1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተገልጋዮች ምሬት

ሐሙስ፣ የካቲት 7 2016

አዲስ ፓስፖርት ለማውጣትና አሮጌ ለማሳደስ እስከ አንድ አመት በመጓተቱ የተለያዩ የውጭ ጉዞዎች እየተሰናከሉባቸው እንደሆነ ተገልጋዮች ገለጹ። በአንጻሩ በተገልጋዩ በኩልም በርካታ ፓስፖርት ጠያቂዎች የተዘጋጀውን ፓስፖርት በወቅቱ ባለመውሰዳቸው ከፍተኛ ክምችት መፈጠሩን እየተነገረ ነው።

https://p.dw.com/p/4cRmJ
የኢትዮጵያ ፓስፖርት
የኢትዮጵያ ፓስፖርትምስል DW/S. Wegayehu

``የፓስፖርት ያለህ!`` የተገልጋዮች ሮሮ

አዲስ ፓስፖርት ለማውጣትና አሮጌ ለማሳደስ እስከ አንድ አመት በመጓተቱ የተለያዩ የውጭ ጉዞዎች እየተሰናከሉባቸው እንደሆነ ተገልጋዮች ገለጹ። የፌደራል የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በበኩሉ ችግሩ የተፈጠረው ፓስፖርት ከውጭ ታትሞ መምጣት ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ በመቆየቱ ነው ይላል።መስሪያ ቤቱ ችግሩን ለማቃለል 24 ሰዓታት እየሰራን ነውም ብሏል።

ሰዓሊ በቀለ መኮንን ሰሞኑንበፓስፖርት አሰጣጥ ቤተሰቡ ያጋጠመውን በፌስቡክ ገጹ ያጋራው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ሰዓሊው አንዲት የቤተሰቡ አባል ፓስፖርት ለማውጣት በሄደችበት የገጠማትን እና የፈጠረበትን ስሜት እንዲህ አጋርቶናል።
``የቀበሌ መታወቂያ እያለህ፣ ካልላደግክበትና ከማታዉቀዉ አካባቢ ማንነትህን የሚገልጽ ተጨማሪ መረጃ ወይም ወረቀት አምጣ ማለት ተገቢ አልነበረም። በሁኔታው ስለተበሳጨሁ ጽሑፉን ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጋርቼዋለሁ  በኋላ መስሪያቤቱ ድረስ በመሄድ ሃላፊዎችን አነጋግሬ የተሰጠኝ ምላሽ፤ ለደህንነት ሲባል እንደዚያ አይነት ጥያቄ መቅረቡን  ማብራሪያ ተሰጥቶኛል``
ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁም ፓስፖርቱን ለማሳደስ ካመለከተ ለአንድ ዓመት አንድ ሳምንት ቢቀረውም እስከአሁን ፓስፖርቱ ታድሶ እንዳልተሰጠው ገልጾልናል።
`` በኦንላይን ለእድት ተመዝግቤ የሚገባኝን ክፍያ ፈጽሜመጠባበቅ ጀመርኩ። እንደው ወር ሁለት ወር ይወስድብኝ ይሆናል የሚል ግምት ነበረኛ ኸው አንድ አመት ሊሞላኝ አንድ ሳምንት ቀረኝ። እስከአሁን ፓስፖርቴ ታድሶ በእጄ አልገባም።``

የኢትዮጵያ ፓስፖርት
የኢትዮጵያ ፓስፖርትምስል DW/E. B. Tekle


ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ፓስፖርቱ ለአንድ ዓመት ያህል ታድሶ በእጁ ባለመግባቱ በሙያውና በስራ አጋጥመውት የነበሩ አጫጭር የውጭ ጉዞዎች እንደተሰናከሉበት ገልጾልናል። ሌሎች በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ዜጎችም አዲስ ፓስፖርት ለማውጣትና ነባሩን ለማሳደስ ከፍተኛ መጉላላት እንደሚደርሳቸው ገልጸዋል ። 
የፌደራል ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የሕዝብ ግኑኝነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ማስተዋል ገዳን በጉዳዩ ላይ አነጋግረናቸዋል። እሳቸው ችግሩ የተፈጠረው ከውጭ ታትሞ የሚመጣው ፓስፖርት ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ ስለነበር  አዲስ አመልካቹን ለማስተናገድ ከአቅም በላይ ሆኖብን ነበር ይላሉ። አሁን ግን ውዝፉን እና አዲስ አመልካቹን ለማስተናገድ በቂ ሰራተኞች መድበን 24 ሰዓታት እሰራን ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራን ነው ብለዋል። ወይዘሮ ማስተዋል አክለውም በአንጻሩ በተገልጋዩ በኩልም በርካታ ፓስፖርት ጠያቂዎች የተዘጋጀውን ፓስፖርት በወቅቱ ባለመውሰዳቸው ከፍተኛ ክምችት መፈጠሩን ወቅሰዋል።
ፓስፖርት ለማሳደስና አዲስ ለማውጣት በሚደረግ እንቅስቃሴ አንዳንድ ደላሎችና ምግባረ ብልሹ የመስሪያቤቱ ሰራተኞች የሚፈጽሙአቸውን የሙስና ተግባራት መስሪያቤታቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ሕጋዊ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነና ሕብረተሰቡም ለዚህ ተባባሪ እንዲሆን ወይዘሮ ማስተዋል ጠይቀዋል። 
አስቸኳይ የሕክምናም ሆነ ሌላ የውጭ ጉዞ ያለባቸው ወገኖች ማስረጃቸውን ይዘው ከቀረቡ በፍጥነትና በልዩ ሁኔታ እንደሚስተናገዱም ወይዘሮ ማስተዋል አክለዋል።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሔር 

ነጋሽ መሐመድ