1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአየር ንብረት ለውጥ ተመልካች ጉባዔ በፖላንድ

ሰኞ፣ ኅዳር 24 2011

በፖላንድ የካቶቪትስ ከተማ ዛሬ ከተጀመረው 24ኛው የተመ የአየር ለውጥ ተመልካች ጉባዔ የምድር ሙቀትን በመቀነሱ ረገድ ብዙ ይጠበቃል። ድርቅ እና ጎርፍ የሚያሰጋቸው ሃገራት ይህንኑ 12 ቀናት የሚቆየውን ጉባዔ የበለጸጉ ሃገራት በፀረ አየር ንብረት ለውጥ ትግሉ ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅዕዖ እንዲያደርጉ የሚያሳስቡበት እንደሚሆን ጠበብት ጠቁመዋል።

https://p.dw.com/p/39M9u
UN-Klimakonferenz 2018 in Katowice, Polen
ምስል picture-alliance/Zuma Press/Le Pictorium Agency/S. Souici

የካቶቪትስ የአየር ንብረት ለውጥ ተመልካች ጉባዔ

ድርቅ፣ ኃይለኛ ዝናብ ፣ ጎርፍ፣ ብርቱ ሙቀትን በመሳሰለው የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ ከሁሉም አህጉራት አብዝቶ የተጎዳው አፍሪቃ ነው። በፖላንድ ካቶቪትስ ከተማ ዛሬ በተከፈተው የተመድ አየር ንብረት ጉባዔ ላይ የተገኙት አፍሪቃውያኑ ልዑካን ቃል አቀባይ ሰይኒ ናፎ ለ DW እንደተናገሩት ግን ለአየር ንብረት ለውጥ የአፍሪቃ ድርሻ ንዑስ ነው። በዚህም የተነሳ ለአየር ንብረት ለውጥ ያን ያህል ተጠያቂ ባትሆንም፣ የዚሁ ክስተት መዘዝ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ የሆነችው የአፍሪቃ የልዑካን ቡድኖች ዛሬ በፖላንድ ወደተጀመረው 24ኛው የአየር ለውጥ ጉባዔ ፣ COP 24 የሄዱት ለአህጉራቸው አስፈላጊው ርዳታ ይገኛል የሚል ተስፋ ሰንቀው ነው።  በብዙ ቦታዎች በየዕለቱ የሚከሰተውእና  ከባድ መዘዝ የሚያስከተለው ድርቅ፣ ኃይለኛ ጎርፍ እና ብርቱ ሙቀት ከሀገራቱ ጠቅላላ ምርት መካከል ከአምስት እስከ 10 ከመቶ እንደሚያወድም ናይጀሪያዊው የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ኒሞ ባሲ ለ DW በሰጡት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።
« ተራው ሰው በተለያዩት የአየር ንብረት ለውጥ ተመልካች ጉባዔዎች  የተደረሱ ውሳኔዎች ያስገኙትን ውጤት አላየውም። ህዝብ በግልጽ እያየ ያለው  በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙቀት መጨመሩን፣ የአየር ፀባይ ለውጥን፣ በምግብ ምርት ላይ የተደቀነውን ፈተና ፣ ባህሮችና ውቅያኖሶች የገጠማቸውን ተግዳሮት ነው። እና ይህ ሁሉ ስጋት ያሳደረበት ህዝብ  ታድያ አንድ ነገር መደረግ እንዳለበት ይሰማዋል። »
አህጉሩ ወደፊት ከአየር ንብረቱ ለውጥ ብዙ አሳሳቢ መዘዝ አብዝቶ ሊጎዳ እንደሚችል የተመድም አስጠንቅቋል። በአየሩ ሙቀት እየጨመረ በሚሄድበት ችግር በአህጉሩ በጎርጎሪዮሳዊው 2020 ዓም እስከ 250 ሚልዮን ሰዎች አሳሳቢ የውኃ እጥረት ይጎዳል። የሙቀቱ ጭማሪ ከሁለት ዲግሪ ሴንቲግሬድ ከበለጠ ከአፍሪቃውያን መካከል ግማሹ በምግብ እጥረት ይሰቃያል። የአየር ንብረት ለውጥ ልማታችንን መና የሚያደርግበት አቅም እንዳለው  ሰይኒ ናፎ አስጠንቅቀዋል። 
«  እውነታው የአየር ንብረት ለውጥ ገሀድ መሆኑ፣ የማይጠፋ መሆኑ፣ ምንም እንኳን ጉዳዩ ቢያሳዝንም፣ አፍሪቃውያት ሀገራት ለችግሩ ያን ያህል ተጠያቂ ባይሆኑም፣ ዋነኛ ተጋላጭ መሆናቸው  እና  ከሁሉም የበለጠ መሰቃየታቸው ነው።  ይሳካልን አይሳካልን  ችግሩን ለመታገል እንታገላለን። ከኛ ጋር ለመስራት ፈቃደኛ ከሆኑትም ጋር እየሰራን ነው። እንደሚመስለኝ፣ ብዙኃኑ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ከልብ ለመታገል ይፈልጋሉ። » 
አፍሪቃውያኑ ልዑካን  ትኩረታቸውን ያሳረፉት ከሦስት ዓመት በፊት በፓሪስ በተካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ተመልካች ጉባዔ ላይ የምድርን ሙቀት ወደ 1,5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ዝቅ ከማድረጉ ዓላማ ጎን አፍሪቃውያት ሃገራት የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉበት ርዳታ፣ ሀብታሞቹ ባለ ግዙፍ ኢንዱስትሪ መንግሥታት እስከ 2020 ዓም ድረስ በየዓመቱ 100 ቢልዮን ዶላር መክፈል ይገባቸዋል ለሚለው ሀሳብ ነው። ሆኖም፣ ይህን ርዳታ በተመለከተ እስካሁን በተጨባጭ የተገባ ቃል እንደሌለ ሰይኒ ናፎ ገልጸዋል። አንዳንድ የተመ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ኮሚሽን የአየር ፀባይ ጉዳይ ጠቢብ ጄምስ ሙሮምቤድዚን የመሳሰሉ አፍሪቃውያን ፣ አህጉሩ በብዛት በግብርና ላይ ጥገኛ በመሆኗ 100 ቢልዮን ዶላር በዓመት በቂ እንዳልሆነ ይናገራሉ። 
« በአየር ንብረት ላይ የሚታየው ለውጥ የግብርና አውታራችንን ለትንበያ የማይመች፣ የመስኖውን አውታር ተጨማሪ ወረት የሚጠይቅ አድርጎታል።  የመስኖው አውታርም ቢሆን ግን  በተለያዩት ለውጦች መነካቱ አልቀረም።  በአየር ሙቀት ላይ የሚታየው ለውጥም የሰብል እና የእንሰሳት ምርት ላይ ተፀዕዕኖ እያሳረፈ ነው። »
የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝን ለመታገል አስፈላጊ የሆነው የጋራ ጥረት በብዙ ሃገራት ውስጥ ተነቃቅቶ  መታየቱ አበረታች ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል ሰይኒ ናፎ  ተስፋቸውን ገልጸዋል። 
 « በአየር ንብረት ላይ የሚታየው ለውጥ የግብርና አውታራችንን ለትንበያ የማይመች፣ የመስኖውን አውታር ተጨማሪ ወረት የሚጠይቅ አድርጎታል።  የመስኖው አውታርም ቢሆን ግን  በተለያዩት ለውጦች መነካቱ አልቀረም።  በአየር ሙቀት ላይ የሚታየው ለውጥም የሰብል እና የእንሰሳት ምርት ላይ ተፀዕዕኖ እያሳረፈ ነው። »

UN-Klimakonferenz 2018 in Katowice, Polen | Teilnehmerinnen aus Nigeria
ምስል Getty Images/AFP/J. Skarzynski
UN-Klimakonferenz 2018 in Katowice, Polen | Antonio Guterres, UN-Generalsekretär
ምስል picture-alliance/NurPhoto/J. Arriens

አርያም ተክሌ/ዳንየል ፔልስ

ሸዋዬ ለገሠ