1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጦሩ «3ኛዉን ምዕራፍ» ዉጊያ እንዲከፍት ታዘዘ

ሐሙስ፣ ኅዳር 17 2013

የኢትዮጵያ የፌደራል ጦር ኃይል በሕወሓት መሪዎችና ታጣቂዎች ላይ የከፈተዉ የጦር ዘመቻ ከመጨረሻዉ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ዐስታወቁ።

https://p.dw.com/p/3lqbQ
Äthiopien Ministerpräsident Abiy Ahmed Ali
ምስል Office of the Prime Minister/Reuters

የኢትዮጵያ የፌደራል ጦር ኃይል በሕወሓት መሪዎችና ታጣቂዎች ላይ የከፈተዉ የጦር ዘመቻ ከመጨረሻዉ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ዐስታወቁ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ዛሬ በቲዊተርና በፌስቡክ ገፃቸው (በእንግሊዝኛና በአማርኛ) ባሰራጩት መልዕክት የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)መሪዎችና ታጣቂዎች እጃቸዉን በሰላም እንዲሰጡ «የተሰጣቸዉ» ገደበ-ሰአት «ተጠናቅቋል» ብለዋል። ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ «ሕግን የማስበከር» ያሉት የመጨረሻው ዘመቻ እንዲጀመር ትእዛዝ መሰጠቱንም ይፋ አድርገዋል። ሕወሓት በሰላም እጅ እንዲሰጥ የተሰጠው የ72 ሰአታት ጊዜ መጠናቀቁን የገለጡት ጠቅላይ ሚንሥትሩ «ሕግን የማስከበር ዘመቻው የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ» መደረሱን ገልጠዋል። 

የኢትዮጵያ መንግስት «ጁንታ» የሚላቸዉ የሕወሓት መሪዎችና ተከታዮቻቸዉ ለፌደራሉ መንግሥት እጅ እንዲሰጡ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሰጡት የ72 ገደበ-ሰአት ትናንት ተጠናቅቋል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በዛሬ ማስታወቂያቸዉ የተቀመጠውን ገደበ-ሰአት ተጠቅመዉ «በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ልዩ ኃይልና የሚሊሺያ አባላት እጃቸዉን መስጠታቸዉን» ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለዉ እንዳሉት የኢትዮጵያ መከላከያ ጦር «የመጨረሻዉንና 3ኛዉን ምዕራፍ ዘመቻ» እንዲጀምር ታዟል። የኢትዮጵያ ጦር ኃይል የትግራይን ርዕሠ ከተማ መቀሌን መክበቡን ካለፈዉ እሁድ ጀምሮ ሲያስታዉቅ ነበር።

ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንደሚኖርባት በሚገመተዉ በመቀሌ ከተማ የሚደረገዉ ዉጊያ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ተፋላሚ ኃይላት ይጠነቀቁ ዘንድ እየተማፀኑ ነዉ። ጠቅላይ ሚንስትሩ በዛሬ መግለጫቸዉ ጦራቸዉ የከተማይቱን «ሕዝብ፣ ቅርሶች፣ ቤተ እምነቶች፣ የሕዝብ መገልገያዎች፣ የልማት ተቋማትና ንብረቶች እንዲሁም የሕዝብ መኖሪያ ሥፍራዎችላይ ጉዳት የማያደርስ ስልት» መንደፉን ዐስታዉቀዋል።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ