1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥሪ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 26 2015

ኮሚሽኑ በአፋር ክልል ካሳጊታ ከተማ በአንድ መኖሪያ አካባቢ በድንገት በፈነዳው የሞርታር ጥይት 4 ሰዎች ወዲያው ሕይወታቸው ማለፉን፣ በከፍተኛ ደረጃ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 5 ሰዎች ወደ ዱብቲ ሆስፒታል ተወስደው ሆስፒታል ከደረሱ በኋላም አንድ ሕፃን ሕይወቱ ማለፉን ማረጋገጡን ተናግሯል።አድዓር ወረዳም 23 ሕፃናት በፈንጂ እንደሞቱም ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/4Uh8D
Krieg betroffene Gebiete in der Afar-Region Äthiopien neu
ምስል Seyoum Getu/DW

ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የተቀብሩ ፈንጂዎች እንዲመክኑ ኢሰመኮ ጥሪ አቀረበ

 

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የተቀበሩና የወዳደቁ ፈንጂዎች በአፋር ክልል 27 ሰዎችን፣ በአማራ ክልል ቁጥራቸው ያልተገለፀ ሰዎችን ለሞት እንዲሁም ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ። ችግሩ በትግራይ ክልል ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰ ያልገለፀው ኮሚሽኑ "ጉዳት የሚያደርሱ ፈንጂዎችን የማጽዳት እና የማስወገድ ተግባር ሊፋጠን ይገባል ሲል አሳስቧል። መንግሥት የዚህ ችግር ተጎጂዎችን የማቋቋም እና የተሐድሶ አገልግሎት ድጋፎችን የማቅረብ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቋል። በአፋር የተለያዩ አካባቢዎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አካባቢውን ከፈንጂ እና ከወዳደቁ የጦር መሣሪያዎች ለማጽዳት ጥረት ማድረጉን መረዳቱን ኢሰመኮ ገልጿል። ሆኖም የተቀበረ ፈንጂ ማውጣት ላይ ብዙ ሥራ ይቀራል ሲሉ ጉዳት ከደረሰበት አካባቢ ዶቼቬለ ያነጋገርናቸው ግለሰብ አረጋግጠዋል። ስለጉዳዩ  ከመከላከያ ሚኒስቴር የፈንጂ ማምከን ቢሮ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ዶቼቬለ ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

የተተኳሽ ቁሶች አደጋ በትግራይ ክልልኢሰመኮ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ሲቪል ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች፣ በእርሻ ማሳዎች ፣ በውኃ መቅጃ ስፍራዎች ፣ በገበያ ቦታዎች ፣ በትምህርት እና በጤና ተቋማት አካባቢ የተቀበሩ ፈንጂዎች፣ የተጣሉ ቦምቦች፣ የከባድ መሣሪያ ቅሪቶች እና በቀላል ንክኪ የሚፈነዱ ሌሎች መሣሪያዎች በሰዎች ሕይወት ፣ በአካል እና በንብረት ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን ገልጿል።ኮሚሽኑ ይህን በተመለከተ ባደረገው ክትትል በአፋር ክልል፣ ካሳጊታ ከተማ በአንድ መኖሪያ አካባቢ በድንገት በፈነዳው የሞርታር ጥይት ምክንያት 4 ሰዎች ወዲያው ሕይወታቸው ማለፉን፣ በከፍተኛ ደረጃ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 5 ሰዎች ወደ ዱብቲ ሆስፒታል ተወስደው ሆስፒታል ከደረሱ በኋላም አንድ ሕፃን ሕይወቱ ማለፉን ማረጋገጡን ተናግሯል።  በዚሁ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የጠየቅናቸው በኮሚሽኑ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋዊያን መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሜቲ አቶምሳ

"ጦርነት ተካሂዶባቸው በነበሩ ቦታዎች ላይ ያለ አግባብ በምድር ላይ ሊሆን ይችላል ተቀብረው ያሉ ፈንጂዎች በተለይ ሕፃናት በሚጫወቱበት፣ ወደ ትምህርት ቤት በሚሄዱበት ወቅት አጋጣሚ ሲነኩ የሞት እና የአካል ጉዳት እያደረሱ ነው" ብለዋል።በአፋር ክልል አድዓር ወረዳ 23 ሕፃናት በወዳደቁና በተቀበሩ ፈንጂዎች ጉዳት ደርሶባቸው እንደሞቱና 20 የሚሆኑት ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ዶቼ ቬለ በአካባቢው በመንግሥት የኃላፊነት ቦታ ላይ ይሠሩ ከነበሩ ሰው ለመረዳት ችሏል። ሌላኛው የዐይን እማኝ በዚሁ ችግር ምክንያት የሞቱ ሰዎች እንደነበሩ ሆስፒታል ውስጥ መመልከቱን ገልጿል።ኢሰመኮ በጦርነቱ ወቅት በአዲአርቃይ ወረዳ ተመሳሳይ ችግር መከሰቱን በምርመራ ዘገባው አመልክቷል።

የጦርነቱ ዋነኛ ቀጣና ከነበሩት አንዱ በሆነው ትግራይ ክልል የደረሰ ጉዳት ስለመኖር አለመኖሩ ግን ያለው ነገር የለም። ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የቀሩ መሣሪያዎችን የማጽዳት እና ሙሉ በሙሉ የማስወገድ ተግባር እንዲፋጠን የጠየቀው የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ለፈንጂ ተጎጂዎች ሊደረጉ የሚገባቸው ያላቸውን የማቋቋም እና የተሐድሶ አገልግሎት ድጋፎች እንዲስፋፋም ጥሪ አቅርቧል።የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተለይ በአፋር ክልል ችግሩን ለማስወገድ በቦታው ጥረት ማድረጉን ኮሚሽኑ የክትትል ሥራውን ባከናወነበት ወቅት መረዳቱን ገልጿል። በመከላከያ ሚኒስቴር የፈንጂ ማምከን ቢሮ በጉዳዩ ላይ መረጃ መስጠት የሚችለው ሚኒስቴሩ ሲፈቅድ መሆኑን በመግለጹ ለጊዜው የሚኒስቴሩን ምላሽ ማካተት አልቻልንም።