2014 የዓለም አበይት ክንዉኖች፤ ክፍል I | ዓለም | DW | 22.12.2014
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

2014 የዓለም አበይት ክንዉኖች፤ ክፍል I

ለዋሽንግተን ሐቫና ግንኙነት አሮጌዉ ዓመት አዲስ ተስፋ ፈንጥቋል። ከአፍሪቃ በስተቀር የሌላዉን ዓለም አበይት ክንዉኖች በሁለት ክፍሎች ቃኝተን፤ የማላላን ገደኛ፤ የማሌዥያን ፈሪሰኛ ግን ጉደኛ ዓመት እንሸኘዉ፤

አምና ይሔኔ የኪየቭ አደባባይን ያተራመሰዉ የሞስኮ፤ ዋሽግተን ብራስልስ የጥቅም ሽኩቻ ዩክሬንን እየሸረፈ፤ ሕዝቧን እየፈጀ፤ ዓለምን ወደ ቀዝቃዛዉ ጦርነት ዘመን እንደገፋ የጎርጎሮሳዊያኑ ዘንድሮ አምና ሊሆን ሳምንት ቀረዉ።አስከሬን ቀብረዉ፤ ሌላ ለመቅበር፤ በመገዳደሉ ለተካኑበት ለእስራኤል-ፍልስጤሞች 2014 የመገዳደል ታሪካቸዉ ባንድ ዓመት ጨምሮ፤ እንደ አርባ አምስት ቀዳሚዎቹ ሁሉ ድሮ ሊሆን ነዉ።አፍቃኒስታን የሠፈረባትን የዉጪ ጦር ሲቀነስላት፤ ኢራቅ፤ የተሰናበታትን ጦር ላዲስ ጦርነት ጋብዛለች።ሶሪያም ሰወስት ዓመት የኖረችበትን ጥፋት፤ ዉድመትን ዓመት ኖራበት ለሌላ ጥፋት ሌላ ዓመት ትጠብቃለች።ለዋሽግተን ሐቫና ግንኙነት አሮጌዉ ዓመት አዲስ ተስፋ ፈንጥቋል። ከአፍሪቃ በስተቀር የሌላዉን ዓለም አበይት ክንዉነች በሁለት ክፍሎች ቃኝተን፤ የማላላን ገደኛ፤ የማሌዥያን ፈሪሰኛ ግን ጉደኛ ዓመት እንሸኘዉ።

                

2004 ጀምሮ የየራሳቸዉን ታማኞች ኪየቭ ቤተ-መንግሥት ለመዶል በቀጥታም በተዘዋዋሪም የሚጓቱት የሞስኮ እና የዋሽግተን-ብራስልስ ሐያላን ለእስር ዓመት ረገብ ያለዉ የዩክሬን ታማኞቻቸዉ ዉጥረት ሕዳር 2013 ዳግም ሲግም ለየተከታዮቻቸዉ ድል ዉጥረቱን ከማክረር ባለፍ አንዳቸዉ ሌላቸዉን፤ ሁለቱም ተከታዮቻቸዉን በቅጡ ያወቁ አይመስሉም።

የሞስኮዎችን አቋምና አፀፋ በቅጡ የማያዉቁት ወይም የናቁት ምዕራባዉያን፤ የማያዉቋቸዉን ታማኞቻቸዉን ከማይዳን አደባባይ ወደ ቤተ-መንግስት ሲነዷቸዉ ለዲፕሎማሲዉ ወግ ያሕል እንኳን የሐገርን ሉዓላዊነት ማክበርን ከቁብ አልቆጠሩትም ነበር።

              

«እኔ ሪፐብሊካን ነኝ።ሴናተር መርፊን ዲሞክራት ናቸዉ።እዚሕ የመጣነዉ የአሜሪካ ሕዝብ ከጎናችሁ መቆሙን በጋራ ለመናገር ነዉ።ነፃዉ ዓለም ከናንተ ጋር ነዉ።አሜሪካ ከናንተ ጋር ናት።እኔ ከናንተ ጋር ነኝ።»

የዩናይትድ ስቴትሱ የሪፐብሊካን ፓርቲ ሴናተር ጆን ማኬይን።ማይዳን አደባባይ።ታሕሳስ ማብቂያ 2013። ሞስኮዎች ባንፃሩ በቅጡ የማያዉቋቸዉን የኪየቭ መሪዎች ሳይቀደሙ እንዲቀድሙ ጃስ አሏቸዉ።የካቲት 18። የማይተዋወቁት ሐይላት ጠብ- ሽኩቻ ኪየቭ ላይ ደም ያራጭ፤ ሕይወት ይቀጭ ገባ።

                በፀጥታ አስከባሪዎችና በተቃዉሞ ሰልፈኞች መካከል በተደረገዉ ግጭት ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ተገደሉ።ብዙ ቆሰሉ።ፀጥታ አስከባሪዎቹን ያዘመቱት ፕሬዝዳንት ቪክቶር ያኑኮቪች ግን የሟች ቁስለኛዉ ቁጥር እስኪነገር ኪየቭ አልጠበቁም።ሐገር-ሥልጣናቸዉን ጥለዉ ወደ ሩሲያ እብስ አሉ።

የምዕራባዉያኑ ታማኞች ድል ለሩሲያ ያስረከበዉ ስደተኛዉን ፕሬዝዳንት ብቻ አይደለም የዩክሬንን ሥልታዊ፤ሐብታም፤ ጥንታዊ ግዛት ጭምር እንጂ።ክሪሚያን።ሞስኮዎች የኪየቭን ቤተ-መንግሥት መቀማታቸዉ በተረጋገጠ በወሩ ደጋፊዎቻቸዉ በጠሩት ሕዝበ-ዉሳኔ አፀድቀዉ ሥልታዊቱን ግዛት ከጃቸዉ ዶሉ።መጋቢት 16።ሳቫስቶፖል።

              

«ክሪሚያ የሩሲያ ፌደሬሽን አካል ብትሆን ትደግፋለሕ የሚለዉን የመጀመሪያዉን ጥያቄ መርጦ ድምፅ የሰጠዉ ሕዝብ 1 ሚሊዮን 233 ሺሕ 2 ነዉ።ይሕ ማለት ካጠቃላዩ ድምፅ 96,77 ከመቶ ነዉ።»

ምዕራባዉያን መንግሥታት ሞስኮዎችን ለመበቀል ከመጣደፍ ባለፍ የባላንጣቸዉን አፀፋ፤ የእርምጃቸዉን ጦስ-መዘዝም የተረዱት አልመሰሉም።ሩሲያን በማዕቀብ ሲቀጡ፤ከጋራ ማሕበራቸዉ አባልነት ሲያባርሩ፤ ጦራቸዉን ሩሲያ ጠረፍ ሲያለማምዱ፤ሩሲያ፤ አዳዲሶቹን የዩክሬን ፖለቲከኞች የሚቃወሙትን ወገኖች ታደራጅ፤ ታስታጥቅ ገባች።

ምሥራቅ ዩክሬንም የኪየቭ የመንግሥት እና የዓማፂያን የጦር አዉድማ ሆነች።ሚያዚም አበቃ።በግጭት ጦርነት፤ መበቃቀሉ መሐል ግንቦት 25 በከፊል ዩክሬን በተደረገዉ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቸኮላት አምራቹ ቢሊዮኔር ቱጃር ፖለቲከኛ ፔትሮ ፖሮሼንኮ አሸነፉ።የአዲሱ ፕሬዝዳንት ዓላማ፤ ዕቅድ ንግግራቸዉ ግን ከሰላም ተስፋ ይልቅ እስቸዉን ለሥልጣን ያበቃቸዉ የዚያችን ሐገር ፖለቲካዊ ጡቃንጡቅ የሚያማዝዝ መሆኑን ጠቋሚ ነበር።

                   «እነዚሕ ሰዎች ፌደራሊዝምንም ሆነ ሩሲያኛ ተናጋሪዎችን፤ ወይም መብታቸዉን ከጥቃት የሚከላከሉ አይደሉም።ወንበዴዎች ናቸዉ።ሽፍቶች ናቸዉ።ገዳዮች ናቸዉ።አሸባሪዎች ናቸዉ።»

በዩክሬን ሰበብ ሐያላኑ የገጠሙት ዉዝግብ ሽኩቻ ንረት አይን ጆሮዉን ከአፍቃኒስታን፤ ከኢራቅ በጣሙን ከሶሪያዉ ጦርነት አስነቅሎ-ዩክሬን እንዲተክል የተገደደዉ ዓለም የዚያን ሰሞን ወደ ደቡብ ምስራቅ እስያ አለማማተር አይችልም ነበር።መጋቢት 8።ኩዋላ ላፑር-ማሌዢያ።

«መጋቢት 8፤ ከቀኑ 6 ሠዓት ከ 41 ላይ የበረራ ቁጥር MH370 የሆነዉ የማሌዢያ የመንገደኞች አዉሮፕላን 227 መንገደኞችንና (12 ሠራተኞቹን) አሳፍሮ ወደm ቤጂንግ ለመብረር ከኩዋላ ላምፑር አዉሮፕላን ማረፊያ ተነሳ።ከአንድ ሰዓት በኋላ ቦይንግ 777ቱ አዉሮፕላን ከማሌዢያ የሲቢል በረራ መቆጣጠሪያ (ሬዳር) ጋር ግንኙነቱን አቋረጠ።»

ሥለ አዉሮፕላኑን አንዴ አሸባሪዎች፤ ሌላ ጊዜ አብራሪዎቹ፤ ሌላ ጊዜ አምሪካኖች አንድም ሰዋራቦታ አሳርፈዉታል፤አለያም አጋይተዉታል። እያሉ ብዙዎች ብዙ አሉ።ባሕር፤ ተራራ፤ ሸለቆ ያልታሰሰ ሥፍራ የለም።አዉሮፕላኑም የለም።ጠፋ፤ ጠፋ።

                  የበረራ ቁጥር MH370 አዉሮፕላንን ሥለተሰወረበት ሰበብ ምክንያት ብዙ ተብሎ፤ ብዙ ተፈልጎ ምንም ፍንጭ አለመገኘቱ ዓለምን በሐዘን ጉድ አጃብ ሲያሰኝ አሳዛኙ ዜና በሌላ መጥፎ ዜና ተጆቦነ።ተረኛዋ የማሌዢያ ጎረቤት ናት።ደቡብ ኮሪያ።አደጋዉ የመርከብ።መርከቢቱ 476 ሰዎችን በአብዛኛዉ ለሽርሽር የሚጓዙ ተማሪዎች ሰዎችን አሳፍራ ባሕር ትቀዝፍ ገባች።ሚያዚያ 16።ብዙም ሳይቆይ ተሳፋሪዎቹ ወጣቶቹ መንጫጫት ያዙ።«ልናልቅ ነዉ ይላሉ» ገሚሱ፤ ሌሎቹ ድረሱልን»

«መርከቡ እያጋደለ ነዉ። የርዳታ ያለሕ፤ካላችሁበት ሥፍራ እንዳትቀሳቀሱ።ለአደገኛ ሁኔታ ተዘጋጁ።እየሰመጥን ነዉ።እዉነት እየሰመጥ ነዉ።መዉጣት እፈልጋለሁ።መሞት አልፈልግም» እንዳሉ ሰመጡ።306ቱ ሞቱ።

ፍልስጤም እስራኤል ከታወቁበት፤ እነ አፍቃኒስታን፤ ኢራቅ፤ ሶሪያ ከተደፈቁበት እልቂት ፍጅት አዉሮፓዊቱን ዩክሬንን የቀየጠዉ 2014 ለአዉሮጳ ቀኝ አክራሪዎች ዳግም ትንሳኤ ብጤ ነዉ የሆነዉ።ግንቦት ማብቂያ ለአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት እንደራሴነት በተደረገዉ ምርጫ በተለይ የፈረንሳይና የብሪታንያ ቀኝ አክራሪዎች በርካታ መቀመጫዎችን አግኝተዋል።

የቅኝ አክራሪዎቹ ድልና ትንሳኤ ስደተኞችን፤ ሙስሊሞችንና አይሁዶችን የሚቃወሙ ቡድናት እየተደራጁ የአዉሮጳ አደባባዮችን በጥላቻ ሰልፍ ሙጥኝ እንዳሉ ዓመቱ ተገባደደ።

የዩክሬን ጦርነት እንደ እስራኤል ፍልስጤሞች፤ አንደ አፍቃኒስታን፤ እንደ ኢራቅ፤ ወይም እንደ ሶሪያ እየተለመደ፤ የቀኝ ፅንፈኞች አዉሮጳ ላይ ማንሠራራት እንዳዲስ ሲያነጋግር የተለመደዉ የኢራቅ እልቂት ፍጅት አዲስ ለዓለም ሐያላን አዲስ ጠላት አፍርቶ ያዲስ የሆነ ያክል በዓለም ናኘ።አዲሱ ጠላት-የኢራቅ እና የሻም( ላቬንት) እስላማዊ መንግሥት።ISIS-ISL ወይም IS ይስኛል በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ።የኢራቅን የነዳጅ ቋት፤ ሁለተኛ ትልቅ ከተማም ሞሱልን ተቆጣጠረ።ሰኔ።

ISIS ድል ለኢራቁ ጠቅላይ ሚንስትር ለኑሪ አልመሊኪ ግን የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸዉን ማዉገዢያ ሰበብ ነበር የሆነዉ።

«ዛሬ የሪፕብሊኪቱን ፕሬዝዳን በፌደራላዊዉ ፍርድ ቤት እከሳለሁ።ከኢራቅ ሕዝብ ፍላጎት ይልቅ ለራሳቸዉ ጠባብ ፖለቲካዊ ጥቅም ሲሉ ሕገ-መንግሥቱን ጥሰዋል።»

ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽና ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር ያዘመቱት ጦር ኢራቅን ከወረረበት ከ2003 ወዲሕ ያቺ ሐብታም ሐገር ከሽብር፤ ጥፋት፤ ከእልቂት ዉድመት ሌላ ፤ ሌላ ታሪክ በርግጥ የላትም። ISISም ሶሪያ ዉስጥ ምዕራባዉያን መንግሥታትና የአረብ ተከታዮቻቸዉ ከሚያደራጁ፤ከሚያሰለጥኑና ከሚስታጥቋቸዉ ደፈጣ ተዋጊዎች ጋር አብሮ የበሽር አል አሰድን መንግሥት ሲወጋ አደገኛነቱ ብዙም አልተነገረም ነበር።

ዓለም፤ የዓለም ምርጥ የስፖርት ግጥሚያን ለመከታተል ወደ ብራዚል ሲያማትር-ድፍን ዓለም በጣሙን አሜሪካዊዉ አዲስ ጠላት መጣባሕ ተባለ።ጦሩም ለዳግም ጦርነት ሰንቀ።

«ባሁኑ ሰዓት ትልቁ ሥጋት የሚመጣዉ፤ አክራሪ ቡድናት የሰዎችን ብሶት ለራሳቸዉ ዓላማ ከሚጠቀሙበት ከመከካለኛዉ ምሥራቅና ከሰሜን አፍሪቃ ነዉ።ከነዚሕ ቡድናት አንዱ ISIL ነዉ።እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ ይጠራል።ቡድኑ የአሜሪካ ዜጎችን፤ ተቋማትንና ወታደሮችን ጨምሮ በሶሪያ፤ በኢራቅና በመላዉ መካከለኛዉ ምሥራቅ ትልቅ ሥጋት ፈጥሯል።ይሕ አሸባሪ ቡድን ካልተገታ ከዚያ አካባቢ አልፎ ለአሜሪካና ለመላዉ ዓለምም አደገኛ ነዉ።»

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ኢራቅ፤ ሶሪያ፤ ዩክሬን በጦርነት ሲሾቁ፤ ስፖርተኞች ብራዚል ላይ በኳስ ሲከታከቱ እስራኤል እና ፍልስጤም ላዲስ እልቂት ሲዛዛቱ-አሜሪካዊዉ እዉቅ ድምፃዊና ገጣሚ ቦቢ ዎማክ ሞተ።ሰኔ 27ሐምሌም ግም አለ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic