶች በግፍ እንደተገደሉ ይነገራል። ይህንስ ታሪክ ይነግሩናል?

« እንደሚባለዉ በአስራ ሁለት ዓመት ዉስጥ ከ 1933 እስከ 1945 ዓ.ም ድረስ ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑ አዉሮጳዉያን ተጨፍጭፈዋል።  በአዉሽቪትስ በትሬብሊንካ እና በሌሎች የማጎርያ ጣብያዎች  ነዉ ተገደሉት። አብዛኛዉን የተገደሉት በጋዝ ነዉ።  ሆሎኮስት በሰዉ ልጅ ታስቦ ተወጥኖ ሰዉን በግፍ ለመጨረስ የተካሄደ አሳዛኝ የሰዉ ልጅ ምዕራፍ ነዉ ለማለት እንችላለን።»

To the Point Sendung Asfa Wossen Asserate
ምስል DW

ጥር 20 ፤ 2013 ዓ.ም በቡንደስታግ ወይም በጀርመን ፓርላማ በነበረዉ ሥነ-ስርዓት ላይ ተጋብዘዉ ንግግር ያደረጉት በጀርመን የአይሁዶች ተጠሪ ቻርሎተ ክኖብላሁ ናቸዉ። ቻርሎተ በፓርላማዉ ንግግር ሲያደርጉ እጅግ ከፍተኛ ጭብጨባን ተቸረዋል። በሦስት ዓመታቸዉ ቤተሰቦቻቸዉ በናዚ ወታደሮች የተገደሉባቸዉ ቻርሎተ ፤ እንዴት ሰዉ ደብቆአቸዉ እንዳመለጡ ፤ እንዴት ተሰደዉ እንደሄዱ ከዝያም ወደ ጀርመን ተመልሰዉ መምጣታቸዉን እና ለጀርመን ያላቸዉን ፍቅር በከፍተኛ ሁኔታ ገልጸዋል።

«እዚህ ከፊታችሁ ስቆም እንደ  አንድ ኩሩ ጀርመናዊ ነዉ ። አብዛኞቹ አይሁዳዉያን  ለጀርመን ከፍተኛ ፍቅር አላቸዉ። እዚህ የሚኖሩት አብዛኞቹ አይሁድ ጀርመናዉያን ተመሳስለዉ እንደራሳቸዉ ሃገር ሆነዉ መኖርን ይፈልጋሉ። ክቡራን እና ክቡራት በጀርመናዊነታችን መኩራት ይገባናል።  በመቀጠልም ለጀርመን በጋራ እንቆማለን። » በጀርመን ፓርላማ ቡንደስታግ በነበረዉ የመታሰብያ ሥነ-ስርዓት ላይ ሌላዋ ተናጋሪ ትዉልደ  ዩክሬናዊ ጀርመናዊትዋ አይሁዲ ናቸዉ። ወጣትዋ የታሪክ አስተማሪ አያቶቻቸዉ እንዴት እንደተገደሉ። አሁን ያላቸዉን ኑሮ ሁሉ ተርከዋል።

Deutschland 25 Jahre Holocaust-Gedenken im Bundestag | Marina Weisband
ምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

አይሁዳዉያን በናዚ በግፍ የተጨፈጨፉበት ግዙፍ የሚባለዉ የናዚ እና ግብራበሮቹ የሰዎች ማሰቃያ ጣብያ ከናዚ ቁጥጥር ነፃ የሆነበት 76ኛ ዓመት መታሰብያን በተመለከተ በጀርመን የአፍሪቃና የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች አማካሪን ልዑል አስፋ ወሰን አስራተን ጠይቀናቸዋል። በቡንደስታግ ማለትም በጀርመን ፓርላማ የተካሄደዉንም ሥነ-ስርዓት ይተርካሉ። ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነዉ እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

 

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ