ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ፤ የ "በርሊናለ" የክብር ተሸላሚ -ክፍል ሁለት ቃለ-ምልልስ
ሐሙስ፣ የካቲት 26 2018
ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ፤ የ "በርሊናለ" የክብር ተሸላሚ -ክፍል ሁለት ቃለ-ምልልስ
ከአስርተ ዓመታት የታሪክ ማህደር ፍለጋ እና ማሰባሰብ አድካሚ ሥራ በኃላ “ጥቁር አንበሳ - የፎማ ተኩላ” በሚል ርዕስ የቀረበዉ ፊልም ፤ የኢጣልያ ፋሽስት በሁለተኛዉ የኢትዮጵያ ወረራ ወቅት ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም፤ ከፍሺስት ኢጣልያ ጋር ያደረጉትን ተጋድሎ የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ነዉ። ይህ ፊልም ጀርመን መዲና በርሊን በየዓመቱ በሚካሄደዉ በዓለምአቀፉ የፊልም ፊስቲቫል “በርሊናለ” ላይ ለእይታ አቅርበዋል። በጀርመን በርሊን መዲና በተካሄደዉ 76ኛ የፊልም ፊስቲባል ላይ ከፍተኛ እዉቅና ያገኙትን ኢትዮጵያዊ የፊልም ስራ ባለሞያ ከፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ ጋር የተካሄደ ቃለ ምልልስ አንደኛ ክፍል ባለፈዉ ሳምንት ዝግጅታችን ቀርቦ ነበር። ይህ ዝግጅት ን ነበር ዛሬ ደግሞ ሁለተኛዉን እና የመጨረሻዉን ክፍል ይዘን ቀርበናል፤
ፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ በበርሊኑ በዓለም አቀፉ የፊልም ፊስቲቫል “በርሊናለ” ላይ ለእይታ ያቀረቡት የጥበብ ሥራቸዉ ፊስቲቫሉ ልዩ የሆነዉን የክብር ሽልማት « የበርሊን ካሜራ»ን አበርክቶላቸዋል። 76ኛዉ የፊልም ጥበብ መድረክ “በርሊናለ” ኃይሌ ገሪማ ላላቸዉ ነጻ የሲኒማ ጥበብ የእድሜ ልክ ቁርጠኝነት ፤ ታሪካዊ ፊልምን የመተረክ ብቃት እና፤ የጥቁር አፍሪቃዉያን ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረክ ጎልቶ እንዲወጣ ላደረጉት ጥረት እና ላበረከቱት አስተዋፅኦ እዉቅና በመስጠት ቆሞ አጨምብጭቦላቸዋልዉ። ኃይሌ ገሪማ ጀርመን መዲና በበርሊን በተካሄደዉ በዚሁ ዓለም አቀፍየሲኒማ ጥበብ ማሳያ መድረክ ላይ ያቀረቡት “ጥቁር አንበሳ - የሮማ ተኩላ” የተሰኘዉ ታሪካዊ ዘጋቢ ፊልማቸዉ በኢጣልያ ፤እንጊሊዝ፤ ሩስያ፤ ጀርመን እና ፈረንሳይ ዉስጥ በሚገኙ ታሪካዊ የተንቀሳቃሽ እና የምስል ማህደራት የተገኙ ታሪካዊ ማስረጃዎችን ያካተተ እንደሆነም ተነግሯል። ይህ አምስት ተከታታይ ክፍሎች ያሉት እና ወደ ዘጠኝ ሰዓት ርዝመት ያለዉ የኃይሌ ገሪማ ታሪካዊ ዘጋቢ ፊልም ለወጣት ኢትዮጵያዉያን ምን አይነት መልዕክትን ያስተላልፍ ይሆን? በርሊን ከተማ ፕሮፊሰር ኃይሌን አግኝታ ያነጋገረቻቸዉ የዶቼ ቬለዋ ክርስቲነ ቴሼራ ኃይሌን ወጣት ኢትዮጵያዉያን ፊልሙን አይተዉ ምን አሉ ስትል ጠይቃቸዉ ነበር።
“ፊልሙ ለመጀመርያ ጊዜ ለእይታ እንደቀረበ መጥተዉ የተከታተሉ ወጣቶች "አናመሰግናለን " ይህ ሁሉ የእኔ ታሪክ መሆኑን አላወኩም ነበር ብለዉኛል። ይሄንን ነዉ ልነግርሽ የምችለዉ። ለወጣቶች ከፊልሜ ይህን ይዉሰዱ ብዬ ልናገረዉ የምችለዉ ነገር የለኝም። እንደ ግለሰቡ ይለያያል። እኔን ፊልሙ ምን አደረገልህ ብለሽ ብትጠይቂኝ ፤ መልሴ የተሻለ ሰዉ አድርጎኛል ፤ ብዙ ግንዛቤ እንጨብት አድርጎኛል። ኢትዮጵያዉዉያን ጥንታዊ እና አስደናቂ መሆናቸዉንም አይቻለሁ። የጣሊያንን ወረራ በጥልቅ ሰብአዊነት እንዴት እንደተዋጉ እና እንደተቃወሙም አይቻለሁ። ይህ ደሞ እኔ በጣም ፈዉሶኛል።”
የዶቼ ቬለዋ ክርስቲነ ቬራ ቴሼራ ጥያቄዋን ለፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ በመቀጠል በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተለይም አሁን አሁን ፤ ቲክቶክ በተሰኘዉ ማኅበራዊ መድረክ ፤ ኢትዮጵያዉያን በጎጥ በሃይማኖት ሲወዛገቡ፤ ብሎም ከፍተኛ ጠብ ዉስጥ ሲገቡ ይታያል። ይህን እርሶ እንዴት ይገልፁታል? እዚህ ላይ የእርሶ አስተያየት ምንድን ነዉ ስትል ጠይቃቸዋለች። “ ሞባይል ስልክ የለኝም ፤ ሞባልይ ገዝቼ እንኳ አላዉቅም። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ምን እየተደረገ እንደሆነ አላዉቅም። ስለዚህ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጉዳይ ለኔ ትርጉም የለሽ ነገር ነዉ። “
ወጣት ኢትዮጵያዉያን አሁን አሁን የሚሰሩት ፊልም፤ አገር በቀል ይዘት ያለዉ መሆኑን ፤ በተለይ ገጠርኛ ይዘት ያለዉ እንደሆነ ይነገራል ይሁን እና ይህ በጣም በጥቂቱ እንደሆነ የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የፊልም ሰሪዎች በአብዛኛዉ ለእይታ የሚያቀርቧቸዉ ፊልሞች የምዕራባዉያን የአሰራር ዘዴን ተፅኖ ያለባቸዉ መሆኑን አጥብቀዉ ሲተቹ ይሰማል። ፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ በዚህ አስተያየት ይስማሙ ይሆን?
10“እነሱ ብቻ አይደሉም። በዓለም ዙሪያ ያሉ ላቲን አሜሪካውያን፣ እስያውያን እና አፍሪቃውያን የሮማን ኢምፓየርን ኮርጀዋል። አዲሱ የሮማ ኢምፓየር ደግሞ አሜሪካንን እየኮረጀ ነዉ ፊልም የሚሰራዉ። ሆሊውድን ይከተላሉ። እንደ ሆሊውድ ፊልሞችን መሥራት ይፈልጋሉ። ለኔ ግን ይህ ያረጀ፤ ጊዜዉ ያለፈበት ኢንዱስትሪ ነዉ። መኮረጅ ይቻላል። ነገር ግን የጥበብ ሰዉ ወይም አርቲስት ማለት፤ የራስን ሀሳብ፤ የራስን የትረካ አመክንዮ ፣ የእራስን ዘይቤ ፣ የራስን ታሪኮች እና የትረካ መንገድ ማዳበር ማለት ነው። ዓለም ሊያከብረው የሚገባው ይህን አይነቱን የአፍሪቃ ወጣት ፊልም ሰሪን ነዉ እንጂ ከሆሊውድ የተኮረጀ ስራን አይደለም። “
በዓለም አቀፍ መድረኮች የጥቁሮች ሲኒማ በአዎንታዊ መልኩ እያደገ ይሆን ? በዓለም አቀፉ የሲኒማ መድረክ ለነፃ ጥቁር ሲኒማ ተጨማሪ ቦታ አለ? በዓለም የሲኒማ መድረክ እዉቅናን ያገኙት ኢትዮጵያዊ ፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ እንዴት ይገልጹታል? አስተያየተያየታቸዉ ምን ይሆን? "አዎ፣ ሆሊውድ ዉስጥ በጣም ትልቅና ጠንካራ እንቅስቃሴ ያለ ይመስላል። እኔ ያላየሁት ነገር ቢኖር - የትረካ ስነ-ልቦና፣ ባህላዊ፣ መንፈሳዊ ሃይል በሆሊውድ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገለት አይደለም። ሆሊዉድ እራስህን እንድታውቅ፣ እራስህን እንድታገኝ ፍፁም አይደግፍህም። የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግልህ ሆሊዉድ ገንዘብ ለማግኘት ወይም መስራት ሲችል ነዉ። ገንዘብ ለማግኘት ደግሞ አንተ የተለመደዉን አሰራር መከተል አለብህ ለኔ ይህ ተቀባይነት የለዉም።"
ፕሮፊሰር - ስለ ወቅታዊዉ ዓለም አቀፍ ፖለቲካ እናዉራ። የእርሶ ታሪካዊ ዘጋቢ ፊልም ስለሙሶሎኒ እና ፋሺስታዊ ሃሳቦቹ ይጠቀሳል። አሁን ደግሞ በዓለማችን የቀኝ አክራሪነት እየተስፋፋ ዓለም ወደ ቀኝ እያዘነበለ የመጣበት ወቅት ላይ እንገኛለን። እርሶ ይህንን ሁኔታ እንዴት ያዩታል? ለአብነት የኢትዮጵያን ታሪክ እንውሰድ። የዓለማችን ወቅታዊ አካሄድ ለመመከት ከጥንቱ የኢትዮጵያ ታሪክ ምን እንማራለን ይላሉ?
"የኔን ፊልም ከተመለከቱ በዝያን ወቅት የኢጣልያ ህዝብ ሞሶሎኒን ፈጠረ ብዬ አምናለሁ። እሱ ባይኖር ኖሮ ኢጣልያዉያን ሞሶሎኒን ላብራቶሪ ገብተዉ ይፈጥሩት ነበር። ሞሶሎኒን የፈጠረዉ ማኅበረሰቡ ራሱ ነዉ። ለኔ ይህ እዉነታ ዛሬም እየታየ ነዉ። ፋሺስት መሪን የፈጠረዉ ራሱ ፋሽት የሆነዉ ህዝብ ነዉ። እንደ ፊልም ሰሪ፤ ግለሰቦች ላይ ማተኮር ትልቅ ስህተት ነው እላለሁ። በሂትለር እና ሙሶሎኒ ጊዜ ይህን ስህተት ሠርተናል። ለኔ ችግሩ ያለው ሙሶሎኒን ማን እንደሆነ ባደረጉት ሰዎች ላይ ነው። ለዚህም እስካሁን መፍትሄ አላገኘንም። ብዙሃኑ ህብረተሰብ መሪዎችን ይፈጥራል። ስህተቱ እዝያ ላይ ነዉ" ፕሮፊሰር ኃይሌ የቅኝ ግዛት ዘመን ብዙ አስከፊ ነገሮች ታይተዉ እንደነበር የታሪክ ማህደራት ያሳያሉ። ዛሬ በግልፅ የሚያዩዋቸዉ የቅኝ ግዛት ጠባሳዎች ምንድናቸው?
"የጎሳ እና የሃይማኖት ልዩነቶች፤ በአፍሪቃ የቅኝ ግዛት ውርስ ናቸዉ፤ አራት ነጥብ ። ለአርባ ዓመታት ያህል ፋሽስቶች በኢትዮጵያ ውስጥ የጎሳ መለያየትን ተክለዋል። ጉዳቱ ዛሬም ድረስ ይታያል፣ ዛሬም ችግራችን ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ይህን ችግር እንዴት ማየት እንዳለብን አናውቅም። ለአርባ ዓመታት ኢጣልያኖች ዛሬ የምናየውን የጎሳ እና የሃይማኖት መለያየት ተክለዉብናል። የድንበር፤ ወይም የክልል እና በዘር ላይ ያሉት ችግሮች ፋሺስት ኢጣልያ ወቅት የጀመሩ ችግሮች ናቸዉ።"
ስለዚህ ይህን ችግር ለመቅረፍ ፤ ብሎም ችግሩን መልሶ ለመዉጋት አንዱ መንገድ አንድነትን መፈጥር፤ አንድ መሆን መፍትሄ ሊሆን ይችላል ይላሉ? “አዎ፣ ግን ታሪክሽን ካላወቅሽ አንድ መሆን አትችይም። በምን መሰረት ላይ ሆኜ ነው ከአንቺ ጋር አንድነት እና ዉህደት ልፈጥር የምችለዉ። በኔ እይታ ከአንድነት በፊት ከየት እንደመጣን፤ ማንን እንደሆን ማወቅ አለብን። የት እንደደረስን ማወቅ አለብን። አሁን የምናየዉ ግራ በተጋባ ሰዎች ስር ያለ አንድነት፤ በእብደት ጥገኝነት ላይ ያለ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ዓለምን ለመለወጥ እብዶች የተደራጁበት ነዉ ። ይህ ደግሞ እብደት ነዉ" ፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ ለሰጡኝ ቃለ ምልልስ እጅጉን አመሰግናለሁ። -- እኔም አመሰግናለሁ!
ዶቼ ቬለ ከፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ ጋር ያደረገዉ ቃለ ምልልስ የቀረበበት ሁለተኛ ክፍል እስከዚሁ ነበር። የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሔር