1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 9 2017

..." በዚህ በመሰላቸቷ ከቤቷ ትወጣለች፡፡ የአከባቢው ሽማግሌዎች ጉዳያችሁን በቤታችሁ እናይላችኋለን ተመልሰሽ ግቢ አሏት፡፡ እሷ ግን ለህይወቴ እሰጋለሁ በደንብ ታይቶ ችግሬ ካልተፈታልኝ አልገባም በማለቷ ሽማግሌዎቹ በእንጨት ላይ ታስራ እንድትገረፍ ፈረዱባት” የተጎጂ ቤተሰብ

https://p.dw.com/p/4lyxU
Symbolbild | Entführung
ምስል Nataliya_Dx/Pond5 Images/IMAGO

ከባድ የጭካኔ ድርጊት


በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን ወጫሌ ወረዳ አንዲት ሴት በአደባባይ የቆመ ግንድ ላይ ተጠፍራ በመታሰር ስትደበደብ በማህበራዊ ሚዲያ የተጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል ብዙዎችን ክፉኛ አስቆጥቷል፡፡
በባለቤቷ በአደባባይ ታስራ ስትደበደብ የሚያሳየው ይህ ድርጊት ስሜትን እጅግ የሚረብሽ ሲሉ ብዙዎች እያወገዙት ይገኛል።


ተበዳይዋን ለአደባባይ አሰቃቂ ድብደባ ያበቃት ውሳኔ
ምስራቅ ቦረና ዞን ወጫሌ ወረዳ ቀቀሎ ቀበሌ ውስጥ ኩሹ ቦነያ ጉዮ የተባለች ሴት በአደባባይ በገበያ  እንጨት ላይ ታስራ ክፉኛ ስትገረፍ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት ከመጋራቱም አልፎ የበርካቶችን ስሜት እጅግ የሚረብሽ ሆኖ ተስተውሏል፡፡ መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ተከሰተ የተባለው ይህ ድርጊት ሚስት ከባለቤቷ ጋር በነበራት አለመግባባት የተነሳ ለመታረቅ ዝግጁ አይደለችም ተብላ በአከባቢው ሽማግሌዎች ታስራ እንድትገረፍ ተወሰነባት። እናም በአደባባይ ተገረፈች። ይህ አሰቃቂ ድርጊት ብዙዎችን አስቆጥቷል።
የተጎጂዋ ወንድም ጃርሶ ቡሌ የሶስት ልጆች እናት የሆነችው እህታቸው እንዲህ በሚያሳቅቅ መልኩ በአደባባይ ታስራ የተደበደበችው በባለቤቷ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ አክለውም “እሱ ውትድርና ሄዶ ስለነበር ለአራት ዓመታት ገደማ ልጆቿን ብቻዋን ለማሳደግ ላይ ታች ስትል ነበር፡፡ እሱ ከውትድርናው ከተመለሰ በኋላም ስለቤተሰብ ማስተዳደር አሳስቦት አያውቅም፡፡ ሰርቶ ያገኘውን ጫት ይቅምበታል ጠላ ይጠጣበታል በቃ፡፡ ከዚያን ሌሊት እየገባ ይደበድባታል ተመክሮም ማንንም ልሰማ አልቻለም፡፡ በዚህ በመሰላቸቷ ከቤቷ ትወጣለች፡፡ የአከባቢው ሽማግሌዎች ጉዳያችሁን በቤታችሁ እናይላችኋለን ተመልሰሽ ግቢ አሏት፡፡ እሷ ግን ለህይወቴ እሰጋለሁ በደንብ ታይቶ ችግሬ ካልተፈታልኝ አልገባም በማለቷ ሽማግሌዎቹ በእንጨት ላይ ታስራ እንድትገረፍ ፈረዱባት” ብለዋል፡፡

የተጎጂዋ ወንድም ጃርሶ ቡሌ የሶስት ልጆች እናት የሆነችው እህታቸው እንዲህ በሚያሳቅቅ መልኩ በአደባባይ ታስራ የተደበደበችው በባለቤቷ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
የተጎጂዋ ወንድም ጃርሶ ቡሌ የሶስት ልጆች እናት የሆነችው እህታቸው እንዲህ በሚያሳቅቅ መልኩ በአደባባይ ታስራ የተደበደበችው በባለቤቷ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ምስል Depositphotos/IMAGO


ተበዳይዋን ፍትህ ለማሰጠት የተጀመረው የህግ ሂደት
የተበዳይ ወንድም አቶ ጃርሶ እንዲህ አይነት ጭካኔ የተሞላበት የሽማግሌዎች ውሳኔ በቦረና ያልተለመደ አይነት ክስተትም እንደነበር በአስተያየታቸው አስረድተዋል፡፡ እህታቸው በገበያ ውስጥ እንዲያ ታስራ ስትገረፍ የሚያሳይ ቪድዮ ሲሰራጭ ቁጭትና ንዴት እንደተሰማቸውም አልሸሸጉም፡፡ “ስትደበደብ ማንም እንዳያስጥላት ሲከለክሉ ነበር፡፡ ሴቶች ምነው የሰው ልጅ አይደለች ተውአት እንጂ ሲሉ ሰሚ አጥተዋል፡፡ ለማስጣል የመጣውን ሰው እንኳ ስለሚመቱ ሰው ሁሉ በፍርሃት ቆመው ሲመለከቱም ነበር፡፡ መጨረሻ ላይም እሷም ክፉኛ በመደብደቧ ለህይወቷም ፈርተን ሆስፒታል ወሰድናት፡፡ ለፖሊስና አቃቤ ህግም አሳወቅን፡፡ እነሱም ወንጀሉን መርምረው በድርጊቱ የተሳተፉትን 8 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው በዋጪሌ ፖሊስ ጣቢያ ከታሰሩ በኋላ አሁን ከባለቤቷ ውጪ ሌሎቹ በፍርድ ቤት በዋስ ተለቀዋልም” ነው ያሉት፡፡
ወንጀሉ ከተፈጸመ በሳምንት በኋላ ጥቆማውን መስማቱን የሚገልጸው የወረዳው አቃቤ ህግ ቪዲዮው ከተሰራጨ በኋላ የወንጀሉ ተሳታፊ የሆኑ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ይገልጻል፡፡ አቶ ጉዮ አሬሮ የወረዳው አቃቤህግ ኃላፊ ናቸው፡፡ “አሰቃቂው ድርጊት ውስጥ ተሳተፉ የተባሉ በቁጥጥር ስር ውለው የምስክሮችም ቃል ለማሰባሰብ ጥረት ተደርጎ ነበር፡፡ እሷም እንድትታከም ሆኖ የህግ ሂደቱ እስከተቻለ ድረስ እንዲሄድ ተደርጓል፡፡ አሁንም የተበዳይዋ የህክምና ማስረጃ በማቅረብ ክስ ተመስርቶ ፍትህ እንድታገኝ እየጣርን ነው” ብለዋል፡፡
የሴቶች መብት ጥሰት ክትትል
በወረዳው የሴቶች ጉዳይን ጨምሮ የባህል፤ ወጣቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚያቅፈው የአደረጃጀት ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት ሊበን ጉዮ በፊናቸው ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት በጥፋቱ የተሳተፉትን አስቀድሞ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ከማድረግ ጀምሮ ጽህፈት ቤታቸው ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ “ይህቺ ሴት በጣሙን ተጎድታለች፡፡ እንዴትስ እነዚህ ሰዎች የዋስ መብታቸው ተጠብቆላቸው ይወጣሉ ብለን ሞግተናል፡፡ አቃቤህግም ሽማግሌ የተባሉትና በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ በፍርድ ቤት በመለቀቃቸው አልረካም፡፡ አሁንም ግን የህክምና ማስረጃዋን በማቅረብ ትክክለኛ ፍትህ እንዲሰጥ መክረናል” ነው ያሉት፡፡
የወረዳው አደረጃጀት ኃላፊው አቶ ሊበን እንደሚሉት መሰል ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት በቦረና ባህልም ሆነ በገዳ ስርዓት ቦታ የለውም፡፡ “እንዲህ ያለ ባህል በቦረና ውስጥ የለም፡፡ በተለይም እንዲህ በአደባባይ ሰው አውጥተው ሰብዓዊ መብት ገፎ ማስደብደብ አንግዳ ነው የሆነብን፡፡ እናም በባህልም በህግም የሌለው ነገር በህግ ውሳኔ ፍትህ እንዲያገኝ ነው አቋማችን” ብለዋል፡፡   
ሥዩም ጌቱ   
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር