1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

2020 ፖለቲካዊ ጣጣ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 26 2013

የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ወደ ባግዳድ አዉሮፕላን ማረፊያ ይጓዙ የነበሩትን የኢራን የጦር ጄኔራል ቃሲም ሱሌይማኒያን፣ የኢራቅ አቻቸዉን ጄኔራል አቡ መሕዲ አል ሙሐንዲስን እና ሌሎች የሁለቱ ሐገራትን ከፍተኛ ባለስልጣናትን በሚሳዬል ገደለ።ጥር 3።ለአሜሪካ-እስራኤል-ሳዑዲ አረቢያዎች ብሥራት።

https://p.dw.com/p/3nVTU
Silvester und Jahreswechsel zu 2021
ምስል Sebastian Kahnert/dpa/picture alliance

2020 የዓለም ዓበይት ፖለቲካዊ ክንዉኖች

ዘመኑን በግሪጎሪያኑ ቀመር የሚያሰለዉ የአብዛኛዉ ዓለም ሕዝብ በየዓመቱ ይኼኔ እንደሚያደርገዉ ሁሉ ሰሞኑንም 2020ን ሸኝቶ 2021ን ሲቀበል የሸኘዉን ዓመት ክስተት በጣሙን ኮሮና የተባለዉ መቅሰፍት እስካሁን ያደረሰዉን ጥፋት ለታሪክ  ዝክር ሲዘግብ፣  የመጪዉን በጎነት በዱዓ-ፀሎቱ ተመኝቷል።ሰዉ፣ ከ1,8 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ከፈጀዉ ክፉ ደዌ ጋር  የገጠመዉ ትግል ዓመቱ ማብቂያ ላይ በጀመረዉ ክትባት መሳሪያነት ለድል መብቃት አለመብቃቱን ለማየት «ዕድሜ ይስጠን» ከማለት ምኞት በላይ በርግጥ ማረጋገጪያ የለንም።ባለፈዉ ሐሙስ-ለዓርብ አጥቢያ የተሰናበተዉ 2020 የሚዘከርበትን ዓበይት ፖለቲካዊ ጉዳዮች ግን ባጭሩ መቃኘት አይገደንም።ከአፍሪቃና አዉሮጳ በስተቀር በሌላዉ ዓለም የሆነዉን ነካክተን አዲሱን ዓመት እንቀበል። 
ቀዝቀዝ፣ ደብዘዝ፣ ፈንጠርጠር፣ በተንተን፣ ጭር-ጭል ባለ ድግስ-ፀሎት፣ምኞት፣በተሸኘዉ 2020 ዓለም ላይ የሆነዉ ዳግም እንዳይመጣ ያልተመኘ የለም።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽን እንጥቀስ።
*«2020 የፈተና፣ የመቅሰፍትና የለቅሶ ዓመት ነበር።ኮቪድ19 ሕይወታችንን አናግቶ፣ ለስቃይና ሰቆቃ ዳርጎናል።ብዙዎች ተወዳጆቻቸዉን አጥተዋል።አዲስ የበሽታና የሞት ማዕበል አስከትሎብናል።ድሕነት፣ መበላለጥና ረሐብ ተስፋፍቷል።ስራዎች ጠፍተዋል።እዳዎች ተከምረዋል።ልጆች ተፈትነዋል።የቤት ዉስጥ ጥቃት ጨምሯል።የትኛዉም ሥፍራ ለደሕንነት ያሰጋል።»

Iran General bei Raketenangriff im Irak getötet - Ghassem Soleimani
ምስል Office of the Iranian Supreme Leaderpicture alliance/AP/picture alliance

አጀማመሩም ከቀደማዊ ዓመት በወረሰዉ ጠብ፣ግጭት፣ግድያ ላይ ጡንቸኞች ሌላ ፍጅት-ግድያ ለመጨመር ዳርዳር ያሉበት ነበር።ከአብዛኛዉ ዓለም ተስፈንጥራ በአራዊት-እንስሳ፣በዱር-ተራራ፣ ሙቀት-ልምላሜ ያሸበረቀችዉ አዉስትሬሊያን የሚያጋየዉን እሳት መጨረሻ ለመታዘብ ዓለም ጆሮ-ዓይኑ ከየቴሌቪዥኑ ላይ እንደሰካ ከወደ ባግዳድ የአዲስ ግድያ ዜና ሰማ።
የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ወደ ባግዳድ አዉሮፕላን ማረፊያ ይጓዙ የነበሩትን የኢራን የጦር ጄኔራል ቃሲም ሱሌይማኒያን፣ የኢራቅ አቻቸዉን ጄኔራል አቡ መሕዲ አል ሙሐንዲስን እና ሌሎች የሁለቱ ሐገራትን ከፍተኛ ባለስልጣናትን በሚሳዬል ገደለ።ጥር 3።ለአሜሪካ-እስራኤል-ሳዑዲ አረቢያዎች ብሥራት።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ።
*«ትናንት ማታ፣ በእኔ ትዕዛዝ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኢላማዉን አነጣጥሮ በመታ ጥቃት፣ከመላዉ ዓለም ቁጥር አንድ አሸባሪ ቃሲም ሱሌይማኒን ገድሏል።»  
ለኢራን፣ ኢራቅ፣ ሶሪያ ሊባኖሶች መርዶ።ለተቀረዉ ዓለም የአዲስ ጦርነት ስጋት።የዋሽግተን-ቴሕራን መሪዎች ከ1979 ጀምሮ የገጠሙት ዉዝግብ፣ ሽኩቻ፣ ግድያና የእጅ አዙር መበቃቀል በዘመን ሒደት ናረ እንጂ አልቀዘቀዘም።የሱሌይማኒ ግድያም መበቃቀል፣ መዛዛት፣ መሻኮቱ ለመጪዉ ትዉልድም እንደሚቀጥል የሁለቱ ሐገራት አዛዉንት መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የተተኪዉ ትዉልድ አብነቶችም አረጋግጡት።የሱሌይማኒ ሴት ልጅ።
«አሜሪካ፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ ሊባኖስ፣ አፍቃኒስታን፣ የመንና ፍልስጤም ዉስጥ የከፈተችዉን አረመኒያዊ ጦርነት የሚያዉቁ፣ ምዕራብ እስያ ዉስጥ የሠፈሩት የአሜሪካ ወታደሮች ቤተሰቦች፣ የልጆቻቸዉን ሞት መርዶ ለመስታት ቀናት እያሰሉ ነዉ።»
ለጄኔራል ሱሌይማኒ ቀብር በታደመዉ ሕዝብ መሐል በተፈጠረ መገፋፋት 56 ሰዉ ሞተ።ከ200 በላይ ቆሰለ።ጥር 7። ዓመቱ ለኢራን መጥፎ የሆነዉ ገና ከጅምሩ ነዉ።እርግጥ ነዉ ቴሕራኖች እንደ ፎከሩት፣ ጦራቸዉ ኢራቅ የሚገኙ ሁለት የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ሠፈሮችን በሚሳዬል መትቷል።ሚሳዬሉ ያቆሰለ እንጂ የገደለዉ አሜሪካዊ የለም።ይልቅዬ ከሚሳዬሎቹ ቢንስ አንዱ  የዩክሬንን የመንገደኞች አዉሮፕላንን ቀድቦ ጥሎ፣አዉሮፕላኑ አሳፍሯቸዉ የነበሩ 176 መንገደኞችና ሠራተኞችን ፈጀ።ጥር 8።
ፕሬዝደንት ትራምፕ  «ቁጥር አንድ አሸባሪ» ያሏቸዉን ጄኔራል የማስገደላቸዉን ድል በቅጡ ሳያጣጥሙ ሥልጣናቸዉን «አላግባብ ተጠቅመዋል» የሚለዉን የዴሞክራቲትክ ፓርቲ ተቀናቃኞቸዉን ክስ ለመከላከል መባተል ነበረባቸዉ።
ጥር 16 የተጀመረዉ ክስ ለሳምንታት አሟግቶ የካቲት 5 ላይ አበቃ።ድሉ የትራምፕ ነበር«ለሳምንታትና ትናንትም በድጋሚ፣ፅኑዎቹ የሪፐብሊካን ፖለቲከኞችና መሪዎች ማንም ሰዉ ትክክል እንደሆነ የሚያዉቀዉን እዉነት ለመወሰን ብልሕነታቸዉን አረጋግጠዋል።»
የዴሞክራቶቹ የምክር ቤት መሪ ወይዘሮ ናንሲ ፔሎሲ ግን አልተበገሩም።«የፈለጉትን ቢሉም፣ የሚሹትን አርዕሥተ ዜና ቢይዙም፣ እስከወዲያኛዉ ድረስ ተከስሰዋል።ጠባሳዉም ይኖራል።»
ትንቢት ይሆን? አናዉቅም።ብቻ ባለፈዉ ሕዳር በተደረገዉ ምርጫ ነዉጠኛዉን፣ ፅንፈኛዉን ከፋፋዩን፣ሞገደኛዉን፣ ተሳዳቢዉን መሪ የአሜሪካ ሕዝብ «በቁን-በቃንዎት» አላቸዉ።
ጥር 30።የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትን ለዓለም ሕዝብ አስቸኳይ የጤና ችግር በማለት ሰየመዉ።የድርጅቱ የአስቸኳይ ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ዲዲዮ ሳር።«ዛሬ የአስቸኳይ ጊዜ ኮሚቴዉ፣ የኖቨል ኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት የዓለም ሕዝብ  አስቸኳይ የጤና ቀዉስ መሆኑን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።»
ኮሮና የያኔዉ አዲስ ዓመት፣ የመጀመሪያ ወር እስኪያበቃ ድረስ ከቻይና ዉጪ የያዘዉ ሰዉ ቁጥር 89 ብቻ ነበር።የዓለም ጤና ድርጅት የበላይ ኃላፊ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖም ያኔ እንዳሉት።«ባሁኑ ጊዜ ከቻይና ዉጪ በ18 ሐገራት 89 ሰዎች በተሕዋሲዉ ተይዘዋል።»
ኮሮና የዓለምን ሁለንተናዊ ሥርዓት ለማዘበራረቅ ሲያዘግም፣ «የሕንዱ ትራምፕ» የሚባሉት ጠቅላይ ሚንስትር ናረንድራ ዳሞዳርዳስ ሞዲ የቢሊዮኖቹን ሐገር ከራስዋም፣ ከቻይና-ፓኪስታንም ያላትሟት ነበር።የሒንዱ ብሔረተኛዉ ፖለቲከኛ አዲስ ያወጡትን የዜግነት ሕግ በመቃወም ደሊሕ ዉስጥ አደባባይ የወጣዉን ሕዝብ ለመበተን ፖሊስ በወሰደዉ ርምጃ 23 ሰዎች ተገደሉ።ከ200 በላይ ቆሰሉ።ቀኑም ደልሒ ላይ በሞቱት ሰዎች ቁጥር ልክ ነበር።የካቲት 23።

Symbolbild Black Lives Matter Schriftzug
ምስል David Ramos/Getty Images

የካቲት 29 ዩናይትድ ስቴትስና የአፍቃኒስታኑ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ታሊባን ቅድመ-ግድታ የበዛበትን የሰላም ዉል ተፈራረሙ።ዶሐ-ቀጠር የተፈረመዉ ስምምነት 20ኛ ዓመቱን የያዘዉን የሁለቱን ወገኖች ዉጊያ ለማስቆም፣ የአሜሪካ ጦርም ከአፍቃኒስታን እንዲወጣ እንደ ጥሩ ርምጃ ታይቷል።ስምምነቱ ገቢር ሳይሆን ግን ጊዜ-ጊዜን ሻረ።
ዘሔግ-ኔዘርላንድስ የሚያስችለዉ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት በአፍቃኒስታኑ ጦርነት የተፈፀመዉ የጦር ወንጀል እንዲመረመር የተወሰነዉ የዶሐዉ ስምምነት በተፈረመ ሳምንት ነበር።መጋቢት 5።ዉሳኔዉ ከፀና የአሜሪካ ወታደሮች ለሚጠረጠሩበት ወንጀል እንዲመረመሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘዘ ሕግ ነዉ።
የምያንማር ጦር በሮሒንጂያ ሙስሊሞች ላይ የሚፈፅመዉ ግፍ  እንደቀጠለ አምናም እንደ እስከ ሐቻምናዉ  መጥቶ ሄደ።የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ቢሮ እንዳስታወቀዉ የምያንማር መንግሥት ጦር ሚያዚያ አጋማሽ ብቻ 23 ሰላማዊ ሰዎችን በጄት ቦምብ ገድሏል።ዓለም አቤቱታ፣ ወቀሳ፣ ስሞታዉን ሰምቶ-ያዉ ሁሌም እንዳልሰማ አለፈዉ። 
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያደራጀችዉ የደቡብ የመን የሽግግር ምክር ቤት አደን ላይ መንግስት መመሥረቱን በርግጥ ብዙዉ ዓለም የሰማ አይመስልም።ያቺን ጥንታዊ፣ ታሪካዊ፣ ሥልታዊ ሐገርን ለሚያወድሙት ለሪያድ-አቡዳቢ-ካይሮ ገዢዎች ግን አሳሳቢ ነበር።ክፍፍል፣ ዉድቀትና ሽንፈትን ሊያስከትል የሚችለዉን ጣጣ ለማስወገድ ያኔ መራወጥ የጀመሩት የሪያድ ነገስታት ዓመቱ ማብቂያ ላይ የተሳካላቸዉ መስሏል።
ሪያዶች ያስጠጉት፣ የሚያዙና የሚያሽከረክሩት ስደተኛዉ የፕሬዝደንት አብድረቦ  መንሱር ሐዲ መንግሥትና የአቡዳቢዎቹ የሽግግር ምክር ቤት ተጣማሪ መንግስት መሰረቱ።ታሕሳስ 26።ሪያድ።አብድ ረቦ መንሱር ሐዲ የ«አዲሲቱ የመን» አዲስ መንግስት አሉት።
የአዲሲቱ የመን አዲስ መንግስት መሪዎች ባለፈዉ ሳምንት አደን ሲገባ ከአበባ  አኩል  የሚሳዬል፣ ቦምብ ፈንዳታም  ነበር-የተቀበላቸዉ።ፖለቲከኞቹ አልተጎዱም።26 ሰላማዊ ሰዎች ግን ሞቱ።የሪያድ-አቡዳቢዎች አንድነት ፀና።የመኖች ግን እብዙ ሥፍራ ተከፋፍለዉ፣ ዘር-ኃይማኖት፣ ታሪክ በሚጋሯቸዉ ጎረቤቶቻቸዉ አረቦች መርገፍ፣ መራብ፣ መታረዙን ለተጨማሪ ዓመት ቀጠሉበት።
ግንቦት 19፣ የፍልስጤሙ ፕሬዝደንት ማሕሙድ አባስ መስተዳድራቸዉ ከእስራኤልና ከዩናይትድ ስቴትስ  ጋር ያደረገዉን ስምምነት በሙሉ አቋረጡ።ምክንያት እስራኤል የዮርዳኖስ ሸለቆን ከግዛትዋ ለመጠቅለል ማቀዷን በመቃወም ነዉ።ግን ምን ሊያመጡ።
እንዲያዉም የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ባሕሬን፣ሱዳንና ሞሮኮ እየተግተለተሉ የእስራኤልን ወዳጅነት ተማፀኑ።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አረቦቹን አባብለዉ፣ አማልለዉ፣ አስፈራርተዉም ከእስራኤል ጋር ማወዳጀታቸዉ፣ ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያምን ኔታንያሁን ከመሰሉ ወዳጆቻቸዉ ምሥጋና አድናቆቱ መንቆርቆሩ በርግጥ ሲያንሳቸዉ ነዉ።
ክፋቱ ወይም ደግነቱ ሁለቱም 2021ን የተቀበሉት የጡረታ ዶሴያቸዉን ከየቢሯቸዉ እየሸከፉ ነዉ።የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ፀሐይ ፈንጠቅ፣ ደመቅ፣ ሞቅ እያለ የኮሮናን ግስጋሴ ላፍታ ረገብ ሲያደርገዉ ግንቦት፣ አሜሪካ ለጥቁር ዘር ጥላቻ ቆሌዋ ጆርጅ ፍሎይድን ሚኒፖሊስ ላይ ጭዳ አደረገች።ቄስ አል ሻርፕተን በፍሎይድ አስከሬን ሽኝት ላይ ሁሉንም አሉት።
 «በፍሎይድ ላይ የተፈፀመዉ፣ እዚች ሐገር ዉስጥ በየዕለቱ የሚደርስ ነዉ።በየትምሕርቱ፣ በየጤናዉ ተቋማት በሁሉም የአሜሪካ የኑሮ መስኮች በየዕለቱ የሚፈፀም ነዉ።በጋራ ቆመን፣ በጆርጅ ስም «ጉልበታችሁን ካንገታችን ላይ አንሱ» የምንልበት ጊዜ አሁን ነዉ።» 
በርግጥም  የድፍን ዓለም ጥቁር፣ክልስ፣የዘር ጥላቻን የሚጠየፈዉ ነጭም ከግንቦት ማብቂያ የጀመሮ አደባባዮችን በቁጣ ተቃዉሞ አጥለቀለቀዉ።«ብላክ ላይቭስ ማተር (የጥቁር ነብሶች ዋጋ አላቸዉ)» እንደ ተወዳጅ ሙዚቃ  ይዘመር፣ ይፈከር፣ ይንቆረቆር ገባ፤ ይፃፍ ይለጠፍ ያዘ።
ዓመታት ያስቆጠረዉ የሕንድና የቻይና የድንበር ግዛት ይገባኛል ጠብ-ዉዝግብ ከየካቲት ጀምሮ የጦር  ኃይል ቁርቁስ መልክና ባሕሪ ተላብሶ ሰኔ ላይ ነብስ ወዳጠፋ ግጭት ናረ።ሰኔ 15። ግራ ቀኝ የተፋጠጠዉ የሁለቱ ሐገራት ጦር ግላዋን ሸለቆ ላይ ተጋጭቶ 40 የቻይና፣ 20 የሕንድ ወታደሮች ተገደሉ ወይም ቆሰሉ።
ነሐሴ 4።ቤይሩት-ሊባኖስ ከምሽቱ 12 ሰዓት።ቤይሩት ወደብ መጋዘን ዉስጥ የታጨቀ ተቀጣጣይ ንጥረ ነገር ዉቢቱን፣ ዘመናይቱን ግን ደም የለመደችዉን  የባሕርዳር ከተማ አነደዳት።220 ሰዉ ገደለ።ሺዎችን አቆሰለ።3 መቶ ሺሕ ነዋሪዎችዋን አፈናቀለ።15 ቢሊዮን ዶላር አከሠራት።ፍንዳታዉ መንግሥቷን አፍርሶ፣ ሹማምንቶችዋን ወሕኒ አስዶሎ፣ የለጋሾችን ርዳታ እንዳማተረች ዓመቱ በዓመት  ተተካ።
ዓለም ስለ ቤይሩቱ ፍንዳታና ጥፋቱ መረጃ ሲቃርም የቀድሞዋ የሶቬትሕ ሕብረት ሪፐብሊክ ቤሎ ሩስ አወዛጋቢዉን ምርጫና ዉጤቱን አስተናገች።ነሐሴ 9። በምርጫዉ ሐገሪቱን ከ1994 ጀምሮ የገዙት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ አሸንፈዋል መባሉ የቀሰቀሰዉ ቁጣ ተቃዋሚዎችን ለድብደባ፣ ስደት፣እስራት ዳርጎ ዉዝግቡ እንደናረ 2020 አምና ሆነ።
ዓመቱ ለቀድሞዎቹ የሶቭየት ሕብረት ሪፐብሊኮች በተለይም ለአዛርበጃንና አርሜንያም ደም አፋሳሽ ነበር።ናጎርኖ ካራባሕ በተባለዉ ግዛት ሰበብ የሚወዛገቡት ሁለቱ ሐገራት 30 ዓመት ያዳፈኑት ጠብ  መስከረም ላይ ዳግም ነድዶ ሁለቱን ሐገራት ያጋይ ገባ።እስከ ሕዳር በዘለቀዉ ዉጊያ ከሁለቱም ወገን ሺዎች አለቁ። አስር ሺዎች ተፈናቀለ።ሕዳር ላይ ዉጊያዉ በሩሲያ አደራዳሪነት አበቃ።
«ዛሬ ሕዳር 9 የአዘርበጃን ፕሬዝደንት አሊየቭ የአርሜኒያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ፓሺኒያን እና የሩሲያዉ ፕሬዝደንት አጠቃላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራርመዋል።በሞስኮ አቆጣጠር ከሕዳር 10 እኩለ ሌት ጀምሮ በናጎርኖ ካራባሕ ግጭት የሚሳተፉ ወታደሮች እንቅስቃሴዎችን በሙሉ ይቆማሉ።»
የጦር ሜዳዉ ዉጊያ፣ የሞስኮዉ ዲፕሎማሲም ለአዘርበጃን ድል፣ ለአርሜኒያ ሽንፈት ነበር።አሊየቭ ከሞስኮ ባኩ ሲገቡ የጀግና አቀባበል ሲደረግላቸዉ፣ ፓሺኒያን ግን ጃርዋን የገጠማቸዉ ባደባባይ ሰልፍ «ዓይንሕ ላፈር» የሚል ሕዝብ ነበር።
ሕዳር 3 አሜሪካ የወዲፊት መሪዋን መረጠች።ከሳምንት ልብ አንጠልጥል ቆይታ በኋላ የዴሞክራቶቹ ዕጩ ጆ ባይደን አሸነፉ።አሉም።
«ዛሬ፣  አሸናፊዉን የሚያረጋግጠዉን የሚወክሉት የአስመራጭ ኮሌጅ አባላት ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንትና ምክትል ፕሬዝዳንቶች ድምፃቸዉን ሰጥተዋል።ርምጃዉ ለሐገራችን ለራስዋ ፍትሕን ያስከበረ ነዉ።አሜሪካ ዉስጥ የሕግ የበላይነት፣ ሕገ-መንግስታችንና የሕዝብ ድምፅ መከበሩ ዳግም ተረጋግጧል።»
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ሽንፈታቸዉን አልተቀበሉም።በአደባባይ ሰልፍ፣ በፍርድ ቤቶች ሙግት፣ በመገናኛ ዘዴዎች ቅስቀሳ ፣ አስመራጮችን በማስፈራራት የምርጫዉን ዉጤት ማስቀየር ወይም የአስተዳደር ዘመናቸዉ እንደሚታወቅበት ፈሊጥ «አማራጭ እዉነት» መፍጠር አልቻሉም።አሜሪካ ጉዳይ ባይ ትራምፕ ሲል ዓመቱም ላይመጣ ሔደ፣ ዓለምም- «ኮረና አለ ገና» እያለ 2021ን ተቀበለ።ዐርብ።መልካም አዲስ ዓመት።

Aserbaidschan übernimmt die Kontrolle über Lachin von Armenien
ምስል Emrah Gurel/AP Photo/picture alliance
Armenien Proteste
ምስል Asatur Yesayants/dpa/picture alliance
Kombobild | Donald Trump und Joe Biden

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ