1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

18 ዓመት የሞላው የአፍሪቃ ሕብረት

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 4 2012

ለበርካታ ዓመታት የአፍሪቃ ሃገራትና መሪዎች በኢትዮጵያዋ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ላይ በመሰባሰብ የአህጉሪቱን ተግዳሮቶችና መጪ ዕድሎች በተመለከተ ይነጋገራሉ። እንዲያም ሆኖ በአውሮጳውያን ለጋሾች ላይ ጥገኛ የሆነው የአፍሪቃ ሕብረት ውሳኔ ግን ተግባራዊ የሚሆነው አልፎ አልፎ ነው።

https://p.dw.com/p/3fARX
Afrikanische Union Flaggen
ምስል picture-alliance/landov

«ትኩረት በአፍሪቃ»

በጎርጎሪዮሳዊው 2002 ዓ,ም ነው ከአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪቃ ሕብረት የተሸጋገረው። ዓላማው አፍሪቃን ወደሰላም ደሴትነት ለማሸጋገር ቢሆንም እስካሁን ሕብረቱ በተጓዛቸው 18 ዓመታት ለአካለ መጠን አልደረሰም እንደ ዶቼ ቬለው እንግሊዝኛ ለአፍሪቃ ክፍል ባልደረባ አይዛክ ሙጋቤ አስተያየት። የአፍሪቃ አንድነት የአህጉሪቱ መሠረታዊ ችግሮች ለሆኑት ድህነትና የኤኮኖሚ ደካማነት አንዳች መፍትሄ አላበጀም በሚል ይወቀሳል። የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት በአባል ሃገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት አቋም ይዞ ቆይቷል። በአንጻሩ የአፍሪቃ ሕብረት አስተዳደሩን በማጠናከር ሰብዓዊ ጣልቃ ገብነት በሚያስፈልግበት አካባቢ የሚሠማራ ኃይል አደራጅቶ ለዚህም መብትን ሰጥቷል።  የአፍሪቃ ሕብረት መመስረት እንደአንድ ትልቅ እመርታ በመወሰዱ በመላው አፍሪቃ አድናቆትን አትርፏል። የዚህ አዲስ ልጅ መወለድም ውሎ አድሮ ለአካለ መጠን በመድረስ ሁሉም የሚኮራበት ይሆናል የሚል ተስፋ አሳድሯል። ልጁ አሁን አድጓል። ሆኖም ቤተሰቦቹ እኛ አፍሪቃውያን የወደፊቱ ጥርጣሬ ፈጥሮብናል። ምክንያቱ ደግሞ የአፍሪቃ ሕብረት 18 ዓመት ቢሞላውም ገና በጉርምስና ደረጃ ያለ ልጅ መምሰሉ ነው። በጠዋት መነሳት እንደሚሳነውና የገዛ ክፍሉን እንደማያጸዳ ልጅ፤ በየጊዜው ከወንድም እህቶቹ ጋር እንደሚጋጭ ልጅ አይነት መሆኑ። ለዚህ ማሳያው ደግሞ የአፍሪቃ ሕብረት በዓለም የንግድ ድርጅት ውስጥ ቀጣይ መሪ መሆን የሚችለውን እጬ መደገፍ አለመቻሉ፤ ወይም ይበልጥ የሚያሳፍረው ደግሞ በቅርቡ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የሚለቀቀውን መቀመጫ የሚተካውን ተባብሮ አለመደገፉን መጥቀስ ይቻላል።

Äthiopien Addis Abeba Gipfeltreffen der Staatschefs der Afrikanischen Union
ምስል picture-alliance/AA/Palestinian Prime Ministry Office

ለበርካታ ዓመታት የአፍሪቃ ሃገራትና መሪዎች በኢትዮጵያዋ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ላይ በመሰባሰብ የአህጉሪቱን ተግዳሮቶችና መጪ ዕድሎች በተመለከተ ይነጋገራሉ። እንዲያም ሆኖ በአውሮጳውያን ለጋሾች ላይ ጥገኛ የሆነው የአፍሪቃ ሕብረት ውሳኔ ግን ተግባራዊ የሚሆነው አልፎ አልፎ ነው። ምክንያቱም አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች ብዙ ገንዘብ የሚጠይቁ በመሆናቸው። ለዚህ መፍትሄ ለማምጣት በሚል በሩዋንዳው ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ የሚመራ አንድ ኮሚሽን ተቋቋመ። ኮሚሽኑም ለምሳሌ የአፍሪቃ የሰላም አስከባሪ ኃይል በገንዘብ እንዴት ሊደገፍ ይችላል የሚለውን አጥንቶ አቀረበ። ብዙዎች «የካጋሜ ሪፖርት» የተሰኘው የኮሚሽኑ ዘገባ ላይ ተስፋ ጥለው ነበር። ሆኖም ከ55 አባል ሃገራት 419ኙ ብቻ የፈረሙት የአፍሪቃ ነፃ የንግድ ቀጣና ከመፈጠሩ በቀር ሌሎች የቀረቡት ሃሳቦች ተግባራዊ አልሆኑም። የአፍሪቃ ሕብረት በሶማሊያ እና በሱዳን ዳርፉር ግዛት መጠነኛ ሰላም የማምጣት ጥረት አድርጓል። ሆኖም ግን በሰሜን ማሊና በቻድ ሐይቅ አካባቢ በሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ባልሆኑ ጂሃዳዊ ኃይሎች፤ እንዲሁም በካሜሮን በሚንቀሳቀሱ የተገንጣዮች እንቅስቃሴና ሊቢያ ውስጥ ባለው ጦርነት ምክንያት አፍሪቃ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የትላልቅ ግጭቶች ምንጭ መስላለች።

ሌላው መነሳት ያለበት የአፍሪቃ ሕብረት ያለው ከባድ የገንዘብ እጥረት ነው። ከመራር ድህነት ጋር የሚታገሉት ከሰሃራ በስተደቡብ የሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራት አብዛኞቹ ከቻይና እጅግ በርካታ ገንዘብ መበደር ጀምረዋል። ሆኖም ለመክፈል የሚችሉ አይደሉም። ይህ ደግሞ የአፍሪቃ ሕብረት ያቀዳቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለማሳካት አዳጋች ያደርግበታል። በዚያ ላይ ቻይና አዲስ አበባ የሚገኘውን የሕብረቱን ዋና መወመጫ ለመገንባት 180 ሚሊየን ዩሮ አውጥታለች። በርካታ ታዛቢዎች እንደሚሉት በዚህ ድርጅት ውስጥ የቻይና ተፅዕኖ የጎላ ነው። እግረ መንገዱንም በአፍሪቃ ኤኮኖሚም ሆነ እንቅስቃሴ ላይ የቻይና ተፅዕኖ እየተስፋፋ መሄዱ ይታያል።

አዲሱ የአፍሪቃ ሕብረት ሕንጻ
ምስል Getty Images

በዚህ መሀል በአዛውንቶችና በፈላጭ ቆራጮች የሚመሩት አብዛኞቹ የአፍሪቃ ሕብረት አባል ሃገራት የአህጉሩ አብዛኛው ኃይል ስለሆነው ወጣቱ ፍላጎት የሚገዳቸው አይመስሉም። የአፍሪቃ ሕብረትም ቢሆን ድንገት የሚፈለገውን የኤኮኖሚ ነፃነት ለማግኘትም ሆነ ለመላው አፍሪቃ ዴሞክራሲ ከልቡ መሥራት ይጀምራል ብሎ ማሰቡ ይከብዳል።  እንዲያም ሆኖ ለአካለ መጠን ሳይደር 18 ዓመት የሞላውን የአህጉሪቱን ትልቅ ድርጅት እንኳን አደረሰህ እንበለው። ሐምሌ 2 ቀን የለኮሰውን የልደት ሻማውን ሲያጠፋም ማደጉን የሚያመላክት አንዳች ተስፋ ድንገት ያሳየን ዘንድ እንመኝለት።

rበኮትዴቬዋር የፕሬዝደንቱን መንበረ ሥልጣን ይረከባሉ በሚል የታሰቡት የጠቅላይ ሚኒስትሬ አማዱ ጎን ኩሊባሊ ድንገተኛ ሕልፈተ ሕይወት የሀገሪቱን ቀጣይ መሪ ማንነት ጥያቄ ላይ ጥሎታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኩሊባሊ ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ ዕለት ነበር ድንገት በፕሬዝደንቱ ቤተ መንግሥት ከሚኒስትሮች ጋር ለስብሰባ በተቀመጡበት ታምመው ወደሀኪም ቤት የተወሰዱት። በ61 ዓመታቸው ያረፉት ኩሊባሊ አሟሟት እስካሁን ግልፅ ባይሆንም ለሁለት ወራት የልብ ህክምና ሲያደርጉ ከሰነበቱባት ፈረንሳይ በቅርብ ነው ወደሀገራቸው የተመለሱት። በጎርጎሪዮሳዊው 2012ም የልብ ቀዶ ህክማ እዚያው ፈረንሳይ አድርገዋል። ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር የኮትዴቩዋር ፕሬዝደንት አላሳን ዋታራ ድንገት ለሦስተኛ ጊዜ ለፕሬዝደንትነት አልወዳደርም በማለታቸው የሀገሪቱን ገዢ ፓርቲ እጩ ሆነው በመጪው ጥቅምት ወር በሚካሄደው ምርጫ እንዲወዳደሩ ተሰይመው ነበር። አሁን የእሳቸው ሕልፈተ ሕይወት ከፓርቲው በቦታቸው በእጩነት ማን ይቀርብ ይሆን የሚል ጥያቄ አስነስቷል። ፕሬዝደንት ዋታራ «ታናሽ ወንድም» አንዳንዴም «ልጅ» እያሉ የሚጠሯቸው ኩሊባሊ ከእሳቸው ጋር ተግባብተው በታማኝነት ላለፉት 30 ዓመታት ለሀገራቸው ሢሰሩ መኖራቸውን ሞታቸው ከተሰማ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት ጠቁመዋል። 

ፕሬዝደንት አላሳን ዋታራ እና አማዱ ኩሊባሊ
ምስል Reuters/T. Gouegnon

በአቢጃን የኮንራድ አደናወር ተቋም ኃላፊ የሆኑት ጀርመናዊው ፍሎሪያን ካርነር እንደሚሉት ለህክምና ከቆዩባት ፈረንሳይ ከተመለሱ በሳምንታት ዕድሜ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መሞት ኮትዴቩዋርን እጅግ ማስደንገጡን ከሕዝቡ ስሜት መረዳት ይቻላል ባይ ናቸው። በዚህ መሀልም የእጬ ፕሬዝደንትነቱን ቦታ ለመያዝ ፉክክሮች መኖራቸው እንደማይቀርም ያስረዳሉ።

«በርካታ እጩዎች ይኖራሉ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት የሚገልጸውን የፕሬዝደንቱን መልእክት በመገናኛ ብዙሃን ያወጁት የፕሬዝደንቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፓትሪክ አቺ አንዱ ናቸው፤ ከዚህም ሉሌላ የወቅቱ የፓርላማ ፕሬዝደንት አማዱ ሱማሆሮ ሌላው ታሳቢ ሊሆኑ ይችላሉ።»

በማለትም በእሳቸው ዕይታ በእጩነት ሊቀርቡ የሚችሉትን ይዘረዝራሉ። በአቢጃን የፍሬደሪሽ ኤበርት ተቋም ኃላፊ ቲሎ ሹነር  ጀርመናዊ የኩሊባሊ የጤና ይዞታ ከታወከ ዓመታት መቆጠራቸውን ያስታውሳሉ። ባለፉት ዓመታትም ተደጋጋሚ የልብ  ድካም ህመም እንዳጋጠማቸው ያነሱት ሹነር ኩሊባሊ በኮሮና ተሐዋሲ ተይዘው እንደነበርም አንስተዋል።

«ለማስታወስ ያህል በ2016 የሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ እስኪደረግበት ድረስ እያንዳንዱ ፕሬዝደንታዊ እጩ ኃላፊቱን ለመቀበል በሚያስችል ይዞታ ላይ መሆኑን የሚያመለክት የጤና ሁኔታ ሰርተፊኬት ማቅረብ እንዳለበት ይደነግግ ነበር። ሆኖም በአዲሱ ሕገ መንግሥት ይህ ተሰርዟል። ኩሊባሊ በ2012 የልብ ቀዶ ህክምና አድርገዋል በቅርቡ ደግሞ በኮሮና ተሐዋሲ ተይዘው ነበር። እናም ይህን ኃላፊነት መቀበል ይችላሉ ወይ የሚል ጥያቄ ለረዥም ጊዜ መነጋገሪያ ነበር። ትናንት የታየውም ይህ ሊሆን እንደማይችል ነው።»

Elfenbeinküste I Präsident Amadou Coulibaly verstorben
ምስል Reuters/L. Gnago

ምንም እንኳን ከባህልን ሥርዓት አኳያ አሁን በይፋ በጉዳዩ ላይ የሚነጋገር ባይኖርም በኩሊባሊ ቦታ እጩ ሆኖ የሚቀርበው ማን ይሆን የሚለው አሁንም የብዙዎች ጥያቄ መሆኑንም ጠቁመዋል። እንዲያም ሆኖ በፓርቲው ደረጃ በተጠባባቂነት እገሌ ተይዟል ማለት እንደማይቻል፤ ጋዜጠኞችና የሀገሪቱ ፖለቲካ አዋቂዎች ግን የሚገምቷቸው ሰዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። በእሳቸው ግምትም ኩሊባሊ ለህክምና አውሮጳ በቆዩበት ወቅት ሥራቸውን በአግባቡ ሸፍነው ያከናወኑት የወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር የ55 ዓመቱ አህመድ ባካያኮ ለቦታው ብቁ ናቸው። ፍሎሪያን ካርነርም በዚህ ግምት ቢስማሙም ባካያኮ የፓርቲያቸውን ብሎም የፕሬዝደንት ዋታራን ድጋፍ ያገኛሉ ብለው አይገምቱም። ያም ሆነ ይህን የዋታራ ፓርቲ እስከ ያዝነው ሐምሌ ወር ማለቂያ ድረስ ይህን ማሳወቅ ይኖርበታል።

የ78 ዓመቱ አላሳን ዋታራ ባለፈው መጋቢት ወር ከእንግዲህ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ራሳቸውን ለኃላፊነት ለማቅረብ እንደማይፈልጉ ማሳወቃቸው ከፍተኛ ድጋፍ እና አክብሮትን አስገኝቶላቸዋል። ሃሳባቸውን ጥለውባቸው የነበረው የኩሊባሊ ሞት ምናልባት ሃሳባቸውን ሊያስለውጣቸው ይችል ይሆን የሚሉ ባይጠፉም ቲሎ ሹነር ግን ሰውየው ቃላቸውን በመጠበቅ የሚታወቁ ከመሆናቸው ሌላ የጤና ይዞታቸውም ሆነ ዕድሜያቸው እንዲህ እንዲያደርጉ አይፈቅድላቸውም ነው የሚሉት። ሌሎች የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው ዋታራም ሆነ ፓርቲያቸው ያቀዱት ዐይናቸው እያየ ከሚበላሽ አማራጭ ነው ያሉትን ሊሞክሩ ይችላሉ፤ ይህም ራሳቸው ዋታራ በድጋሚ በእጩነት ከመቅረብ ላያግዳቸው ይችላል ባይ ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ አዲሱ ሕገ መንግሥት ይደግፋቸዋል። ተቃዋሚዎቻቸው ደግሞ ይህን ተቃውመዋል። በዓለም አቀፉ የቀውስ መንስኤ አጥኚ ተቋም ክራይስስ ግሩፕ የምዕራብ አፍሪቃ ፕሮጀክት ዳይሬክተር ሪናልዶ ዴፓኜ እንደሚሉትም ምንም እንኳን ዋታራ ባሉበት ጎራ ያለምንም ተቃውሞ ተመራጭ ቢሆኑም አቋማቸውን ለውጠው ለምርጫው ቢቀርቡ በጣም አደገኛ ነው። ፕሬዝደንት ዋታራ የሚመሩት ፓርቲ ወደሥልጣን የመጣው የቀድሞው ፕሬዝደንት ሎሮን ባግቦና ፓርቲያቸው በምርጫ ተሸንፈው በተፈጠረ ውዝግብ 3000 ዜጎች ካለቁ በኋላ ነው። አሁን የሚመርጡት የፓርቲያቸው እጩ የሚወዳደረው ከጎርጎሪዮሳዊው 1993 እስከ 1999 ድረስ የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ከነበሩት ሄንሪ ኮናን ቤዲ ጋር ይሆናል። ለጊዜው ግን ማንነቱ አልተለየም።

Elfenbeinküste Yamoussoukro City
ምስል Getty Images/AFP/S. Kambou

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ