1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2019 የመጀመሪያ መንፈቅ ፖለቲካዊ ሁነት

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 13 2012

የየኃይማኖቱ፣ ፀሎት፣ ቡራኬ፣ሰበካ ሞልቶ የፈሰሰበት መካከለኛዉ ምሥራቅ ዘንድሮም እንደ ድሮ-ጥንቱ ሰናይ እየተሰበከ እኩይ እንደሚፈፀምበት ለማረጋገጥ ይመስል የርዕሠ-ጳጳሳቱ ቡራኬ፣ፀሎት ምልጃ ከአቡዳቢ ሲንቆረቆር በአቡዳቢ ገዢዎች ትዕዛዝ የመኖች ያልቁ ነበር።ሶሪያዎችም ይገደሉ፣ይሰደዱ፣ ይፈናቀላሉም

https://p.dw.com/p/3VHZE
Treffen Kim und Trump Juni 2019
ምስል Reuters/K. Lamarque

2019 ከጥር-ሰኔ ዓበይት ፖለቲካዊ ክንዉኖች


ሩሲያዊዉ የኬሚስትሪ ሊቀ-ሊቃዉንት ዲሚትሪ ኢቫኖች ሜድንዴሌየቭ Periodic Table የተሰኘዉን የኬሚስትሪ ሰንጠረዥ ለዓለም ካስተዋወቀ 150ኛ ዓመቱን ደፈነ።2019። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረቂቁን የሳይንስ ግኝት ለመዘከር ዛሬ የሳምንት ዕድሜ የቀረዉን  2019ን 150ኛዉ የPeriodic Table መታሰቢያ በማለት ሰይሞት ነበር።
ከሳይንስ ምጡቅ ግኝቶች ባንዱ የተሰየመዉ ዓመት ግን እንደ ብዙ ቀዳሚዎቹ ሁሉ የሳይስንስ ቴክኖሎጂን ሰናይ-እኩይ ግኝትን በሐብት፣ እዉቀት ብልጠቱ የተቆጣጠረዉ ዓለም፣ ከኮሪያ ልሳነ ምድር እስከ ካሽሚር በኒኩሌር ቦምብ ሰዉን ሊያጫርስ እንደተዛዛተበት፤ በሚሳዬል፣ ቦምብ፣ ጥይት ከየመን እስከ ኮንጎ፣ ከፍልስጤም እስከ አፍቃኒስታን፣ ከሶሪያ እስከ ዩክሬን ሺዎችን እንዳረገፈበት ዘመን ተክቶ በዘመን ሊተካ ሳምንት ቀረዉ።2019።
ዓመቱ ዓለም ዓይታዉ የማታቀዉን የስደተኛ-ተፈናቃይ ሕዝብን አስቆጥሯት፣ ቦምብ-ሚሳዬል ጥይታቸዉ፣ አለያም ሐብት የማጋበስ ሴራቸዉ ያሰደደ፣ ያፈናቀለዉን ሰዉ የሚጥሉ፣ ከዘራቸዉ ዘር፣ ከኃይማኖታቸዉ ኃይማኖት የማይጋራዉን ሰዉ የሚጠየፉ፣ ለደሐ-ይበልጥ ዉድቀት-ድቀት፣ ለቱጃር -ሽቅብ-ምጥቀት፣ ይበልጥ-ምቾት የሚጣጠሩ ቀኝ ፖለቲከኞች የተጠናከሩበት ዓመትም ነዉ።
ከዓዉሮጳ በመለስ በተቀረዉ ዓለም የተከናወኑ አበይት ፖለቲካዊ ሁነቶችን ዛሬና በመጪዉ ሳምንት ሰኞ ጠቃቅሰን እንሰናበተዉ።
ከዘር ነጭን፣ከመደብ ሐብታምን፣ ከትብብር መነጣጠልን፣ ሰጥቶ ከመቀበል መንጠቅን፣ ከፍትሐዊነት በሐብት ጉልበት መታበይን የሚሰብኩት አሜሪካዊ ቱጃር ነጋዴ ዶናልድ ትራምፕ የትልቂቱን ሐገር ትልቅ ሥልጣን ከያዙ ከ2017 ወዲሕ የአዉሮጳ ቀኝ አክራሪ ፖለቲከኖች የልብ ልብ አግኝተዉ አንዳድ ሐገር አብያተ-መንግስታትን  ብዙ ሥፍራ ጠቀም ያሉ የአብያተ-መማክርት ወንበሮችን ተቆጣጥረዋል።
ቀኝ አክራሪዎች ለንደን፣ ቡዳፔሽት፣ ሮም፣ በርሊን፣ ቤርን፣ ፓሪስ፣ ስቶክሆልም በሌሎችም የአዉጳ ሐገራት ምክር ቤቶች  በርካታ መቀመጫዎችን መቆጣጠራቸዉ ብዙ ቢያነጋግርም ለብዙ ታዛቢዎች በብዙ ምክንያት «የሚጠበቅ» ሥለነበር  አላስገረመም።
በእግር ኳስ ድንቅ ጠበብ፣ ዓለም የሚዉቅ-የሚያደንቃት-፣ ለቀቅ-ዘና-ቀበጥ ባለ ባሕሏ፣በሳንባ ዳንኪራ፣ በካርኒቫል ቱማታዋ  የደመቀችዉ፣ ከሁሉም በላይ የስልጣኔን «ስይጣኔ» የረገጠ ዜጋዋን፣ ከደን ነዋሪዋ ጥንታዊ ትዉልዷ፤ ጥቁሩን ከነጩ፣ ክልሱን ከቢጫዉ አሰባጥራ የያዘችዉ ብራዚል ቅኝ ፅንፈኛ ፖለቲከኛን ከትልቅ የስልጣን ማማዋ መስቀሏ ግን ለብዙዎች በርግጥ አስደንጋጭ ነበር።
ግን ሆነ።2019ድም አንድ አለ።በ2018 ማብቂያ የተመረጡት የዶናልድ ትራምፕ ብራዚላዊ ቅጂ ያር ቦልሶናሮ ቃለ መሐላ ፈፀሙ።ጥር 1።«ብራዚል ከሶሻሊስቶችና ከቸከ ፖለቲካ ነፃ ወጣች» አሉ፣የቀድሞዉ መቶ አለቃ።ትራምፕን መስለዉ፣ ዓለም የተፈጥሮ መቅሰፍትን ለመቀነስ የሚያደርገዉን የጋራ ጥረት ልክ እንደ ትራምፕ ያጣጣሉት ቦልሶናሮ የሰዉ ጥፋት ያስከተለዉ የተፈጥሮ ጨካኝ በትር በዜጎቻቸዉ ላይ ሲወርድ ለማየት ወር አልጠበቁም።ብሩማዲንሆ ከተማ ላይ የተገነባዉ ግዙፍ የማዕድን ማንጠሪያ ግድብ ተደረመሰ።260 ሰዉ አለቀ።አንዱ የአድርያኖ ወንድም ነዉ።«አይታመነም።እዚሕ መስራት ከጀመርኩ 15 ዓመቴ ነዉ።ቤተሰቦቼን አጣሁ።ወዳጆቼን አጣሁ።» ጥር 25 ነበር።ኑሮ፣ ሕይወቱ በማዕድን ቁፋሮና ሽያጭ ላይ የተመሠረተዉ አብዛኛዉ የብሩማዲንሆ ነዋሪ ዛሬም ተፈናቃይ ነዉ።
ግንቦት 18። ቤለም በተባለች ከተማ መሸታ ቤት በተነሳ ጠብ 11 ሰዉ ተገደለ።
ግንቦት 26ና 27 የአራት የአማዞን ግዛት ወሕኒ ቤት እስረኞች ባበቀሉት ረብሻ  50 እስረኞች ተገደሉ።ቦልሶናሮ ብራዚልን ከሶሻሊስቶች እንጂ ከወንበዴዎች፣ ከአደንዛዥ ዕፅ ነጋዴዎች፣ከአጭበርባሪ፣ ሙስኞች ነፃ የሚያወጡበት ጊዜ እንደራቀ የዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወር አበቃ።
የዓረብ እስራኤሎች ጦርነት፣ዉዝግብ መሻጠር ለምዕተ-ዓመት ያክል የጋረደዉ፣ የአረቦች የርስበርስ ጠብ ቁርቁስ በ2011 ምርጊቱን በርቅሶ ሲፈነዳ ሶሪያን፤ሊቢያን፣ የመንን በጋራ ያፈረሱት፣ ኢራንን የገዘገዙት የሪያድ፣ዶሐ፣አቡዳቢ ነገሳስታት ወዳጅነት ከ2015 ጀምሮ ምንቅርቅሩ እንደወጣ ነዉ።
ዘንድሮ ጥር 2፣ ቀጠር፣ ሪያዶች የሚጫኑትን የዓለም የነዳጅ ላኪዎች ድርጅት (OPEC)ን ጥላወጣች።የዶሐ ገዢዎች ከአረቦቹ ራቅ፣ ወደ ቱርክ ፋርሶች ጠጋ ማለታቸዉ ያበገናቸዉ የሚመስለዉ የአቡዳቢ ነገስታት ከመካከለኛዉ ምሥራቅ፣ ከአረብ-ፋርስ-ቱርክ ከእስልምናም ራቅ ብለዉ የሮማ ካቶሊካዊት ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት ፍራሲስን አቡዳቢ ላይ ላይ አስተናገዱ።የካቲት 3።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ሙስሊሞች የሚበዙበትን የአረብ ባሕረ-ሠላጤን በመጎብኘት የመጀመሪያዉ የካቶሊክ ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት ሆኑ።«ባርኩ።ይሕ ክርስቶስ በማቲዎስ ወንጌል ሰበካ የጀመረበት ቃል ነዉ።በልባችን እንዲሰርፅ የፈለገ ይመስል ዛሬም ይደግመዋል።»
የየኃይማኖቱ፣ ፀሎት፣ ቡራኬ፣ሰበካ ሞልቶ የፈሰሰበት መካከለኛዉ ምሥራቅ ዘንድሮም እንደ ድሮ-ጥንቱ ሰናይ እየተሰበከ እኩይ እንደሚፈፀምበት ለማረጋገጥ ይመስል የርዕሠ-ጳጳሳቱ ቡራኬ፣ፀሎት ምልጃ ከአቡዳቢ ሲንቆረቆር በአቡዳቢ ገዢዎች ትዕዛዝ የመኖች ያልቁ ነበር።ሶሪያዎችም ይገደሉ፣ይሰደዱ፣ ይፈናቀላሉም።ስምተኛ ዓመታቸዉ።እንደ ኃይማኖቱ ብዛት፣ፅናት፣ ስብከት፣ እንደ ነዳጅ፣ ጋዝ ወርቁ ሐብቱ ሁሉ ጦርነት፣ሽብር፣ ግድያ፣ሴራ በነገሰበት መካከለኛዉ ምሥራቅ ትንሽ ጠንከር ያለ መንግሥት፣ሰከን፣ ሻል ያለ ሰላም ያለባት ኢራን ዘንድሮ የካቲት በትልቅ ሽብር  ተናወጠች።
ደቡባዊ ኢራን የሰፈረዉን የአብዮታዊ ዘብ  ጦር ባልደረቦችን አሳፍረዉ ይጓዙ በነበሩ ካሚዮኖች ላይ አሸባሪዎች በጣሉት አደጋ 27 ወታደሮች ተገደሉ።ብዙ ቆሰሉ።
ኢራንና ዩናይትድ ስቴትስ፣ ኢራንና የዩናይትድ ስቴትስ ተከታይ አረቦች የመን ላይ የከፈቱት የተልዕኮ ጦርነት ደሐይቱን፣ ጥንታዊቱን፣ ታሪካዊቱን አረባዊት ሐገር ከማጥፋት፣ቱጃሮቹን አረቦች ከማክሰር ባለፍ አሸናፊና ተሸናፊዉ ሳይለይ ዘንድሮም መጥቶ ሊሔድ ሳምንት ቀረዉ።
ግንቦት  ኦማን ባሕረ ሰላጤ ላይ ይቀዝፉ የነበሩ አራት የነዳጅ መርከቦች በተተኮሰባቸዉ ሚሳዬል ወይም ሌላ መሳሪያ በከፊል ጋዩ።ከአራቱ ሁለቱ የሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ ኩባንያ መርከቦች ናቸዉ።
ለጥቃቱ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሳዑዲ አረቢያና እስራኤል  ኢራንን ለመወንጀል አላመነቱም።በአደጋዉ ሰበብ ዩናይትድ ስቴትስ «የሷንና የወዳጆችዋን ጥቅም ለማስከበር» ተጨማሪ ጦር አረብ ወይም ፋርስ ባሕረ-ሰላጤ ላይ አሰፈረች።ሰኔ 18።
በሳልስቱ፣ የኢራን ጦር  በሆርሙዝ ሰርጥ ዓየር ላይ ትበር የነበረች ዩናይትድ ስቴትስ ሰዉ አልባ አዉሮፕላን (ድሮን)ን መትቶ ጣለ።የቴሕራን ሹማምንት እንዳሉት ድሮኗ የተመታችዉ የኢራንን ሉዓላዊ የዓየር ክልል በመጣስዋ፣ ተደጋጋሚዉን ማስጠንቀቂያ እንቢኝ ብላ በመብረሯ ነዉ።የአሜሪካዉ ጄኔራል ግን «ሐሰት» ይላሉ።
«ከምድር ወደ አየር በሚዘገዘግ IRGC ሚሳዬል ነዉ የተመታዉ።ሚሳዬሉ የተተኮሰዉ ከጉሩክ-ኢራን አቅጣጫ ነዉ።ይሕ ምንም ዓይነት የጠብ አጫሪነት ሙከራ ሳይደረግ በዩናይትድ ስቴትስ ቃኚ ሐብት ላይ የተፈፀመ ጥቃት ነዉ።(ድሮኑ) የኢራንን የአየር ክልል ጨርሶ አልጣሰም።»
የሶሪያ፣የመን፣የየሊቢያ ጦርነት፤ የአረብ-ፋርስ-የሁዲ-አሜሪካኖች ዉዝግብ ግመት ጀቡኖት የነበረዉ የፍልስጤም እስራኤሎች መገዳደል ግንቦት ሲብት ጋለ።እስራኤል ሁለት ወታደሮቿን ያቆሰሉ የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎችን ለመበቀል ጋዛ ሰርጥን ከግንቦት 3 እስከ 6 በአዉሮፕላን ቦምብ ታነፍረዉ ገባች።በትንሽ ግምት 20 ፍልስጤም ተገደለ።አንዷ ነብሰ ጡር፣ አንዱ ሕፃን ነበር።ዓመቱም ተጋመሰ።
የዋሽግተን-ሪያድ-ቴልአቪቭ-ቴሕራን መዛዛት፣መጓሸም፣ በተልዕኮ ማዋጋት ግን እንደቀጠለ ነዉ።ደግሞ ለሌላ መንፈቅ፣ደግሞ ለሌላ ዓመት፣ ምናልባትም ለሌላ ምዕተ-ዓመታት።
ዓመቱ መጀመሪያ ላይ የትንሺቱ አፍሪቃዊት ሐገር የጋቦን የጦር መኮንኖች ፕሬዝደንት አሊ-ቤን ቦንጎ ኦንዲማን ከስልጣን ማስወገዳቸዉን አዉጀዉ ነበር።ወዲያ ከሸፈ።አመቱ አጋማሽ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት «መፈንቅለ መንግስት» ያለዉ ግድያ፣ ባሕርዳርና አዲስ አበባን ላይ ደም አራጨ።
የአማራ መስተዳድር ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም፣ የአማራ የፀጥታ አዛዥን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ተገደሉ።
ጥር ላይ ያየለዉ የቬኑዙዌላ ፖለቲከኞች ዉዝግብ በነዳጅ የበለፀገችዉን ሐገር እያደኸ፣ ዜጎችዋን እያጋደለ፣ እያሰደደ፣መጋቢት ላይ የሁለት ፕሬዝደንቶች ባለቤት አደረጋት።የመጀመሪያዉ በሕዝብ የተመረጡት ማዱሮ ናቸዉ።ሁለተኛ የተቃዋሚዎቹ መሪ ዮአን ጉኢዶ እራሳቸዉን ሾሙ።«እንደ የቬኑዙዌላ የሽግግር ፕሬዝደንት፣ የሐገሪቱን የሥራ አስፈፃሚ ሥልጣን በሙሉ ገቢር ለማድረግ ቃል አገባለሁ።» 
የጉኢዶ ደጋፊዎቻች ቦረቁ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ እስከ ኮሎምቢያ፣ ከብራስልስ እስከ ብራዚል ከሚገኙ መንግሥታት እዉቅና ይጎርፍላቸዉ ያዘ።
ቬኑዙኤላ ሁለት ፕሬዝደንት ስትንበሻበሽ ሱዳን በሕዝባዊ ዓመፅ፣ግድያ መሐል በተደረገ መፈንቅለ መንግስት የ30 ዘመን አንድ መሪዋን ሚዚያ ላይ አሰናበተች።መዓሰላማ እንዲል ዑመር ሐሰን አልበሽር እንዲል ሱዳን።
የካቲት 27-እና 28። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሰሜን ኮሪያዉ መሪ ሊቀመንበር ኪም ጆንግ ኡን ለሁለተኛ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኝተዉ ተነጋገሩ።ሐኖይ-ቬትናም።«ሐገርዎ ለምጣኔ ሐብት ዕድገት በጣም ከፍተኛ ዕድል አላት ብዬ አምናለሁ።የማይታመንና ገደብ የለሽ ዕድል።እርስዎ እንደ ትልቅ መሪ ለሐገርዎ ትልቅ ርዕይ አለዎት ብዬ አምናለሁ።ሲሆን ለማየት፣ እንዲሆን ለመርዳት እጓጓለሁ።እንዲሆን እረዳለንም።»
ከዘለቀ ለሰላም ጥሩ ተስፋ ነዉ።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያን የሚለየዉን ድንበር አቋርጠዉ የሰሜን ኮሪያን ግዛትም ረገጡ።ሰኔ ሰላሳ።ከዚያስ።የ2019 የመጀመሪያ፣መፈንቅ አበቃ።ሳምንት የጠብቁን።የሳምንት ሰዉ ይበለን።ቸር ያሰማን።

Äthiopien Amhara | Beerdigung in Bahrdar
ምስል DW/A. Mekonnen
Ärzte ohne Grenzen| Gaza | Dionysios Mavrodis
ምስል privat
Treffen Kim und Trump Juni 2019
ምስል Reuters/K. Lamarque
Papst besucht die Vereinigten Arabischen Emirate
ምስል picture-alliance/dpa/M. Al Hammadi
Jair Bolsonaro- Präsident von Brasilien
ምስል picture-alliance/AP/E. Peres

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሰ