1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

10 ኛዉ የፌዴራል ክልል ለሆነዉ የሲዳማ ዞን የስልጣን ርክክብ ተደረገ

ሐሙስ፣ ሰኔ 11 2012

የደቡብ ክልል ምክር ቤት አስረኛ የፌዴራል ክልል ሆኖ ለሚደራጀው የሲዳማ ዞን የስልጣን ርክክብ አደረገ ። የስልጣን ርክክቡ የተከናወነው በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የክልሉ ምክር ቤት አምስተኛ ዙር አምስተኛ ዓመት ሁለተኛ አስቸኳይ ጉባኤው ላይ ነው ። 

https://p.dw.com/p/3e0cZ
Äthiopien SNNPR Konferenz zur Sidama-Zone
ምስል DW/S. Wegayehu

የደቡብ ክልል ምክር ቤት አስረኛ የፌዴራል ክልል ሆኖ ለሚደራጀው የሲዳማ ዞን የስልጣን ርክክብ አደረገ ። የስልጣን ርክክቡ የተከናወነው በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የክልሉ ምክር ቤት አምስተኛ ዙር አምስተኛ ዓመት ሁለተኛ አስቸኳይ ጉባኤው ላይ ነው ። በጉባኤው ላይ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሄለን ደበበ የስልጣን ማስረከቢያ ደብዳቤውን ለቀድሞው የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ሰለሞን ላሌ አስረክበዋል። የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ አስፈጻሚ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዳነ ገበየሁ የደቡብ ክልል ለአዲሱ የሲዳማ ክልል በይፋ የህገ መንግስታዊ የስልጣን ርክክብ ማድረጉን ለጉባኤተኞቹ በንባብ አሰምተዋል። በጉባኤው ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ርእስቱ ይርዳው ህዝቡ ክልል የሚባል አደረጃጀት ከመምጣቱ በፊት ህዝቡ ለዘመናት አብሮ የኖረ በመሆኑ አሁን ተግባራዊ የሆነው አደረጃጀት ሊያሳስብበው አይገባም ብለዋል። የስልጣን ማስረከቢያ ደብዳቤውን የተቀበሉት የቀድሞው የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ሰለሞን ላሌ በበኩላቸው የሲዳማ ህዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ለዘመናት ሲጠይቅ የነበረው ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ እንኳን ደስ አለን ብለዋል። አሁን የተገኘው የመደራጀት መብት የብሄሩ ታጋዮች ባደረጉት ጥረትና ከሁለት ዓመታት ወዲህ የመጣው የለውጥ አመራር በፈጠረው ነፃነት ነው ሲሉ ተናግረዋል። በቀጣይም የሲዳማ ህዝብ እስከ ዛሬ አብሮ ከኖራቸው ህዝቦች ጋር በመሆን ድህነትንና ኋላ ቀርነትን እንደሚታገል አቶ ሰለሞን በንግግራቸው ጠቅሰዋል። ዛሬ በተከናወነው የሲዳማ ዞን የስልጣን ርክክብ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ተቋማት የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ።

 

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ 

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ